የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 10:10-21

ዳንኤል 10:10-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እነሆም፣ አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤ እየተንቀጠቀጥሁም በእጄና በጕልበቴ አቆመኝ፤ እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ወዳንተ ተልኬአለሁና፣ የምነግርህን አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም” አለኝ። ይህን ሲለኝም፣ እየተንቀጠቀጥሁ ተነሥቼ ቆምሁ። ደግሞም እንዲህ አለኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አትፍራ፣ ማስተዋልን ለማግኘትና በአምላክህም ፊት ራስህን ለማዋረድ ከወሰንህበት ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም የቃልህን መልስ ይዤ መጥቻለሁ። ነገር ግን የፋርስ መንግሥት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም በዚያ ከፋርስ ንጉሥ ጋር ተውሁት። ራእዩ ሊፈጸም ገና ብዙ ዘመን ስለሚቀረው፣ ወደ ፊት በሕዝብህ ላይ የሚሆነውን ልገልጽልህ አሁን ወደ አንተ መጥቻለሁ።” ይህን እየተናገረኝ ሳለ፣ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፤ የምናገረውንም ዐጣሁ። ከዚያም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እኔም አፌን ከፈትሁ፤ መናገርም ጀመርሁ፤ በፊቴ የነበረውንም እንዲህ አልሁት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ከራእዩ የተነሣ ተሠቃይቻለሁ፤ ኀይልም ዐጣሁ። ጌታዬ ሆይ፤ ጕልበቴ ከዳኝ፤ መተንፈስም አቅቶኛል፤ እኔ አገልጋይህ ከአንተ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ?” እንደ ገናም፣ ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም። እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና” አለኝ። እየተናገረኝም ሳለ፣ በረታሁና፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አበርትተኸኛልና ተናገር” አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ለምን ወደ አንተ እንደ መጣሁ ታውቃለህ? የፋርስን አለቃ ለመውጋት በቶሎ እመለሳለሁ፤ እኔም ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል። አስቀድሜ ግን በእውነት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ ከእነዚህ አለቆች ጋር ለመዋጋት ከአለቃችሁ ከሚካኤል በስተቀር የሚረዳኝ የለም።”

ዳንኤል 10:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ። እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፥ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፥ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፥ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፥ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት። ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፥ ዲዳም ሆንሁ። እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፥ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ በፊቴም ቆሞ የነበረውን፦ ጌታዬ ሆይ፥ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት። ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፥ አበረታኝም። እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፥ አትፍራ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን፥ በርታ፥ ጽና አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና፦ አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም ከፋርስ አለቃ ጋር እዋጋ ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም ስወጣ፥ እነሆ፥ የግሪክ አለቃ ይመጣል። ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም።

ዳንኤል 10:10-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚያ በኋላ አንዳች እጅ ዳሰሰኝ፤ ገና እየተንቀጠቀጥኩ ስለ ነበር ደግፎ በእጄና በጒልበቴ እንድቆም አደረገኝ። መልአኩም “በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደድክ ዳንኤል ሆይ! እነሆ፥ እኔ ወደ አንተ ተልኬ መጥቼአለሁ፤ ባለህበት ቀጥ ብለህ ቁም፤ የምነግርህንም በጥንቃቄ አስተውል!” አለኝ። ይህን በነገረኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥኩ ቆምኩ። ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ! አትፍራ! ማስተዋልን ለማግኘት ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ለማዋረድ ከወሰንክበት ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ እኔም ተልኬ ወደ አንተ የመጣሁት ጸሎትህ መልስ ከማግኘቱ የተነሣ ነው። የፋርስ መንግሥት አለቃ የሆነው መንፈስ ኻያ አንድ ቀን ሙሉ ተቃወመኝ፤ በፋርስ ብቸኛ መሆኔን አይቶ ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ። እኔም የመጣሁት በወገኖችህ ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚደርስባቸውን ነገር ላስረዳህ ነው፤ ስለዚህ ከዚህም በቀር ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚገልጥ ሌላ ራእይ አለ።” ይህንንም በነገረኝ ጊዜ የምናገረውን አጥቼ ወደ መሬት አቀርቅሬ መናገር አቃተኝ። ከዚህ በኋላ ሰውን የሚመስለው እጁን ዘርግቶ ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እኔም እንዲህ አልኩት፦ “ጌታዬ ሆይ! ይህ ራእይ በጣም ስላሳመመኝ ሰውነቴ ዛለ። እኔ አገልጋይህ ስሆን ከአንተ ከጌታዬ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ? መተንፈስ እስከሚያቅተኝ ድረስ እጅግ ደክሜአለሁ።” ያ ሰው የሚመስለው መልአክ እንደገና በዳሰሰኝ ጊዜ ብርታት አገኘሁ። እርሱም “አንተ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደድክ ሰው ሆይ! መልካም ይሆንልሃል፤ አትፍራ! አይዞህ በርታ!” አለኝ። እርሱም በተናገረኝ ጊዜ ብርታት አገኘሁና “ጌታዬ ሆይ፥ ብርታት ስለ ሰጠኸኝ እነሆ፥ ተናገር” አልኩት። እንደገናም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደ ሆነ ታውቃለህን? እኔ ወደ አንተ የመጣሁት በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን ልገልጥልህ ነው፤ አሁንም ተመልሼ የፋርስ መንግሥት አለቃ ከሆነው መንፈስ ጋር ጦርነት አደርጋለሁ፤ እኔ ከሄድኩ በኋላ የግሪክ መንግሥት አለቃ የሆነው መንፈስ ይመጣል፤ ይሁን እንጂ የእስራኤል ጠባቂ መልአክ ከሆነው ከሚካኤል በቀር እኔን የሚረዳ የለም።