ዳንኤል 9:16-18
ዳንኤል 9:16-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጌታ ሆይ፤ ቀድሞ እንዳደረግኸው የጽድቅ ሥራህ ሁሉ፣ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም፣ ከቅዱሱም ተራራህ ቍጣህን መልስ፤ በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችን በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ዘንድ መሣለቂያ ሆነዋል። “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ። አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው።
ዳንኤል 9:16-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጌታ ሆይ፥ ስለ ኃጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና እንደ ጽድቅህ ሁሉ ቍጣህና መዓትህ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ከቅዱስ ተራራህ እንዲመለስ እለምንሃለሁ። አሁንም፥ አምላካችን ሆይ፥ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፥ ጌታ ሆይ፥ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ። አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፥ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት።
ዳንኤል 9:16-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጌታ ሆይ! ስለ ፈጸምካቸው የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ብለህ ከተቀደሰችው ተራራህ ከኢየሩሳሌም ቊጣህንና መዓትህን እንድታነሣ እንለምንሃለን፤ በኃጢአታችንና በአባቶቻችንም በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በጐረቤቶቻችን ሁሉ መካከል ተዋርደዋል። አምላክ ሆይ! ጸሎቴንና ልመናዬን ስማ፤ ስለ ስምህ ስትል ለፈረሰው ቤተ መቅደስህ ራራ። አምላክ ሆይ! እባክህ አድምጠኝ፤ የእኛን ችግርና በስምህ የምትጠራውን ከተማ ጥፋት ተመልከት፤ ወደ አንተ የምንጸልየው የአንተን ምሕረት በመተማመን እንጂ በእኛ መልካም ሥራ በመመካት አይደለም።