ዳንኤል 5:1-31
ዳንኤል 5:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጉሥ ቤልሻዛር ለሺሕ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በሺሑም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። ቤልሻዛር የወይን ጠጁን እየጠጣ ሳለ፣ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የወርቅና የብር መጠጫዎችን እርሱና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ። ከዚያም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅ መጠጫዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹም ጠጡባቸው። የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገኑ። በድንገትም የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ ጻፉ፤ ንጉሡም ይጽፍ የነበረውን እጅ አየ፤ በዚያን ጊዜ ንጉሡ በድንጋጤ ተሞላ፤ ፊቱም ተለዋወጠ፤ እጆቹና እግሮቹ ከዱት፤ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ። ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ አስማተኞችን፣ ኮከብ ቈጣሪዎችንና መተተኞችን እንዲያስገቡለት አዘዘ፤ ለባቢሎናውያኑ ጠቢባን እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጕሙን የሚነግረኝን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለብሰዋለሁ፤ የወርቅ ሐብልም በዐንገቱ ላይ አጠልቅለታለሁ፤ በመንግሥቴም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል።” ከዚያም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ሊያነብም ሆነ ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ ለንጉሡ ሊነግር የሚችል ማንም አልነበረም። ንጉሥ ቤልሻዛር ከፊት ይልቅ ፈራ፤ ፊቱም እጅግ ተለወጠ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቷቸው ተደናገጡ። ንግሥቲቱም የንጉሡንና የመኳንንቱን ድምፅ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች፤ እንዲህም አለች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ አትደንግጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ! በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብና ማስተዋል፣ ዕውቀትም የሞላበት ሆኖ ተገኝቷል፤ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆርም የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቈጣሪዎችና የመተተኞች አለቃ አደረገው። ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጐም፣ ዕንቈቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጕም ይነግርሃል።” ዳንኤልንም ወደ ንጉሡ አቀረቡት፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ማርኮ ካመጣቸው መካከል አንዱ የሆንኸው ዳንኤል አንተ ነህን? የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋልና ልዩ ጥበብ እንዳለህ ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበው ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ ይነግሩኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች በፊቴ ቀርበው ነበር፤ ነገር ግን ሊገልጡት አልቻሉም። አንተ ግን መተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር መፍታት እንደምትችል ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጕሙን ብትነግረኝ፣ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ያለብሱሃል፤ የወርቅ ሐብል በዐንገትህ ያጠልቁልሃል፤ የመንግሥት ሦስተኛ ገዥም ትደረጋለህ።” ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ስጦታዎችህን ለራስህ አድርግ፤ ሽልማቶችህንም ለሌላ ሰው ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ፤ ትርጕሙ ምን እንደ ሆነም እነግረዋለሁ። “ንጉሥ ሆይ፤ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትንና ታላቅነትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው። ከሰጠው ታላቅ ሥልጣን የተነሣ ሕዝቦችና መንግሥታት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም ሁሉ ተንቀጠቀጡለት፤ ፈሩትም። ንጉሡም ሊገድል የፈለገውን ይገድል፣ ሊያድን የፈለገውን ያድን፣ ሊሾም የፈለገውን ይሾም፣ ሊያዋርድ የፈለገውንም ያዋርድ ነበር። ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸናና በእብሪት በተሞላ ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ። ከሰው መካከል ተሰደደ፤ የእንስሳም አእምሮ ተሰጠው፤ ከዱር አህዮች ጋር ኖረ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ፤ ልዑል አምላክ በሰዎች መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እነርሱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስኪያውቅ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ። “ቤልሻዛር ሆይ፤ አንተ ልጁ ሆነህ ይህን ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም፤ ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ፣ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቍባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ፣ የናስና የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም። ስለዚህ እርሱ ጽሕፈቱን የጻፈውን እጅ ላከ። “የተጻፈውም ጽሕፈት፣ ‘ማኔ፣ ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ’ ይላል። “የቃሉም ትርጕም ይህ ነው፤ ‘ማኔ’ ማለት እግዚአብሔር የመንግሥትህን ዘመን ቈጠረው፤ ወደ ፍጻሜም አደረሰው ማለት ነው። ‘ቴቄል’ ማለት በሚዛን ተመዘንህ፤ ቀለህም ተገኘህ፣ ማለት ነው። ‘ፋሬስ’ ማለት መንግሥትህ ተከፈለ፣ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።” ከዚህ በኋላ በቤልሻዛር ትእዛዝ ዳንኤልን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለበሱት፣ የወርቅ ሐብል በዐንገቱ ላይ አጠለቁለት፤ የመንግሥቱም ሦስተኛ ገዥ ሆኖ ተሾመ። በዚያኑ ሌሊት የባቢሎናውያን ንጉሥ ቤልሻዛር ተገደለ፤ የስድሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስም መንግሥቱን ወሰደ።
ዳንኤል 5:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቶቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ፦ አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ ብሎ አዘዘ። የዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጡትን የወርቁን ዕቃዎች አመጡ፥ ንጉሡና መኳንንቶቹም ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው። የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ። በዚያም ሰዓት የሰው ልጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፉ፥ ንጉሡም የሚጽፉትን ጣቶች አየ። የዚያን ጊዜም የንጉሡ ፊት ተለወጠበት፥ አሳቡም አስቸገረው፥ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፥ ጉልበቶቹም ተብረከረኩ። ንጉሡም አስማተኞቹንና ከለዳውያኑን ቃላተኞቹንም ያገቡ ዘንድ በታላቅ ድምፅ ጮኽ፥ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን፦ ይህን ጽሕፈት ያነበበ ፍቺውንም ያሳየኝ ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል፥ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል ብሎ ተናገረ። የዚያን ጊዜም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፥ ነገር ግን ጽሕፈቱን ያነብቡ፥ ፍቺውንም ለንጉሡ ያስታወቁ ዘንድ አልቻሉም። ንጉሡም ብልጣሶር እጅግ ደነገጠ፥ ፊቱም ተለወጠበት፥ መኳንንቶቹም ተደናገጡ። ንግሥቲቱም ስለ ንጉሡና ስለ መኳንንቱ ቃል ወደ ግብዣ ቤት ገባች፥ ንግሥቲቱም ተናገረች እንዲህም አለች፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፥ አሳብህ አያስቸግርህ፥ ፊትህም አይለወጥ። የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው በመንግሥትህ ውስጥ አለ፥ በአባትህም ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብና ማስተዋል እውቀትም ተገኘበት፥ አባትህ ንጉሡ ናቡከደነፆር የሕልም ተርጓሚዎችና የአስማተኞች የከለዳውያንና የቃላተኞች አለቃ አደረገው። መልካም መንፈስ፥ እውቀትም፥ ማስተዋልም፥ ሕልምንም መተርጐም፥ እንቈቅልሽንም መግለጥ፥ የተቋጠረውንም መፍታት ንጉሡ ስሙን ብልጣሶር ብሎ በሰየመው በዳንኤል ዘንድ ተገኝቶአልና። አሁንም ዳንኤል ይጠራ፥ እርሱም ፍቺውን ያሳያል። የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ንጉሡ ፊት ገባ፥ ንጉሡም ተናገረው ዳንኤልም እንዲህ አለው፦ ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ከማረካቸው ከይሁዳ ምርኮኞች የሆንህ ዳንኤል አንተ ነህን? የአማልክት መንፈስ እንዳለብህ፥ እውቀትና ማስተዋልም መልካምም ጥበብ እንደ ተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ። አሁንም ይህን ጽሕፈት ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ያስታውቁኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች ወደ እኔ ገብተው ነበር፥ ነገር ግን የነገሩን ፍቺ ያሳዩ ዘንድ አልቻሉም። አንተ ግን ፍቺን ትሰጥ ዘንድ፥ የተቋጠረንም ትፈታ ዘንድ እንድትችል ሰምቻለሁ፥ አሁንም ጽሕፈቱን ታነብብ ዘንድ፥ ፍቺውንም ታስታውቀኝ ዘንድ ብትችል፥ ሐምራዊ ግምጃ ትለብሳለህ፥ የወርቅም ማርዳ በአንገትህ ዙሪያ ይሆንልሃል፥ አንተም በመንግሥት ላይ ሦስተኛ ገዢ ትሆናለህ። የዚያን ጊዜም ዳንኤል መለሰ በንጉሡም ፊት እንዲህ አለ፦ ስጦታህ ለአንተ ይሁን፥ በረከትህንም ለሌላ ስጥ፥ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ ፍቺውንም አስታውቃለሁ። ንጉሥ ሆይ፥ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን ክብርንና ግርማን ሰጠው። ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፥ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፥ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር። ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው። ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፥ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። ብልጣሶር ሆይ፥ አንተ ልጁ ስትሆን ይህን ሁሉ እያወቅህ በሰማይ ጌታ ላይ ኰራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም። የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፥ ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፥ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም። ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፥ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። የተጻፈውም ጽሕፈት፦ ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል። የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፥ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ፥ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ። በዚያ ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ። ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ፥ ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ።
ዳንኤል 5:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሥ ብልጣሶር በሺህ ለሚቈጠሩ መኳንንት ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ከእነርሱ ጋር የወይን ጠጅ እየጠጣ ነበር። የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ ብልጣሶር ሞቅ ባለው ጊዜ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጽዋዎችን እንዲያመጡ አገልጋዮቹን አዘዘ፤ ንጉሡ ይህን ያደረገው እርሱና መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹ በእነዚያ የወርቅ ጽዋዎች እንዲጠጡባቸው ፈልጎ ነው። አገልጋዮቹም እነዚያን ከኢየሩሳሌም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅና የብር ጽዋዎች ወዲያውኑ አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹ በእነዚህ ጽዋዎች የወይን ጠጅ ጠጡ። እየጠጡም ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክትንም አመሰገኑ። የሰው እጅ ጣቶች በድንገት ታይተው በቤተ መቅደሱ መቅረዝ ፊት ለፊት ባለው በተለሰነው የቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ መጻፍ ጀመሩ፤ እነዚያም ጣቶች በሚጽፉበት ጊዜ ንጉሡ አየ። ወዲያውኑ ፊቱ ገረጣ፤ ከድንጋጤውም ብዛት የተነሣ ጒልበቱ ተብረከረከ፤ የሰውነቱ መገጣጠሚያዎች ከዱት። አስማተኞችን፥ ጠንቋዮችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን እንዲያስገቡለት በከፍተኛ ድምፅ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ተጠርተው በመጡ ጊዜ ንጉሡ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጒሙን ሊነግረኝ የሚችል ሰው፥ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ይለብሳል፤ የወርቅ ኒሻንም ይደረግለታል፤ በመንግሥቴም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ ይይዛል” አለ። ጥበበኞቹም ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ነገር ግን ጽሑፉን ማንበብም ሆነ ትርጒሙን ለንጉሡ ማስረዳት የቻለ ከእነርሱ መካከል የተገኘ ማንም አልነበረም። ንጉሥ ብልጣሶር እጅግ ስለ ጨነቀው ፊቱ ይብሱን እየገረጣ ሄደ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቶአቸው የሚያደርጉትን አጡ። ቀድሞ ንግሥት የነበረችው የንጉሡ እናት የንጉሡንና የመኳንንቱን ሁካታ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ በመግባት እንዲህ አለች፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! በዚህ ጉዳይ ይህን ያኽል ልትጨነቅና ፊትህም ሊገረጣ አይገባም፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው በመንግሥትህ አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመነ መንግሥት እንደ አማልክት የሆነ ዕውቀት፥ ጥበብና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ ተገኝቶአል፤ በዚህም ምክንያት አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆር የጠንቋዮች፥ የአስማተኞች፥ የጠቢባንና የኮከብ ቈጣሪዎች ሁሉ አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር። እርሱ ሕልምን በመተርጐም፥ እንቆቅልሽን በመፍታትና የተሰወረውን ምሥጢር ገልጦ በማስረዳት ልዩ ችሎታ ያለው ጥበበኛና ብልኅ ሰው ነው፤ ስለዚህ ያንን አባትህ ናቡከደነፆር ‘ብልጣሶር’ ብሎ የሠየመውን ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱ ይህን ሁሉ ነገር ተርጒሞ ያስረዳሃል።” በዚያኑ ጊዜ ዳንኤል በንጉሡ ፊት ቀረበ፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፦ “አባቴ ንጉሥ ናቡከደነፆር ማርኮ ካመጣቸው ከይሁዳ ስደተኞች መካከል አንዱ የሆንክ ዳንኤል አንተ ነህን? የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ እንዳለና ብልኀት፥ ዕውቀትና ጥበብ የተሰጠህ መሆኑን ሰምቼአለሁ። እነሆ፥ ጠቢባን አማካሪዎቼና አስማተኞች ሁሉ ይህን ጽሕፈት አንብበው እንዲተረጒሙልኝ ተጠርተው ወደ እኔ መጥተው ነበር፤ ነገር ግን ተርጒመው ሊያስረዱኝ አልቻሉም፤ አንተ ግን የተሰወረውን ነገር የመተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር ሁሉ የመፍታት ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጒሙን ብትነግረኝ፥ ሐምራዊ መጐናጸፊያ እንድትለብስ፤ የወርቅ ኒሻን በአንገትህ እንድታደርግና በመንግሥቴም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ እንድትይዝ አደርጋለሁ።” ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ስጦታው ለአንተ ይሁን፤ ሽልማቱንም ለሌላ ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን አንብቤ ትርጒሙን እነግርሃለሁ። “ንጉሥ ሆይ! ልዑል እግዚአብሔር ለአባትህ ለናቡከደነፆር ንጉሥነትንና ታላቅነትን፥ ክብርንና ገናናነትን ሰጠው፤ ከገናናነቱም የተነሣ በልዩ ልዩ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ሁሉ በፊቱ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ ነበር፤ የፈለገውን መግደልና የፈለገውን ማዳን፥ የፈለገውን መሾምና ያልፈለገውን መሻር ይችል ነበር። ነገር ግን ትዕቢተኛ፥ እልኸኛና ጨካኝ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ክብሩንና ማዕርጉን ተገፎ ከዙፋኑ ወረደ፤ ከሕዝብ መካከል ተባረረ፤ አእምሮውም ተለውጦ እንደ እንስሳ ሆነ፤ እንደ በሬም ሣር እየበላ ከሜዳ አህዮች ጋር ሆኖ ለመኖር ተገደደ፤ መጠለያ አጥቶ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ፤ ይህም የሆነው ልዑል እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና መንግሥትን ሁሉ ለፈለገው መስጠት እንደሚችል እስከሚረዳበት ጊዜ ድረስ ነበር። “አንተም ብልጣሶር የእርሱ ልጅ በመሆንህ ይህን ሁሉ ስታውቅ ራስህን ዝቅ በማድረግ ትሕትና አላሳየህም። ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ ከቤተ መቅደሱ ተዘርፈው የመጡትን የወርቅ ዕቃዎች አስመጥተህ አንተና መኳንንቶችህ፥ ሚስቶችህና ቁባቶችህ የወይን ጠጅ መጠጫ አደረጋችኋቸው፤ ከጠጣችሁም በኋላ ማየት ወይም መስማት የማይችሉትንና ምንም ነገር የማያውቁትን ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገናችሁ፤ መግደል ወይም ማዳን የሚችለውንና አካሄድህን የሚቈጣጠረውን ሕያው አምላክ ግን አላከበርከውም። እንግዲህ እግዚአብሔር በሰው እጅ ጣቶች ልኮ እነዚህን ቃላት እንዲጽፉ ያደረገው ስለዚህ ነው። “የጽሑፉም ንባብ ‘ማኔ! ማኔ! ቴቄል! ኡፋርሲን’ የሚል ነው። ትርጒሙም የሚከተለው ነው፤ ማኔ ‘እግዚአብሔር የመንግሥትህን ዘመን ቈጥሮ እንዲፈጸም አደረገው’ ማለት ነው። ቴቄል ‘በሚዛን ተመዝነህ፥ ቀለህ ተገኘህ’ ማለት ነው፤ ፋርስ ‘መንግሥትህ ተከፍሎ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ’ ማለት ነው።” ከዚህም በኋላ ብልጣሶር ወዲያውኑ ዳንኤልን መጐናጸፊያ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ኒሻን በአንገቱ እንዲያደርጉለትና በመንግሥቱም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ እንዲይዝ እንዲያደርጉት በዐዋጅ አዘዘ። በዚያኑ ሌሊት የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ፤ በዚያን ጊዜ የስድሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስ መንግሥቱን ወረሰ።