ዳንኤል 3:16-23
ዳንኤል 3:16-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጕዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድድ አዘዘ። ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ። እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ነበረና የእቶኑም እሳት እጅግ ስለ ነደደ፣ የእሳቱ ወላፈን ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ወስደው የጣሏቸውን ወታደሮች ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ግን ተጠፍረው እንደ ታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።
ዳንኤል 3:16-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናብከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፥ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፥ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብድናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ። የዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸውም ከቀረውም ልብሳቸው ጋር ታስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው። እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብድናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት ውስጥ ወደቁ።
ዳንኤል 3:16-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ ጉዳይ ላይ ራሳችንን የምንከላከልበት መልስ ልንሰጥህ አያስፈልገንም። እኛ የምናገለግለው አምላክ ከዚህ ከሚነደው ከእሳት ነበልባልም ሆነ ከአንተ እጅ ሊያድነን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱ ሊያድነን ፈቃዱ ባይሆን እንኳ አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምከውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ ላይ እጅግ ተቈጥቶ መልኩ ተለዋወጠ፤ ስለዚህ እሳቱ ከቀድሞው ይበልጥ በሰባት እጥፍ ከፍ ብሎ እንዲነድ ትእዛዝ ሰጠ። ሦስቱንም ሰዎች አስረው ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ይጥሉአቸው ዘንድ ከሠራዊቱ መካከል ብርቱ የሆኑትን አዘዘ። ስለዚህ ቀሚሳቸው፥ ሱሪያቸውና መጠምጠሚያቸው ሳይቀር ሙሉ ልብሳቸውን እንደ ለበሱ አስረው ወደሚነደው ወደ የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው። ንጉሡ በሰጠው ጥብቅ ትእዛዝ መሠረት እሳቱ በኀይል ተቀጣጥሎ ይነድ ስለ ነበር ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን ወደ እሳቱ የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን አቃጥሎ ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ግን በጥብቅ እንደ ታሰሩ በእሳቱ ነበልባል ላይ ወደቁ።