ዳንኤል 2:1-9

ዳንኤል 2:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም ዐለመ፤ መንፈሱ ታወከ፤ እንቅልፍም ከርሱ ራቀ። ያለመውንም ሕልም እንዲነግሩት ንጉሡ ጠንቋዮችን፣ አስማተኞችን፣ መተተኞችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በፊቱ ቆሙ፤ ንጉሡም፣ “አንድ ሕልም ዐለምሁ፤ ሕልሙም ምን እንደ ሆነ ለማወቅ መንፈሴ ተጨንቋል” አላቸው። ከዚያም ኮከብ ቈጣሪዎቹ ለንጉሡ በአራማይክ ቋንቋ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ሕልምህን ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም እንፈታልሃለን” አሉት። ንጉሡም ለኮከብ ቈጣሪዎቹ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕልሙንና ትርጕሙን ባትነግሩኝ አካላችሁ እንዲቈራረጥና ቤቶቻችሁም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆኑ ወስኛለሁ፤ ነገር ግን ሕልሙንና ትርጕሙን ብትነግሩኝ፣ ስጦታና ሽልማት፣ ታላቅ ክብርም ከእኔ ትቀበላላችሁ፤ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጕሙንም አሳውቁኝ።” እነርሱም እንደ ገና፣ “ንጉሥ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም እንተረጕመዋለን” ብለው መለሱ። ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ምን ብዬ እንደ ወሰንሁ ስለምታውቁ፣ ጊዜ ለማራዘም እንደምትሞክሩ ተረድቻለሁ፤ ሕልሙን ባትነግሩኝ፣ አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ሁኔታው ይለወጣል ብላችሁ በማሰብ የሚያሳስቱ ነገሮችንና ክፉ ሐሳቦችን ልትነግሩኝ አሲራችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጕሙንም ልትነግሩኝ እንደምትችሉ በዚህ ዐውቃለሁ።”

ዳንኤል 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፥ መንፈሱም ታወከ፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፥ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ። ንጉሡም፦ ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኮአል አላቸው። ከለዳውያኑም ንጉሡን በሶርያ ቋንቋ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፥ ለባሪያዎችህ ሕልምህን ንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳይሃለን ብለው ተናገሩት። ንጉሡም መለሰ ከለዳውያኑንም፦ ነገሩ ከእኔ ዘንድ ርቆአል፥ ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፥ ትቈረጣላችሁ ቤቶቻችሁም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ። ሕልሙንና ፍቺውን ግን ብታሳዩ፥ ከእኔ ዘንድ ስጦታና ዋጋ ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ፥ ስለዚህም ሕልሙንና ፍቺውን አሳዩኝ አላቸው። ሁለተኛም ጊዜ መልሰው፦ ንጉሡ ለባሪያዎቹ ሕልሙን ይንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳያለን አሉት። ንጉሡ መልሶ፦ ነገሩ ከእኔ ዘንድ እንደ ራቀ ታውቃላችሁና ጊዜውን እንድታስረዝሙ እኔ አውቃለሁ። ሕልሙንም ባታስታውቁኝ አንድ ፍርድ አለባችሁ፥ ጊዜውን ለማሳለፍ የሐሰትንና የተንኰልን ቃል ልትነግሩኝ አዘጋጅታችኋል፥ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፥ ፍቺውንም ማሳየት እንድትችሉ አውቃለሁ አለ።

ዳንኤል 2:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አየ፤ በጣምም ስለ ተጨነቀ እንቅልፍ አጣ። ስለዚህ ወደ እርሱ መጥተው ያየውን ሕልም ይነግሩት ዘንድ ጠንቋዮች፥ አስማተኞች፥ መተተኞችና የከለዳውያን ኮከብ ቈጣሪዎች እንዲጠሩ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነርሱም መጥተው በፊቱ ቆሙ፤ ንጉሡም “ሕልም አይቼ ስለ ነበር ያ ሕልም ምን እንደ ሆነ እስካውቀው ድረስ እጅግ ተጨንቄአለሁ” አላቸው። እነርሱም “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር! ሕልምህ ምን እንደ ሆነ ንገረንና ትርጒሙን እናስረዳሃለን” ሲሉ በሶርያ ቋንቋ መለሱለት። ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “መጀመሪያ ሕልሜን፥ ቀጥሎም ትርጒሙን ንገሩኝ፤ አለበለዚያ ግን እጅና እግራችሁ እንዲቈራረጥና ቤታችሁ የፍርስራሽ ክምር እንዲሆን ወስኛለሁ። ሕልሙን ከነትርጒሙ ልትነግሩኝ ብትችሉ ግን ሽልማትና ስጦታ ከታላቅ ክብር ጋር እንድታገኙ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ ሕልሙን ከነትርጒሙ ንገሩኝ።” እነርሱም እንደገና “ንጉሥ ሆይ! ሕልምህ ምን እንደ ሆነ ለእኛ ለአገልጋዮችህ ንገረንና እኛም ትርጒሙን እንንገርህ” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የወሰንኩትን ጥብቅ ውሳኔ ስላወቃችሁ የእናንተ ዕቅድ ነገሩን ለማዘግየት መሆኑን ተረድቼአለሁ፤ ሕልሙን ልትነግሩኝ ባትችሉ ለሁላችሁም አንድ ዐይነት ቅጣት ተዘጋጅቶአል፤ ሁኔታዎች የሚለወጡ መስሎአችሁ የሐሰትና የተንኰል ቃል በመናገር ጊዜ ማራዘም ፈልጋችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ብትነግሩኝ ፍቹም እንደማያስቸግራችሁ ዐውቃለሁ።”