ዳንኤል 3:24-30
ዳንኤል 3:24-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር በአድናቆት ከተቀመጠበት ዘልሎ በመነሣት አማካሪዎቹን “አስረን በእሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ እውነት ነው” አሉ። እርሱም፣ “እነሆ፤ ያልታሰሩና ያልተጐዱ አራት ሰዎች በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አላቸው። ናቡከደነፆርም ወደሚነድደው የእቶን እሳት በር ቀረብ ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ፤ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!” አላቸው። ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ወጡ፤ መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹና የቤተ መንግሥት አማካሪዎችም በዙሪያቸው ተሰበሰቡ፤ እነርሱም እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳ፣ ከራሳቸውም ጠጕር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፤ የመጐናጸፊያቸው መልክ አልተለወጠም፤ የእሳትም ሽታ በላያቸው አልነበረም። ከዚያም ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፤ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና። ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።” ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ላይ ሾማቸው።
ዳንኤል 3:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፥ አማካሪዎቹንም፦ ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፥ ምንም አላቈሰላቸውም፥ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ፦ እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ። ናቡከደነፆርም መልሶ፦ መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ። እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ። የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።
ዳንኤል 3:24-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚያን በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር በመደነቅ ፈጥኖ ተነሣና “አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን?” ሲል አማካሪዎቹን ጠየቀ። እነርሱም “አዎ፥ ንጉሥ ሆይ!” አሉት። ንጉሡም “እነሆ፥ እኔ እሳቱ ምንም ሳይጐዳቸው ከእስራት ተፈተው በነበልባሉ ውስጥ የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አለ። ናቡከደነፆር ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ተጠግቶ “የልዑል አምላክ አገልጋዮች የሆናችሁ እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ! ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” በማለት ተጣራ፤ እነርሱም ከእሳቱ ወጡ። ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹ፥ መኳንንቱ፥ አማካሪዎቹ ሁሉ በእነርሱ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳው፥ ከራስ ጠጒራቸውም አንዲቱን እንኳ እንዳላቃጠለ፥ የመጐናጸፊያቸው መልክ እንዳልተለወጠና ሌላው ቀርቶ የእሳቱ ሽታ እንኳ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፦ “የሲድራቅ፥ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! እርሱ መልአኩን ልኮ እነዚህን አገልጋዮቹን አድኖአል፤ እነርሱ በአምላካቸው ተማምነው ለእርሱ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት አንሰግድም በማለት የንጉሡን ትእዛዝ በማፍረስ ሕይወታቸውን በአደጋ ላይ ጥለውት ነበር። “እንደዚህ የሚታደግ ሌላ አምላክ የለም፤ ስለዚህ በአገሮች ሁሉ በሚኖሩና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን በሚናገሩ ሕዝቦች ሁሉ መካከል በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር ሰውነቱ ተቈራርጦ እንዲጣልና ቤቱም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆን ዐውጃለሁ።” ይህንንም ካወጀ በኋላ ንጉሡ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን ግዛት ከፍ ከፍ አድርጎ ሾማቸው።