ዳንኤል 3:1-30
ዳንኤል 3:1-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጉሡ ናቡከደነፆር ከፍታው ስድሳ ክንድ፣ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። ከዚያም መኳንንትን፣ ሹማምትን፣ አገረ ገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችንና በየአውራጃው ያሉትን ሹማምት ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል እንዲመጡ ጠራ። መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችና በየአውራጃው ያሉ ሹማምት ሁሉ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል ተሰበሰቡ፤ በምስሉም ፊት ቆሙ። ከዚያም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ታወጀ፤ “ሕዝቦች ሆይ፤ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤ ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።” ስለዚህ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው ሰገዱ። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቈጣሪዎች ወደ ፊት ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፤ ንጉሥ ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፤ አንተ እንዲህ ብለህ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ድምፅ የሰማ ሁሉ ለወርቁ ምስል ተደፍቶ መስገድ አለበት፤ ማንም ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ባይሰግድ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያገለግሉም፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።” ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤ ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው? አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእንቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?” ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጕዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድድ አዘዘ። ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ። እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ነበረና የእቶኑም እሳት እጅግ ስለ ነደደ፣ የእሳቱ ወላፈን ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ወስደው የጣሏቸውን ወታደሮች ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ግን ተጠፍረው እንደ ታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር በአድናቆት ከተቀመጠበት ዘልሎ በመነሣት አማካሪዎቹን “አስረን በእሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ እውነት ነው” አሉ። እርሱም፣ “እነሆ፤ ያልታሰሩና ያልተጐዱ አራት ሰዎች በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አላቸው። ናቡከደነፆርም ወደሚነድደው የእቶን እሳት በር ቀረብ ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ፤ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!” አላቸው። ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ወጡ፤ መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹና የቤተ መንግሥት አማካሪዎችም በዙሪያቸው ተሰበሰቡ፤ እነርሱም እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳ፣ ከራሳቸውም ጠጕር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፤ የመጐናጸፊያቸው መልክ አልተለወጠም፤ የእሳትም ሽታ በላያቸው አልነበረም። ከዚያም ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፤ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና። ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።” ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ላይ ሾማቸው።
ዳንኤል 3:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፥ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንንትና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ። በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምቶቹ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፥ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ። አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል። ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል። ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የተናገሩ ሁሉ ተደፉ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ። በዚያን ጊዜም ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ። ለንጉሡም ለናቡከደነፆር ተናገሩ እንዲህም አሉ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፦ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፥ ተደፍቶም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ። በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፥ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፥ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም። ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። ናቡከደነፆርም፦ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፥ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፥ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናብከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፥ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፥ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብድናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ። የዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸውም ከቀረውም ልብሳቸው ጋር ታስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው። እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብድናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት ውስጥ ወደቁ። የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፥ አማካሪዎቹንም፦ ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፥ ምንም አላቈሰላቸውም፥ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ፦ እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ። ናቡከደነፆርም መልሶ፦ መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ። እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ። የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።
ዳንኤል 3:1-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሥ ናቡከደነፆር ቁመቱ ሥልሳ ክንድ፥ ወርዱ ስድስት ክንድ የሚያኽል ምስል ከወርቅ አሠራ፤ በባቢሎንም ግዛት በዱራ ሜዳ ላይ አቆመው። የቆመው ምስል በሚመረቅበት ክብረ በዓል ላይ እንዲገኙ አገረ ገዢዎችን መኳንንትን፥ ሹማምንትን፥ አማካሪዎችን፥ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፥ ዳኞችን፥ ሌሎችንም የየክፍለ ሀገሩ ባለሥልጣኖችን አስጠራ። እነዚህ ሁሉ ባለሥልጣኖች ለምረቃው በዓል በአንድነት ተሰብስበው በምስሉ ፊት ለፊት ቆሙ፤ በዚያን ጊዜ አንድ ዐዋጅ ነጋሪ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ከልዩ ልዩ ሀገር የመጣችሁ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ነገዶች ሆይ! የመለከት የእንቢልታ የመሰንቆ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንት፥ የሙዚቃ ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል እንድትሰግዱ ታዛችኋል። በምድር ላይ ተደፍቶ የማይሰግድ ሰው ቢኖር በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ ወዲያውኑ ይጣላል።” ስለዚህ ወገኖች፥ ከልዩ ልዩ ሀገር የመጡ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ሁሉ የመለከትና፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆና፥ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንትና የሙዚቃ ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ በመሬት ላይ ተደፍተው ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ። በዚያን ጊዜ አንዳንድ የባቢሎን ጠቢባን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ። ንጉሡን ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! ንጉሥ ሆይ! አንተ የመለከት፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆ፥ የክራር፥ የበገናና የዋሽንት፥ የሙዚቃ ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ማናቸውም ሰው በመሬት ላይ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል እንዲሰግድ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር። በመሬት ላይ ተደፍቶ የማይሰግድ ሰው ቢኖር በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ ሰጥተሃል። እነሆ፥ በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ገዢዎች አድርገህ የሾምካቸው ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ የአይሁድ ወገኖች የአንተን ትእዛዝ አይፈጽሙም፤ አማልክትህን አያመልኩም፤ ላቆምከውም ምስል አይሰግዱም።” ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም መጥተው በንጉሡ ፊት ቀረቡ። ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ! አማልክቴን አለማምለካችሁና ላቆምኩትም የወርቅ ምስል አለመስገዳችሁ እርግጥ ነውን? እንግዲህ የመለከት፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆ፥ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንትና፥ የሙዚቃም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ላቆምኩት ምስል በመሬት ላይ ተደፍታችሁ ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ወዲያውኑ ትጣላላችሁ፤ ከእጄም የሚያድናችሁ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ።” ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ ጉዳይ ላይ ራሳችንን የምንከላከልበት መልስ ልንሰጥህ አያስፈልገንም። እኛ የምናገለግለው አምላክ ከዚህ ከሚነደው ከእሳት ነበልባልም ሆነ ከአንተ እጅ ሊያድነን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱ ሊያድነን ፈቃዱ ባይሆን እንኳ አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምከውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ ላይ እጅግ ተቈጥቶ መልኩ ተለዋወጠ፤ ስለዚህ እሳቱ ከቀድሞው ይበልጥ በሰባት እጥፍ ከፍ ብሎ እንዲነድ ትእዛዝ ሰጠ። ሦስቱንም ሰዎች አስረው ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ይጥሉአቸው ዘንድ ከሠራዊቱ መካከል ብርቱ የሆኑትን አዘዘ። ስለዚህ ቀሚሳቸው፥ ሱሪያቸውና መጠምጠሚያቸው ሳይቀር ሙሉ ልብሳቸውን እንደ ለበሱ አስረው ወደሚነደው ወደ የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው። ንጉሡ በሰጠው ጥብቅ ትእዛዝ መሠረት እሳቱ በኀይል ተቀጣጥሎ ይነድ ስለ ነበር ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን ወደ እሳቱ የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን አቃጥሎ ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ግን በጥብቅ እንደ ታሰሩ በእሳቱ ነበልባል ላይ ወደቁ። ከዚያን በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር በመደነቅ ፈጥኖ ተነሣና “አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን?” ሲል አማካሪዎቹን ጠየቀ። እነርሱም “አዎ፥ ንጉሥ ሆይ!” አሉት። ንጉሡም “እነሆ፥ እኔ እሳቱ ምንም ሳይጐዳቸው ከእስራት ተፈተው በነበልባሉ ውስጥ የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አለ። ናቡከደነፆር ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ተጠግቶ “የልዑል አምላክ አገልጋዮች የሆናችሁ እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ! ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” በማለት ተጣራ፤ እነርሱም ከእሳቱ ወጡ። ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹ፥ መኳንንቱ፥ አማካሪዎቹ ሁሉ በእነርሱ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳው፥ ከራስ ጠጒራቸውም አንዲቱን እንኳ እንዳላቃጠለ፥ የመጐናጸፊያቸው መልክ እንዳልተለወጠና ሌላው ቀርቶ የእሳቱ ሽታ እንኳ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፦ “የሲድራቅ፥ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! እርሱ መልአኩን ልኮ እነዚህን አገልጋዮቹን አድኖአል፤ እነርሱ በአምላካቸው ተማምነው ለእርሱ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት አንሰግድም በማለት የንጉሡን ትእዛዝ በማፍረስ ሕይወታቸውን በአደጋ ላይ ጥለውት ነበር። “እንደዚህ የሚታደግ ሌላ አምላክ የለም፤ ስለዚህ በአገሮች ሁሉ በሚኖሩና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን በሚናገሩ ሕዝቦች ሁሉ መካከል በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር ሰውነቱ ተቈራርጦ እንዲጣልና ቤቱም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆን ዐውጃለሁ።” ይህንንም ካወጀ በኋላ ንጉሡ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን ግዛት ከፍ ከፍ አድርጎ ሾማቸው።