የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 7:9-14

ዳንኤል 7:9-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“እኔም ስመለከት፣ “ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ የራሱም ጠጕር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆ ይፈስስ ነበር፤ ሺሕ ጊዜ ሺሖች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤ የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቅቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም። ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፍፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው። “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።

ዳንኤል 7:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፥ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፥ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፥ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ። የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፥ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ። ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፥ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ። በሌሊት ራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፥ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፥ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።

ዳንኤል 7:9-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“እኔም እየተመለከትኩ ሳለሁ ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ያ ጥንታዊው በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ፥ ጠጒሩም እንደ ነጭ ሱፍ ነበር፤ ዙፋኑና የዙፋኑ መንኰራኲር እንደሚነድ እሳት ይንበለበሉ ነበር። የእሳትም ምንጭ ከዙፋኑ ፊት ይፈልቅ ነበር፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ አገልጋዮች ነበሩት፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ችሎት ተጀመረ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። “ቀንዱ የሚናገረውን የዕብሪታዊ ንግግር ድምፅ ሰምቼ ተመለከትኩ፤ እየተመለከትኩም ሳለ አውሬው ተይዞ ከተገደለ በኋላ ወደ እሳት በመጣል አካሉ እንዲጠፋ ተደረገ። ሌሎቹም አውሬዎች ሥልጣናቸውን ተነጠቁ፤ ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው። “በሌሊትም ራእይ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከቦ ሲመጣ አየሁ፤ ወደዚያ ወደ ዘለዓለማዊው ፊት አቀረቡት። በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፥ ክብርና ንጉሥነት ተሰጠው፤ ግዛቱም የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።