ዳንኤል 7:1-12
ዳንኤል 7:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም ዐለመ፤ ራእይም አየ፤ የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው። ዳንኤል እንዲህ አለ፤ “አራቱ የሰማይ ነፋሳት ታላቁን ባሕር ሲያናውጡት ሌሊት በራእይ አየሁ። እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕሩ ወጡ። “የመጀመሪያው፣ አንበሳ ይመስል ነበር፤ የንስርም ክንፎች ነበሩት፤ ክንፎቹ እስኪነቃቀሉ ድረስ ተመለከትሁ፤ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምድር ከፍ ከፍ ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው። “እነሆም፤ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር፤ በአንድ ጐኑ ከፍ ብሏል፤ በአፉ ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጐድን ዐጥንቶች ነበሩት። እርሱም፤ ‘ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!’ ተባለ። “ከዚያ በኋላ ተመለከትሁ፤ በፊቴ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤ በጀርባውም በኩል የወፍ ክንፍ የሚመስሉ አራት ክንፎች ነበሩት፤ ይህ አውሬ አራት ራስ ነበረው፤ ለመግዛትም ሥልጣን ተሰጠው። “ከዚህ በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ በፊቴም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ የሆነ አራተኛ አውሬ ነበር፤ ትልልቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ያደቅቅና ይበላ፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር። ከእርሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን፣ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት። “ስለ ቀንዶቹ ሳስብ ሳለሁ፣ ከመካከላቸው አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ ብቅ ሲል አየሁ፤ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች ሦስቱ ከፊቱ ተነቃቀሉ፤ ይህም ቀንድ የሰው ዐይኖችን የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበረው። “እኔም ስመለከት፣ “ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ የራሱም ጠጕር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆ ይፈስስ ነበር፤ ሺሕ ጊዜ ሺሖች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤ የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቅቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም። ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፍፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።
ዳንኤል 7:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፥ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ ዋነኛውንም ነገር ተናገረ። ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፦ በሌሊት በራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር። አራትን ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች። መጀመሪያይቱ አንበሳ ትመስል ነበር፥ የንስርም ክንፍ ነበራት፥ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፥ ከምድርም ከፍ ከፍ ተደረገች፥ እንደ ሰውም በሁለት እግር እንድትቆም ተደረገች፥ የሰውም ልብ ተሰጣት። እነሆም፥ ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፥ በአንድ ወገንም ቆመች፥ ሦስትም የጐድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርስዋ መካከል ነበሩ፥ እንደዚህም፦ ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ ተባለላት። ከዚህም በኋላ፥ እነሆ፥ ነብር የምትመስል በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት ሌላ አውሬ አየሁ፥ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፥ ግዛትም ተሰጣት። ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፥ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፥ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፥ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት። ቀንዶችንም ተመለከትሁ፥ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፥ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት። ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፥ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፥ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፥ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ። የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፥ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ። ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፥ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ።
ዳንኤል 7:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በአልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ፤ ዳንኤል ሕልምና ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ያየውን ሕልም ጻፈ። እርሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ዳንኤል ከአራቱ ማእዘን የተነሣ ነፋስ ታላቁን ባሕር ሲያናውጥ ሌሊት በራእይ አየሁ። አራት የተለያዩ ታላላቅ አውሬዎች ከባሕሩ ወጡ። የመጀመሪያው አውሬ አንበሳ ይመስል ነበር፤ እርሱም እንደ ንስር ያሉ ክንፎች ነበሩት፤ እኔም እየተመለከትኩት ክንፎቹ ተነቃቀሉ፤ አውሬውም ቀና ብሎ እንደ ሰው በሁለት እግሮቹ ቆመ፤ ሰብአዊ አእምሮም ተሰጠው። “ሁለተኛው አውሬ በኋላ እግሮቹ ሸብረክ ብሎ እንደ ቆመ ድብ ይመስል ነበር፤ በጥርሶቹም ሦስት የጐድን አጥንት ነክሶ ይዞአል፤ ‘የፈለግኸውን ያኽል ሥጋ ብላ!’ የሚል ድምፅም ተነገረው። “ይህንን በመመልከት ላይ ሳለሁ እነሆ፥ ሌላ ነብር የሚመስል አውሬ ወጣ፤ እርሱም የወፍ ክንፎች የሚመስሉ አራት ክንፎች በጀርባው ላይ ነበሩት፤ አራት ራሶችም ነበሩት፤ የገዢነት ሥልጣንም ተሰጠው። “ከዚያ በኋላ አራተኛውን አውሬ አየሁ፤ እርሱም አስፈሪ፥ አስደንጋጭና በጣም ኀይለኛ ነበር፤ ይህም አውሬ የሚቦጫጭቅባቸውና የሚሰባብርባቸው ታላላቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት። የተረፈውንም በእግሮቹ ይረግጠው ነበር፤ ካለፉትም አውሬዎች ሁሉ የተለየ ሆኖ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት። እኔም ስለ ቀንዶቹ በማሰላሰል ላይ ሳለሁ ከቀንዶቹ መካከል ሌላ አንድ ትንሽ ቀንድ ወጣ፤ ለእርሱም ቦታ ለመልቀቅ ከፊተኞቹ ቀንዶች ሦስቱ ተነቀሉ፤ ይህም ትንሽ ቀንድ የሰው ዐይኖችና በትዕቢት የሚናገር አንደበት ነበረው። “እኔም እየተመለከትኩ ሳለሁ ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ያ ጥንታዊው በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ፥ ጠጒሩም እንደ ነጭ ሱፍ ነበር፤ ዙፋኑና የዙፋኑ መንኰራኲር እንደሚነድ እሳት ይንበለበሉ ነበር። የእሳትም ምንጭ ከዙፋኑ ፊት ይፈልቅ ነበር፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ አገልጋዮች ነበሩት፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ችሎት ተጀመረ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። “ቀንዱ የሚናገረውን የዕብሪታዊ ንግግር ድምፅ ሰምቼ ተመለከትኩ፤ እየተመለከትኩም ሳለ አውሬው ተይዞ ከተገደለ በኋላ ወደ እሳት በመጣል አካሉ እንዲጠፋ ተደረገ። ሌሎቹም አውሬዎች ሥልጣናቸውን ተነጠቁ፤ ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።