ዳንኤል 3:13-18
ዳንኤል 3:13-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤ ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው? አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእንቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?” ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጕዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”
ዳንኤል 3:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። ናቡከደነፆርም፦ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፥ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፥ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናብከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፥ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።
ዳንኤል 3:13-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም መጥተው በንጉሡ ፊት ቀረቡ። ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ! አማልክቴን አለማምለካችሁና ላቆምኩትም የወርቅ ምስል አለመስገዳችሁ እርግጥ ነውን? እንግዲህ የመለከት፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆ፥ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንትና፥ የሙዚቃም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ላቆምኩት ምስል በመሬት ላይ ተደፍታችሁ ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ወዲያውኑ ትጣላላችሁ፤ ከእጄም የሚያድናችሁ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ።” ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ ጉዳይ ላይ ራሳችንን የምንከላከልበት መልስ ልንሰጥህ አያስፈልገንም። እኛ የምናገለግለው አምላክ ከዚህ ከሚነደው ከእሳት ነበልባልም ሆነ ከአንተ እጅ ሊያድነን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱ ሊያድነን ፈቃዱ ባይሆን እንኳ አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምከውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”