ዳንኤል 1:8-17
ዳንኤል 1:8-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳንኤል ግን በንጉሡ ምግብና የወይን ጠጅ እንዳይረክስ ወሰነ፤ በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ፈቃድ ጠየቀው። እግዚአብሔርም ለዳንኤል በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ሞገስንና መወደድን ሰጠው። ሆኖም የጃንደረቦቹ አለቃ ለዳንኤል፣ “መብሉንና መጠጡን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ብትታዩ፣ በንጉሡ ዘንድ በራሴ ላይ አደጋ ታስከትሉብኛላችሁ።” ብሎ ነገረው። ዳንኤልም የጃንደረቦቹን አለቃ በዳንኤል፣ በአናንያ፣ በሚሳኤልና በአዛርያስ ላይ የሾመውን መጋቢ እንዲህ አለው፤ “እባክህ አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ ለመብል ከአትክልት፣ ለመጠጥም ከውሃ በስተቀር ምንም አይሰጠን፤ ከዚያም የእኛን መልክና የንጉሡን መብል የሚበሉትን ወጣቶች መልክ አስተያይ፤ በአገልጋዮችህ ላይ የወደድኸውን አድርግብን።” እርሱም በዚህ ነገር ተስማማ፤ ለዐሥር ቀንም ፈተናቸው። ከዐሥር ቀን በኋላም የንጉሡን መብል ከበሉት ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ጤናማዎችና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ተገኙ። ስለዚህ መጋቢው ምርጥ የሆነውን ምግባቸውንና ሊጠጡት የሚገባውን የወይን ጠጅ አስቀርቶ በምትኩ አትክልት ሰጣቸው። እግዚአብሔር ለእነዚህ አራት ወጣቶች በማንኛውም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ማንኛውንም ራእይና ሕልም የመረዳት ችሎታ ነበረው።
ዳንኤል 1:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ፥ እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነ። እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። የጃንደረቦቹም አለቃ ዳንኤልን፦ መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፥ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ፥ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ አለው። ዳንኤልም የጃንደርቦቹ አለቃ በዳንኤልና በአናንያ በሚሳኤልና በአዛርያ ላይ የሾመውን ሜልዳርን፦ እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ፥ የምንበላውንም ጥራጥሬ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፥ ከዚያም በኋላ የእኛን ፊትና ከንጉሡ መብል የሚበሉትን የብላቴኖችን ፊት ተመልከት፥ እንዳየኸውም ሁሉ ከባሪያዎችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ አለው። ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው። ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ። ሜልዳርም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው። ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፥ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ።
ዳንኤል 1:8-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዳንኤል ከንጉሡ ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሱን ላለማርከስ ወሰነ፤ በዚህም ሐሳብ እንዲስማማለት አሽፈናዝን ለመነው። እግዚአብሔርም ለዳንኤል በሹሙ ፊት ሞገስን ሰጥቶ ልቡን አራራለት። ይሁን እንጂ ንጉሡን ስለ ፈራ አሽፈናዝ ዳንኤልን “ምግባችሁንና መጠጣችሁን ያዘዘ ንጉሡ ራሱ ነው፤ እናንተ ከሌሎቹ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁና ተጐሳቊላችሁ ብትገኙ ጌታዬ ንጉሡ በሞት ይቀጣኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ዳንኤል ራሱንና ጓደኞቹን ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና አዛርያን እንዲጠብቅ አሽፈናዝ ወደ መደበው ጠባቂ ሄዶ እንዲህ አለው፤ “አትክልት እየተመገብንና ውሃ እየጠጣን እንድንቈይ በማድረግ እኛን አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያኽል ፈትነን፤ ከዚያ በኋላ የእኛን ሁኔታ ከቤተ መንግሥት የታዘዘውን ምግብ ከሚመገቡ ወጣቶች ጋር ታስተያየዋለህ፤ በምታገኘውም ግንዛቤ መሠረት እኛን አገልጋዮችህን በተመለከተ የመሰለህን ታደርጋለህ።” ጠባቂውም በዚህ ሐሳብ ተስማምቶ ለዐሥር ቀን ፈተናቸው። ዐሥሩም ቀን ከተፈጸመ በኋላ ከንጉሡ ምግብ ከሚመገቡት ወጣቶች ሁሉ ይልቅ እነርሱ ፊታቸው አምሮ፥ ሰውነታቸው ወፍሮ ተገኙ። ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ጠባቂው ከቤተ መንግሥት የሚላክላቸውን ምርጥ ምግብና የወይን ጠጅ አስቀርቶ ለእነርሱ የአትክልት ምግብ ይሰጣቸው ጀመር። እግዚአብሔርም ለእነዚህ ለአራት ወጣቶች በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው።