የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 4:4-37

ዳንኤል 4:4-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደልቶኝ በቤተ መንግሥቴም ተመችቶኝ እኖር ነበር። አንድ ያስፈራኝ ሕልም አየሁ፤ በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ፣ ወደ አእምሮዬ የመጡት ምስሎችና ራእዮች አስደነገጡኝ። ስለዚህ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ መጥተው ሕልሜን እንዲተረጕሙልኝ አዘዝሁ። ጠንቋዮቹ፣ አስማተኞቹ፣ ኮከብ ቈጣሪዎቹና መተተኞቹ በመጡ ጊዜ ሕልሙን ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ሊተረጕሙልኝ አልቻሉም። በመጨረሻም በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል ገብቶ በፊቴ ቆመ፤ ሕልሜንም ነገርሁት። እኔም እንዲህ አልሁት፤ “የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ ዐውቃለሁ፤ ምንም ዐይነት ምስጢር አያስቸግርህም፤ ያየሁት ሕልም እነሆ፤ ተርጕምልኝ። በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ያየሁት ራእይ ይህ ነው፦ እነሆ በፊቴ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረዥም የሆነ ዛፍ ቆሞ ተመለከትሁ። ዛፉም እጅግ አደገ፤ ጠነከረም፤ ጫፉም ሰማይ ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር። ቅጠሎቹ ያማሩ፣ ፍሬዎቹ የተንዠረገጉ ነበሩ፤ በላዩም ለሁሉ የሚሆን ምግብ ነበረበት። የምድር አራዊት ከጥላው በታች ያርፉ ነበር፤ በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩ ነበር፤ ፍጥረትም ሁሉ ከርሱ ይመገብ ነበር። “በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየሁት ራእይ አንድ ቅዱስ መልእክተኛ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‘ዛፉን ቍረጡ፤ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ ከሥሩ ያሉት እንስሳት፣ በቅርንጫፎቹም ላይ ያሉት ወፎች ይሽሹ። ነገር ግን ጕቶውና ሥሩ በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ። “ ‘በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ በጥሻም ውስጥ ከአራዊት ጋራ ይኑር። አእምሮው ከሰው አእምሮ ይለወጥ፤ የእንስሳም አእምሮ ይሰጠው፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት። “ ‘ውሳኔው በመልእክተኞች ተገልጿል፤ ፍርዱም በቅዱሳኑ ተነግሯል፤ ይኸውም፣ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።’ “እኔ ናቡከደነፆር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፤ በመንግሥቴ ካሉ ጠቢባን ሁሉ አንዳቸውም ሊተረጕሙልኝ ስላልቻሉ፣ ምን ማለት እንደ ሆነ ንገረኝ። አንተ የአማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ልትተረጕምልኝ ትችላለህ።” ከዚያም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል ለጥቂት ጊዜ በጣም ታወከ፤ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም፣ “ብልጣሶር ሆይ፤ ሕልሙም ሆነ ትርጕሙ አያስደንግጥህ” አለው። ብልጣሶርም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ሕልሙ ለሚጠሉህ ይሁን፤ ትርጕሙም ለጠላቶችህ! እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣ ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጐጆ መሥሪያ ያለው፣ ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ! ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ። “ንጉሥ ሆይ፤ አንተ፣ ‘ዛፉን ቍረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጕቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ እንደ ዱር አራዊትም ይኑር፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት’ እያለ ከሰማይ የወረደውን ቅዱሱን መልእክተኛ አየህ። “ንጉሥ ሆይ፤ ትርጕሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤ ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋራ ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል። የዛፉ ጕቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለስልህ ያመለክታል። ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።” ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ከዐሥራ ሁለት ወራት በኋላ፣ ንጉሡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ ሳለ፣ “በብርቱ ኀይሌ፣ ለገናናው ክብሬ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” አለ። ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ፣ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፤ ስለ አንተ የታወጀው ይህ ነው፤ መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል፤ ከሕዝብ መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊት ጋራም ትኖራለህ፤ እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመት ያልፋል።” ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ከሕዝቡ መካከል ተሰደደ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ። የራስ ጠጕሩ እንደ ንስር ላባና፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ። ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ፣ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁት፤ ለዘላለምም የሚኖረውን ወደስሁት፤ ክብርንም ሰጠሁት። ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነው፤ መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይ ኀይላት፣ በምድርም ሕዝቦች ላይ፣ የወደደውን ያደርጋል፤ እጁን መከልከል የሚችል የለም፤ “ምን ታደርጋለህ?” ብሎ የሚጠይቀውም የለም። አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ፣ ወዲያው ለመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሱልኝ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቴ ፈለጉኝ፤ ወደ ዙፋኔም ተመለስሁ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንሁ። የሰማይ አምላክ የሚያደርገው ሁሉ ትክክል፣ መንገዶቹም ሁሉ ጽድቅ ስለ ሆኑ፣ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር እርሱን አወድሰዋለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ አከብረዋለሁም፤ እርሱም በትዕቢት የሚመላለሱትን ማዋረድ ይችላል።

ዳንኤል 4:4-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። ሕልም አለምሁ፥ እርስዋም አስፈራችኝ፥ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ፥ ስለዚህ የሕልሙን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ። የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፥ ሕልሙንም በፊታቸው ተናገርሁ፥ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም። በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፥ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት፦ የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ አውቄአለሁና ያለምሁትን የሕልሜን ራእይ ፍቺውንም ንገረኝ። የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረ፥ እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ። ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ። ቅጠሉም የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፥ ለሁሉም መብል ነበረበት፥ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር። በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ዛፉን ቍረጡ፥ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹንም አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ፥ አራዊትም ከበታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ። ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፥ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን። ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው፥ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት። ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው። እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ፥ አንተም፥ ብልጣሶር፥ ፍቺውን አስታውቀኝ፥ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ያስታውቁኝ ዘንድ አይችሉምና፥ ነገር ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ። የዚያን ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል አሰበ፥ ልቡም ታወከ። ንጉሡም መልሶ፦ ብልጣሶር ሆይ፥ ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ አለው። ብልጣሶርም መልሶ አለ፦ ጌታዬ ሆይ፥ ሕልሙ ለሚጠሉህ፥ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን። ትልቅ የነበረው የበረታውም ቁመቱም እስከ ሰማይ የደረሰው፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታየው፥ ቅጠሉም አምሮ የነበረው፥ ፍሬውም የበዛው፥ ለሁሉም መብል የነበረበት፥ በበታቹም የምድር አራዊት የተቀመጡ፥ በቅርንጫፎቹም የሰማይ ወፎች ያደሩበት ያየኸው ዛፍ፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፥ ታላቅነትህ በዝቶአል፥ እስከ ሰማይም ደርሶአል፥ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው። ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና፦ ዛፉን ቍረጡ፥ አጥፉትም፥ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተውት፥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቈይ፥ በሰማይም ጠል ይረስርስ፥ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፈንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ፍቺው ይህ ነው፥ በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፥ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል። ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፥ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመመጽወት አስቀር። ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ። ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር። ንጉሡም፦ ይህች እኔ በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ። ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና፦ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፦ መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፥ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው። በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፥ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፥ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፥ ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፥ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና። በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፥ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ እጁንም የሚከለክላት ወይም፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም። በዚያ ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፥ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፥ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፥ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፥ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ። አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።

ዳንኤል 4:4-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“እኔ ናቡከደነፆር በቤተ መንግሥቴ በብልጽግናና በምቾት እኖር ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለ የሚያስፈራ ሕልምና የሚያስደነግጥ ራእይ አየሁ። ስለዚህ የሕልሙን ትርጒም እንዲነግሩኝ በባቢሎን የሚገኙትን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ እንዲመጡ አደረግሁ። ጠንቋዮች፥ አስማተኞች፥ ኮከብ ቈጣሪዎችና መተተኞች ሁሉ ወደ እኔ በመጡ ጊዜ ሕልሜን ነገርኳቸው፤ እነርሱ ግን የሕልሜን ትርጒም ሊነግሩኝ አልቻሉም፤ ከዚህ በኋላ በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራው ዳንኤል ገባ፤ ይህ ሰው የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያደረበት ነው፤ እንዲህም ስል ሕልሜን ነገርኩት፤ ‘የጠቢባን አለቃ የሆንክ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ላይ ስላለ ምሥጢር ሁሉ ለአንተ ሰውር እንደማይሆን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፥ ያየሁትን ሕልም ልንገርህና ተርጒምልኝ።’ “በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለ አንድ ትልቅ ዛፍ በምድር መካከል በቅሎ በራእይ አየሁ። ይህም ዛፍ ጫፉ ወደ ሰማይ እስከሚደርስና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ሁሉ ሊያዩት እስከሚችሉ ድረስ አደገ ጠነከረም። የቅጠሎቹ ልምላሜ የሚያምር ሆነ፤ ፍሬው ሕዝብን ሁሉ ለመመገብ እስከሚበቃ በዛ፤ ጥላው ለአራዊት መጠለያ ሆነ፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጆ ሠርተው ሰፈሩ፤ ሕይወት ያላቸው ሁሉ ከፍሬው ይመገቡ ነበር። “በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ባየሁት ራእይ የሚጠብቅ አንድ ቅዱስ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ ተመለከትኩ። መልአኩም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ ‘ዛፉን ቊረጡ፤ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹን ሸምጥጡ፥ ፍሬውንም በትኑ፥ አራዊቱ ከጥላው ሥር፥ ወፎችም ከቅርንጫፎቹ ይሽሹ። ጒቶውን ግን ከብረትና ከነሐስ በተሠራ ሰንሰለት ዙሪያውን አስራችሁ በመሬት ውስጥ ተዉት፤ በለምለም ሣር መካከል እንዳለ በሜዳው ላይ እንዲቀር አድርጉት። “ ‘በሰማይም ጠል ይረስርስ፤ በመስክ ከአራዊት ጋር ሣር እየበላ ይኑር። ሰብአዊ አእምሮው ተለውጦ፥ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በእንስሳ አእምሮ ይኑር። ውሳኔውም የተላለፈው በቅዱሳን መላእክት ነው፤ ይህም የሆነው ልዑል እግዚአብሔር በምድር መንግሥታት ላይ ሥልጣን ያለው መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅ ነው፤ ሥልጣኑንም ለፈቀደለት ሰው ይሰጠዋል፤ የተናቁትንም በሥልጣን ላይ ያስቀምጣቸዋል።’ “እንግዲህ እኔ ንጉሥ ናቡከደነፆር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አንተም ብልጣሶር ሆይ! ትርጒሙን ንገረኝ፤ በመንግሥቴ ያሉት ጠቢባን ትርጒሙን ሊነግሩኝ አይችሉም፤ አንተ ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ላይ ስላለ ልትነግረኝ ትችላለህ።” በዚያን ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል እጅግ ከመደንገጡና በሐሳብ ከመታወኩ የተነሣ ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ፤ ንጉሡም “ብልጣሶር ሆይ! ሕልሙም ሆነ ትርጒሙ አያስጨንቅህ” አለው። ብልጣሶርም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ሕልሙም ሆነ ትርጒሙ ለአንተ መሆኑ ቀርቶ ለጠላቶችህ ቢሆን በወደድሁ ነበር። እነሆ፥ ጫፉ እስከ ሰማይ የደረሰና በዓለም ዙሪያ ላሉት ሰዎች ሁሉ የሚታይ አንድ ትልቅ ዛፍ በራእይ ተመልክተሃል፤ የዚህ ዛፍ ቅጠሎች ልምላሜ የሚያምር ነበር፤ ሁሉንም ሕዝብ ለመመገብ የሚበቃ ብዙ ፍሬ ነበረው፤ አራዊት በጥላው ሥር መጠለያ አግኝተው፥ ወፎችም በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ይኖሩ ነበር። “ንጉሥ ሆይ! ረጅምና ብርቱ የሆነው ያ ዛፍ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎአል፤ ሥልጣንህም በዓለም ሁሉ ላይ ተንሰራፍቶአል። ንጉሥ ሆይ! አንተ እየተመለከትከው አንድ የሚጠብቅ ቅዱስ ከሰማይ ወርዶ እንዲህ አለ፦ ‘ዛፉን ቈርጣችሁ አጥፉ፤ ጒቶውን ግን ከብረትና ከነሐስ በተሠራ ሰንሰለት ዙሪያውን አስራችሁ በምድር ውስጥ ተዉት፤ በመስኩ ላይ በሣር መካከል ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፤ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ኑሮው ከዱር አራዊት ጋር ይሁን።’ “ንጉሥ ሆይ! እነሆ፥ ትርጒሙ ይህ ነው፤ ልዑል እግዚአብሔር በአንተ በጌታዬ በንጉሡ ላይ እንዲፈጸም የወሰነው ነገር የሚከተለው ነው፤ ከሕዝብ መካከል ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ኑሮህም ከዱር አራዊት ጋር ይሆናል፤ ሰባት ዓመት እስኪያልፍ እንደ በሬ ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠል ትረሰርሳለህ፤ ይህም ሁሉ የሚደርስብህ ልዑል እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና መንግሥትንም ሁሉ ለወደደው ሰው እንደሚሰጥ እስከምትረዳ ድረስ ነው። ጉቶው በመሬት ውስጥ እንዲቀር ትእዛዝ መሰጠቱ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ካወቅህ በኋላ እንደገና ተመልሰህ የምትነግሥ መሆንህን ያመለክታል፤ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! በበኩሌ የምመክርህን ስማ፤ ኃጢአት መሥራትን ትተህ መልካም ሥራ መሥራትን አዘወትር፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑ ሰዎች ራራላቸው፤ ይህን ብታደርግ በሰላም የመኖር ዕድሜህ ይረዝምልህ ይሆናል።” ይህ ሁሉ ነገር በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ። ከዐሥራ ሁለት ወራት በኋላ ንጉሡ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር፤ ንጉሡም እንዲህ አለ፦ “ይህችን ታላቋን ባቢሎን የነገሥታት መኖሪያና ዋና ከተማ ሆና የእኔ ክብርና ግርማ እንዲገለጥባት በሥልጣኔ የሠራኋት እኔ አይደለሁምን?” ንግግሩን ገና ሳይጨርስ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ! የተላለፈብህን ውሳኔ ስማ! እነሆ፥ መንግሥትህ ከአንተ ተወስዳለች፤ ከሕዝብ መካከል ተባረህ መኖሪያህ ከዱር አራዊት ጋር ይሆናል፤ ሰባት ዓመት እስኪያልፍ እንደ በሬ ሣር ትበላለህ፤ ይህም የሚሆነው ልዑል እግዚአብሔር በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና መንግሥትንም ሁሉ ለወደደው ሰው እንደሚሰጥ እስክትገነዘብ ድረስ ነው።” ፍርዱም ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ ተፈጸመ፤ ስለዚህም ከሕዝብ መካከል ተባረረ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ ከሰማይም በወረደ ጠል ሰውነቱ ረሰረሰ፤ ጠጒሩ እንደ ንስር ላባ አደገ፤ ጥፍሩም እንደ አሞራ ጥፍር ሆነ። ንጉሡ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፦ “ሰባቱ ዓመቶች ካለፉ በኋላ ቀና ብዬ ወደ ሰማይ ተመለከትኩ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፤ ለዘለዓለማዊው አምላክ ክብርና ውዳሴ አቀረብኩ፤ “ግዛቱ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ዘንድ ኢምንት ናቸው፤ በሰማይ መላእክትም ሆነ በምድር በሚኖሩ ሕዝቦች ላይ የፈቀደውን ያደርጋል፤ ፈቃዱን እንዳያደርግ ሊከለክለው የሚችል ወይም ‘ምን እያደረግህ ነው’ የሚለው ማንም የለም። “አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ ወዲያውኑ የመንግሥቴ ክብርና ግርማ ማዕርጉም ሁሉ እንደገና ተሰጠኝ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቴ በደስታ ተቀበሉኝ፤ ከቀድሞው የበለጠ ክብር ተጨምሮልኝ በንጉሥነቴ ጸናሁ። “እነሆ፥ እኔ ናቡከደነፆር ለሰማይ ንጉሥ ምስጋና፥ ክብርና ውዳሴ አቀርባለሁ፤ እርሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ነው፤ መንገዱም ፍትሓዊ ነው፤ በትዕቢት የሚመሩትንም ሁሉ ማዋረድ ይችላል።”