የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 12:1-32

ዘዳግም 12:1-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“በም​ድር ላይ በም​ት​ኖ​ሩ​በት ዘመን ሁሉ የአ​ባ​ቶ​ቻ​ችሁ አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትወ​ር​ሷት ዘንድ በሚ​ሰ​ጣ​ችሁ ሀገር ታደ​ር​ጉት ዘንድ የም​ት​ጠ​ብ​ቁት ሥር​ዐት፥ ፍር​ድም ይህ ነው። እና​ንተ የም​ት​ወ​ር​ሱ​አ​ቸው አሕ​ዛብ አማ​ል​ክ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን ያመ​ለ​ኩ​ባ​ቸ​ውን፥ በረ​ዥም ተራ​ሮች፥ በኮ​ረ​ብ​ቶ​ችም ላይ ከለ​ም​ለ​ምም ዛፍ በታች ያለ​ውን ስፍራ ሁሉ ፈጽ​ማ​ችሁ አጥ​ፉት፤ መሠ​ዊ​ያ​ቸ​ው​ንም አፍ​ርሱ፤ ሐው​ል​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ሰባ​ብሩ፤ የማ​ም​ለ​ኪያ ዐጸ​ዶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ቁረጡ፤ የአ​ማ​ል​ክ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ምስ​ሎች በእ​ሳት አቃ​ጥሉ፤ ከዚ​ያም ስፍራ ስማ​ቸ​ውን አጥፉ። ለአ​ም​ላ​ካ​ችሁ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ያለ ሥራ በዚያ አት​ሥሩ። ነገር ግን አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከከ​ተ​ሞ​ቻ​ችሁ ሁሉ በአ​ንዱ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመ​ረ​ጠ​ውን ስፍራ ትሻ​ላ​ችሁ፤ ወደ​ዚ​ያም ትመ​ጣ​ላ​ችሁ። ወደ​ዚ​ያም የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕ​ታ​ች​ሁን፥ ቍር​ባ​ና​ች​ሁ​ንም፥ ዐሥ​ራ​ታ​ች​ሁ​ንም፥ ቀዳ​ም​ያ​ታ​ች​ሁን፥ ስዕ​ለ​ታ​ች​ሁ​ንም፥ በፈ​ቃ​ዳ​ችሁ የም​ታ​ቀ​ር​ቡ​ትን፥ የላ​ማ​ች​ሁ​ንና የበ​ጋ​ች​ሁ​ንም በኵ​ራት ውሰዱ። በዚ​ያም በአ​ም​ላ​ካ​ችሁ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ብሉ፤ እጃ​ች​ሁ​ንም በም​ት​ዘ​ረ​ጉ​በት፥ አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በባ​ረ​ካ​ችሁ ነገር ሁሉ፥ እና​ን​ተና ቤተ​ሰ​ባ​ችሁ ደስ ይበ​ላ​ችሁ። ሰው ሁሉ በፊቱ መል​ካም መስሎ የታ​የ​ውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የም​ና​ደ​ር​ገ​ውን ሁሉ አታ​ድ​ርጉ፤ አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወደ​ሚ​ሰ​ጣ​ችሁ ማረ​ፊ​ያና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አል​ደ​ረ​ሳ​ች​ሁ​ምና። ዮር​ዳ​ኖ​ስን ግን በተ​ሻ​ገ​ራ​ችሁ ጊዜ፥ አም​ላ​ካ​ች​ሁም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሚ​ያ​ወ​ር​ሳ​ችሁ ምድር በተ​ቀ​መ​ጣ​ችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍር​ሀ​ትም እን​ድ​ት​ኖሩ ከከ​በ​ቡ​አ​ችሁ ጠላ​ቶች ሁሉ ዕረ​ፍት በሰ​ጣ​ችሁ ጊዜ፥ በዚ​ያን ጊዜ አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስሙ ይጠ​ራ​በት ዘንድ ወደ​ዚያ ወደ መረ​ጠው ስፍራ፥ እኔ የማ​ዝ​ዛ​ች​ሁን ሁሉ፥ የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕ​ታ​ች​ሁን፥ ቍር​ባ​ና​ች​ሁ​ንም፥ ዐሥ​ራ​ታ​ች​ሁ​ንም፥ ከእ​ጃ​ችሁ ሥራ ቀዳ​ም​ያ​ቱን የተ​መ​ረ​ጠ​ው​ንም መባ​ች​ሁን ሁሉ፥ ለአ​ም​ላ​ካ​ች​ሁም የተ​ሳ​ላ​ች​ሁ​ትን ሁሉ ውሰዱ። እና​ን​ተም፥ ወን​ዶች ልጆ​ቻ​ች​ሁና ሴቶች ልጆ​ቻ​ች​ሁም፥ ወን​ዶ​ችና ሴቶች አገ​ል​ጋ​ዮ​ቻ​ች​ሁም፥ ከእ​ና​ንተ ጋር ክፍ​ልና ርስት ስለ​ሌ​ለው በደ​ጆ​ቻ​ችሁ ውስጥ የተ​ቀ​መ​ጠው ሌዋ​ዊም በአ​ም​ላ​ካ​ችሁ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ደስ ይበ​ላ​ችሁ። የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕ​ት​ህን በሚ​ታ​ይህ ስፍራ ሁሉ እን​ዳ​ታ​ቀ​ርብ ተጠ​ን​ቀቅ። ነገር ግን አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከነ​ገ​ዶ​ችህ ከአ​ንዱ ዘንድ በመ​ረ​ጠው ስፍራ በዚያ የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕ​ት​ህን አቅ​ርብ፤ በዚ​ያም ዛሬ እኔ የማ​ዝ​ዝ​ህን ሁሉ አድ​ርግ። “ነገር ግን አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ሰጠህ በረ​ከት፥ እንደ ፈቀ​ድህ፥ በሀ​ገ​ርህ ሁሉ ውስጥ አር​ደህ ሥጋን ብላ፤ ከአ​ንተ ንጹሕ ሰው፥ ንጹ​ሕም ያል​ሆነ ሰው እንደ ሚዳ​ቋና እንደ ዋላ ያለ​ውን ይብ​ላው። ደሙን ግን እንደ ውኃ በም​ድር ላይ አፍ​ስ​ሱት እንጂ አት​ብ​ሉት። የእ​ህ​ል​ህን፥ የወ​ይን ጠጅ​ህን፥ የዘ​ይ​ት​ህ​ንም ዐሥ​ራት፥ የላ​ም​ህ​ንና የበ​ግ​ህ​ንም በኵ​ራት፥ የተ​ሳ​ል​ኸ​ው​ንም ስእ​ለት ሁሉ፥ በፈ​ቃ​ድህ ያቀ​ረ​ብ​ኸ​ውን፥ የእ​ጅ​ህ​ንም ቀዳ​ም​ያት በከ​ተ​ሞ​ችህ ሁሉ ውስጥ መብ​ላት አት​ች​ልም። ነገር ግን አንተ፥ ወን​ድና ሴት ልጅ​ህም፥ ወን​ድና ሴት አገ​ል​ጋ​ይ​ህም፥ በሀ​ገ​ር​ህም ውስጥ ያለው መጻ​ተኛ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በመ​ረ​ጠው ስፍራ በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ብሉት፤ እጅ​ህ​ንም በም​ት​ዘ​ረ​ጋ​በት ነገር ሁሉ በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ደስ ይበ​ልህ። በም​ድ​ርህ ላይ በም​ት​ኖ​ር​በት ዘመን ሁሉ ሌዋ​ዊ​ዉን ቸል እን​ዳ​ትል ተጠ​ን​ቀቅ። “አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ነገ​ረህ ድን​በ​ር​ህን ባሰ​ፋ​ልህ ጊዜ፥ ሰው​ነ​ት​ህም ሥጋ መብ​ላት ስለ ወደ​ደች፦ ሥጋ ልብላ ስትል፥ ሰው​ነ​ትህ ከወ​ደ​ደ​ችው ሁሉ ብላ። አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዚያ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመ​ረ​ጠው ስፍራ ከአ​ንተ ሩቅ ቢሆ​ንም፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከሰ​ጠህ ከላ​ምና ከበግ መን​ጋህ እን​ዳ​ዘ​ዝ​ሁህ እረድ፤ ሰው​ነ​ት​ህም የወ​ደ​ደ​ች​ውን በሀ​ገ​ርህ ውስጥ ብላው። ሚዳ​ቋና ዋላ እን​ደ​ሚ​በሉ እን​ዲሁ ብላው፤ ከአ​ንተ ንጹሕ ሰው፥ ንጹ​ሕም ያል​ሆነ ይብ​ላው። ደምን እን​ዳ​ት​በላ ተጠ​ን​ቀቅ፤ ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍ​ስም ከሥጋ ጋር አይ​በ​ላ​ምና። በም​ድር ላይ እንደ ውኃ አፍ​ስ​ሰው እንጂ አት​ብ​ላው። በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት መል​ካ​ምና ጥሩ የሆ​ነ​ውን ነገር ስታ​ደ​ርግ ለአ​ንተ፥ ከአ​ን​ተም በኋላ ለል​ጆ​ችህ መል​ካም እን​ዲ​ሆ​ን​ላ​ችሁ፥ አት​ብ​ላው። ነገር ግን የተ​ቀ​ደ​ሰ​ውን ነገ​ር​ህን፥ ስእ​ለ​ት​ህ​ንም ይዘህ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስሙ በዚያ እን​ዲ​ጠራ ወደ መረ​ጠው ስፍራ ሂድ። ሥጋ​ውን የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት አድ​ር​ገህ፥ በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሠ​ዊያ ላይ አቅ​ርብ፤ የመ​ሥ​ዋ​ዕ​ት​ህም ደም በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሠ​ዊያ ላይ ይፍ​ሰስ፥ ሥጋ​ው​ንም ብላው። በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት መል​ካ​ምና ጥሩ የሆ​ነ​ውን ነገር ስታ​ደ​ርግ ለአ​ንተ፥ ከአ​ን​ተም በኋላ ለል​ጆ​ችህ ለዘ​ለ​ዓ​ለም መል​ካም ይሆ​ን​ላ​ችሁ ዘንድ እኔ የማ​ዝ​ዝ​ህን እነ​ዚ​ህን ቃሎች ሁሉ ሰም​ተህ ጠብቅ። “አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትወ​ር​ሳ​ቸው ዘንድ የም​ት​ሄ​ድ​ባ​ቸ​ውን አሕ​ዛብ በፊ​ትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አን​ተም በወ​ረ​ስ​ሃ​ቸው ጊዜ፥ በም​ድ​ራ​ቸ​ውም በተ​ቀ​መ​ጥህ ጊዜ፥ ከፊ​ትህ ከጠፉ በኋላ እነ​ር​ሱን ለመ​ከ​ተል እን​ዳ​ትሻ፥ አም​ላ​ኮ​ቻ​ቸ​ው​ንም እን​ዳ​ትሻ፥ አሕ​ዛ​ብም ለአ​ም​ላ​ኮ​ቻ​ቸው እን​ደ​ሚ​ያ​ደ​ርጉ እኔም አደ​ር​ጋ​ለሁ እን​ዳ​ትል ራስ​ህን ጠብቅ። ለአ​ም​ላ​ክህ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲሁ አታ​ድ​ርግ፤ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ልጆ​ቻ​ቸ​ውን ለአ​ም​ላ​ኮ​ቻ​ቸው በእ​ሳት ስለ​ሚ​ያ​ቃ​ጥሉ አሕ​ዛብ ለአ​ም​ላ​ኮ​ቻ​ቸው የሚ​ያ​ደ​ር​ጉ​ትን ርኩስ ነገር እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይጠ​ላ​ልና። “እኔ ዛሬ የማ​ዝ​ዝ​ህን ነገር ሁሉ ታደ​ር​ገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእ​ርሱ ላይ አት​ጨ​ምር፤ ከእ​ር​ሱም ምንም አታ​ጕ​ድል።

ዘዳግም 12:1-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ)፣ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዐቶችና ሕግጋት እነዚህ ናቸው። ከምድራቸው የምታስለቅቋቸው አሕዛብ በረጃጅም ተራሮች፣ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ። መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ። በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አታምልኩ። ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ። ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ። በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ። ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤ ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም። ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል። ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት አድርጉ። የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝዝህን ሁሉ ጠብቅ። ሆኖም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ መጠን፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል። ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይልሃል። በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ። ስሙን ለማኖር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ፤ ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ። ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለሆነ፣ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ። ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው። ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። የሚቃጠል መሥዋዕትህን፣ ሥጋውንም ደሙንም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ። በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘላለም መልካም እንዲሆንላችሁ፣ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው። የምትወርሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ። እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ አትጨምርበት፤ አትቀንስለትም።

ዘዳግም 12:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በምድር ላይ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ለመውረስ በሰጣችሁ አገር፥ የምትጠብቁአትና የምታደርጉአት ሥርዓትና ፍርድ እነዚህ ናቸው። እናንተ የምትወርሱአቸው አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩባቸውን በረጅም ተራሮች በኮረብቶችም ላይ ከለምለምም ዛፍ በታች ያለውን ስፍራ ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉአቸው፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፥ የአማልክቶቻቸውንም የተቀረጹ ምስሎች አንከታክቱ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሥራ አትሥሩ። ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ። ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ። በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ብሉ፥ እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ። ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የምናደርገውን ሁሉ አታደርጉም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ዕረፍትና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አልገባችሁምና። ዮርዳኖስን ግን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሚያወርሳችሁ ምድር በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍርሃትም እንድትኖሩ ከከበቡአችሁ ጠላቶች ሁሉ ዕረፍት በሰጣችሁ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁ ያነሣችሁትንም ቍርባን፥ ለእግዚአብሔርም ተስላችሁ የመረጣችሁትን ስእለታችሁን ሁሉ ውሰዱ። እናንተም፥ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ባሪያዎቻችሁም፥ ገረዶቻችሁም፥ ከእናንተ ጋር ክፍልና ርስት ስለሌለው በደጆቻችሁ ውስጥ የተቀመጠው ሌዋዊም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በሚታይህ ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከነገዶችህ ከአንዱ ዘንድ በመረጠው ስፍራ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብ፥ በዚያም የማዝዝህን ሁሉ አድርግ። ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰጠህ በረከት፥ ሰውነትህ እንደ ፈቀደ፥ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ አርደህ ብላ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሰው እንደ ሚዳቍና እንደ ዋላ ያለውን ይብላው። ደሙን ግን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም አሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህም ያቀረብኸውን፥ በእጅህም ያነሣኸውን ቍርባን በደጆችህ ውስጥ መብላት አትችልም። ነገር ግን አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም፥ ባሪያዎችህና ገረዶችህም፥ በአገርህም ደጅ ያለው ሌዋዊ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉት፤ እጅህንም በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። በምድርህ ላይ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ። አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ አገርህን ባሰፋ ጊዜ፥ ሰውነትህም ሥጋ መብላት ስለ ወደደች፦ ሥጋ ልብላ ስትል፥ እንደ ሰውነትህ ፈቃድ ሥጋን ብላ። አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙን ያኖር ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፥ እንደ ሰውነትህም ፈቃድ ሁሉ በአገርህ ደጅ ውስጥ ብላ። ሚዳቍና ዋላ እንደሚበሉ እንዲሁ ብላው፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ይብላው። ነገር ግን ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍሱንም ከሥጋው ጋር መብላት አይገባህምና ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ። በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፥ አትብላው። ነገር ግን የተቀደሰውን ነገርህን ስእለትህንም ይዘህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕትህን፥ ሥጋውንና ደሙን፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የመሥዋዕትህም ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፥ ሥጋውንም ብላው። በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘላለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ። አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብን በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥ በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትጠመድ፦ እነዚህስ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩት እንዴት ነው? እንዲሁ ደግሞ እኔ አደርጋለሁ ብለህ ስለ አማልክቶቻቸው እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ። እግዚአብሔር የሚጠላውን ርኵሰት ሁሉ እነርሱ ለአማልክቶቻቸው አድርገዋልና፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ ለአማልክቶቻቸው በእሳት ያቃጥሉአቸዋልና አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ። እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል።

ዘዳግም 12:1-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በሚሰጣችሁ ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቁአቸው ኅጎችና ሥርዓቶች እነዚህ ናቸው፤ በምትወርሱአት ምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በተራሮች፥ በኮረብቶችና በለመለሙ ዛፎች ሥር ለአማልክታቸው የሚሰግዱባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ደምስሱ፤ መሠዊያዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ፤ ከድንጋይ የተሠሩ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም አድቅቁ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላካቸውን ምስሎች ሁሉ በእሳት አቃጥሉ፤ የተቀረጹ ጣዖቶቻቸውን ሰባብሩ፤ ስሞቻቸውንም ከቦታቸው አጥፉ። “እናንተ ለእግዚአብሔር አምላካችሁ የምትሰግዱለት እነዚህ አሕዛብ ለአማልክታቸው በሚሰግዱላቸው ዐይነት መሆን የለበትም። አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ መካከል ለእርሱ መኖሪያ ይሆን ዘንድ በዚያ ስሙ እንዲጠራበት የሚመርጠውን ቦታ ፈልጉና ወደዚያ ሂዱ፤ እዚያም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትንና የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን፥ የከብቶቻችሁንና የበጎቻችሁን በኲር ታቀርባላችሁ፤ እዚያም በባረካችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት እናንተና ቤተሰቦቻችሁ ሁሉ ተሰብስባችሁ ትበላላችሁ፤ በድካማችሁ ያገኛችሁትን መልካም ነገር ሁሉ ትደሰቱበታላችሁ። “ያ ሰዓት በሚደርስበት ጊዜ እስከ አሁን እንደ ፈለጋችሁ በምትፈጽሙት ዐይነት አታደርጉም፤ እነሆ እስከ አሁን የመሰላችሁን ታደርጉ ነበር፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ወደሚሰጣችሁና በሰላም ዕረፍት አድርጋችሁ ወደምትኖሩባት ርስት ገና አልገባችሁም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ ምድር ለመኖር ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ በደኅና እንድትኖሩ በዙሪያ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ዕረፍት ይሰጣችኋል፤ ከዚያም እኔ ያዘዝኳችሁን ነገር ሁሉ የምታመጡት እግዚአብሔር አምላካችሁ ለስሙ መጠሪያ ወደ መረጠው ቦታ ይሆናል፤ ይኸውም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን ሁሉ ታመጡለታላችሁ። እናንተ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻችሁ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮቻችሁ፥ እንዲሁም ከእናንተ ጋር የርስት ክፍያ ከሌላቸው በከተሞቻችሁ ከሚኖሩ ከሌዋውያን ጋር በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ትደሰታላችሁ። የሚቃጠል መሥዋዕትህን በማናቸውም ቦታ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። መሥዋዕትህን ሁሉ ማቅረብ የሚገባህ ከነገዶችህ መካከል የአንዱ ግዛት በሆነው ክፍል እና እግዚአብሔር በሚመርጠው በአንድ ስፍራ ብቻ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህንም ሆነ ሌላውንም እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ በዚያ ስፍራ ብቻ ትፈጽማለህ። “ሆኖም በሚያሰኛችሁ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ በረከት መሠረት ከከተሞቻችሁ በማናቸውም ቦታ ዐርዳችሁ ልትበሉ ትችላላችሁ፤ የአጋዘንና የሚዳቋ ሥጋ ለመብላት እንደሚችል ንጹሕ የሆነ ወይም ንጹሕ ያልሆነ ሰው ያን የታረደውን ሥጋ ሊበላው ይችላል። ነገር ግን ደማቸውን አትብላ፤ ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው፤ ለእግዚአብሔር የምታቀርበው መባ በምትኖርበት በማናቸውም ስፍራ ሁሉ መበላት የለበትም፤ ይኸውም የእህልህ፥ የወይን ጠጅህ፥ የወይራ ዘይትህ ዐሥራት ወይም የከብቶችህና የበጎችህ በኲር፥ ለእግዚአብሔር የተሳልከው የበጎ ፈቃድ ስጦታህ ሁሉ በማናቸውም የመኖሪያ ስፍራ ሁሉ አይበላም። አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጥልህ ቦታ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ፥ እንዲሁም በከተሞችህ ከሚኖሩ ሌዋውያን ጋር እነዚህን ትበላለህ፤ እዚያም በድካምህ ያገኘኸውን መልካም ነገር ሁሉ ትደሰትበታለህ፤ በምድርህ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋውያንን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ። “በሰጠህ ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር ግዛትህን በሚያሰፋበት ጊዜ፥ በሚያሰኝህ ጊዜ ሁሉ ሥጋ መመገብ ትችላለህ። እግዚአብሔር የመረጠው ያ አንድ ስፍራ ሩቅ ቢሆንብህ ግን በሚያሰኝህ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጠህ የከብትም ሆነ የበግ መንጋ መርጠህ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ማረድ ትችላለህ፤ ሥጋውንም በቤት ትበላዋለህ። የነጻም ሆነ ያልነጻ ማንኛውም ሰው የአጋዘንም ሆነ የሚዳቋ ሥጋ በሚበላው ዐይነት ያንን ሥጋ መብላት ይችላል። ነገር ግን የሕይወት መኖሪያ በደም ውስጥ ስለ ሆነ ደም ያለበትን ሥጋ ከመብላት ብቻ ተጠንቀቅ፤ ስለዚህ ሕይወትን ከሥጋ ጋር አትብላ። ደምን አትብላ፤ ይልቅስ እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው። ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆንልህ ዘንድ ደምን አትብላ፤ ይህንንም በማድረግህ እግዚአብሔርን ደስ ታሰኛለህ። ስለዚህም የተቀደሰ መባህንና ለእግዚአብሔር የተሳልከውን ስጦታ ወደተመረጠው ቦታ ብቻ ውሰድ። የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን፥ ማለትም ሥጋውንና ደሙን ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ። የሌሎች መሥዋዕቶችህ ደም ከአምላክህ ከእግዚአብሔር መሠዊያ አጠገብ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን ልትበላ ትችላለህ። ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘለዓለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ ይህንንም ስታደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገርን ማድረግህ ነው። “በምድራቸው ላይ ጦርነት በምታደርግበት ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቦችን ይደመስሳል፤ ምድራቸውንም ወርሰህ ትኖርበታለህ። እነዚህ ሕዝቦች ከተደመሰሱ በኋላ እነርሱ ያደርጉ የነበረውን ድርጊት በማድረግ ወጥመድ ውስጥ አትግባ፤ እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ በማለት እነዚህ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን እንዴት ያመልኩ ነበር ብለህ አትጠይቅ። አንተ ለእግዚአብሔር ለአምላክህ የምትሰግድለት፥ እነዚህ አሕዛብ ለባዕዳን አማልክታቸው በሚሰግዱላቸው ዐይነት መሆን የለበትም፤ እነርሱ ለባዕዳን አማልክቶቻቸው በሚሰግዱበት ጊዜ የሚፈጽሙት ነገር ሁሉ እጅግ አጸያፊና በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፤ እነርሱ ሌላው ቀርቶ የገዛ ልጆቻቸውን በመሠዊያዎቻቸው ላይ ለአማልክታቸው በእሳት ያቃጥላሉ። “እንግዲህ እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ አድርግ፤ በእርሱ ላይ ምንም ነገር አትጨምር፤ ከእርሱም አንዳች ነገር አታጒድል።

ዘዳግም 12:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“የአባቶቻችሁ አምላክ ጌታ፥ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፥ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዓቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው። ከምድራቸው የምታስለቅቋቸው አሕዛብ በረጅሙ ተራሮች፥ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ። መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ አምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የ ‘አሼራ’ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቆራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።” “በዚያ ዓይነት አካሄድ ጌታ አምላካችሁን አታምልኩ። ነገር ግን ጌታ አምላካችሁ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፥ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ ትሻላችሁ፤ ወደ እዚያም ስፍራ ትሄዳላችሁ። እዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፥ አሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፥ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፥ የከብት መንጋችሁን እና የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አቅርቡ። በዚያም በጌታ በአምላካችሁ ፊት ትበላላችሁ፤ ጌታ አምላካችሁ እናንተን በባረከበት፥ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተሰቦችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።” “ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፥ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤ ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና ጌታ አምላካችሁ ወደ የሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም። ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፥ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል። ጌታ አምላካችሁም ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁን ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፥ አሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፥ እንዲሁም ለጌታ የተሳላችሁትን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። እዚያም እናንተ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፥ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በጌታ በአምላካችሁ ፊት ሐሤት አድርጉ።” “የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፥ ጌታ በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝህን ሁሉ ጠብቅ።” “ሆኖም ጌታ አምላክህ በሚሰጥህ መጠን፥ በየትኛውም ከተማህ፥ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኩላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ። በሥርዓቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል። ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። የእህልህን፥ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን አሥራት፥ ወይም የቀንድ ከብት፥ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፥ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፥ ወይም የእጅህን ስጦታ፥ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም። አምላክህ ጌታ በሚመርጠው ስፍራ አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፥ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፤ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፥ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይልሃል። በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።” “አምላክህ ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፥ ሥጋ አምሮህ፥ ‘ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ’ በምትልበት ጊዜ፥ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ። ስሙን ለማኖር ጌታ እግዚአብሔር የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፥ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፥ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ። ሚዳቋ ወይም ድኩላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ መብላት ይችላል። ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለ ሆነ፥ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ። ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። በጌታ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፥ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው። ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ ጌታ ወደ የሚመርጠው ስፍራ ሂድ። የሚቃጠል መሥዋዕትህን፥ ሥጋውንም ደሙንም በጌታ አምላክህ መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በጌታ አምላክህ መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ። በአምላክህ በጌታ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፥ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘለዓለም መልካም እንዲሆንላችሁ፥ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው።” “የምትወሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ ጌታ ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፥ ‘እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ’ ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። አምላክህን ጌታ በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ ጌታ የሚጸየፈውን ሁሉንም ዓይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳን ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።” “እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ በእርሱ ላይ ምንም አትጨምር፤ ከእርሱም አንዳች ነገር አትቀንስ።”