ዳንኤል 7:24-27
ዳንኤል 7:24-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዐሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚወጡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ከእነርሱ የተለየ ሌላ ንጉሥ ይነሣል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያንበረክካል። በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ ለበዓላት የተመደበውን ጊዜና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል፤ ቅዱሳንም ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም ለእርሱ ዐልፈው ይሰጣሉ። “ ‘ነገር ግን የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ ሥልጣኑም ይወሰድበታል፤ ፈጽሞ ለዘላለም ይደመሰሳል። ከዚያም ከሰማይ በታች ያሉ መንግሥታት ልዕልና፣ ሥልጣንና ታላቅነት ለልዑሉ ሕዝብ፣ ለቅዱሳን ይሰጣል። መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ይሆናል፤ ገዦች ሁሉ ያመልኩታል፤ ይታዘዙታልም።’
ዳንኤል 7:24-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፥ ከእነሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፥ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፥ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል። በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፥ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ። ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፥ እስከ ፍጻሜም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል። መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፥ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል።
ዳንኤል 7:24-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዐሥሩ ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡት ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያን በኋላ ከበፊተኞቹ ነገሥታት የተለየ ሌላ ንጉሥ ተነሥቶ ከዐሥሩ መንግሥታት ሦስቱን ይገለብጣል፤ በልዑል እግዚአብሔር ላይ በመታበይ ይናገራል፤ የልዑል እግዚአብሔርንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ የተቀደሱ በዓላትንና ሕጉን ለመለወጥ ያቅዳል፤ ቅዱሳኑም ለሦስት ዓመት ተኩል በእርሱ ሥልጣን ሥር ይሆናሉ። ከዚያን በኋላ የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ እርሱም መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተገፎ ለዘለዓለም ይደመሰሳል፤ ከሰማይ ሁሉ በታች በምድር ላይ ያለ የመንግሥት ሥልጣን፥ ኀይልና ገናናነት ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ይሰጣል፤ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የዓለም ግዛቶች ሁሉም ለእነርሱ በመታዘዝ ያገለግሉአቸዋል።’ ”