የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 1:3-21

ዳንኤል 1:3-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያ በኋላ ንጉሡ የቤተ መንግሥቱን ጃንደረቦች አለቃ አስፋኔዝን፣ ከንጉሣዊው ቤተ ሰብና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑትን እስራኤላውያንን እንዲያመጣ አዘዘው፤ እነርሱም የአካል ጕዳት የሌለባቸው መልከ መልካሞች፣ ማንኛውንም ትምህርት የመማር ችሎታ ያላቸው፣ ዕውቀት የሞላባቸው፣ ሁሉን ነገር በፍጥነት መረዳት የሚችሉትንና በንጉሡም ቤት ለማገልገል ብቃት ያላቸው ወጣት ወንዶች ናቸው፤ የባቢሎናውያንን ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ እንዲያስተምራቸውም አዘዘው። ንጉሡም በየዕለቱ የሚበሉትን ምግብና የሚጠጡትን የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማእድ ድርጎ እንዲሰጣቸው አደረገ፤ ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ከይሁዳ የመጡት ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። የጃንደረቦቹ አለቃም አዲስ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፣ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያን አብድናጎ ብሎ ጠራቸው። ዳንኤል ግን በንጉሡ ምግብና የወይን ጠጅ እንዳይረክስ ወሰነ፤ በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ፈቃድ ጠየቀው። እግዚአብሔርም ለዳንኤል በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ሞገስንና መወደድን ሰጠው። ሆኖም የጃንደረቦቹ አለቃ ለዳንኤል፣ “መብሉንና መጠጡን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ብትታዩ፣ በንጉሡ ዘንድ በራሴ ላይ አደጋ ታስከትሉብኛላችሁ።” ብሎ ነገረው። ዳንኤልም የጃንደረቦቹን አለቃ በዳንኤል፣ በአናንያ፣ በሚሳኤልና በአዛርያስ ላይ የሾመውን መጋቢ እንዲህ አለው፤ “እባክህ አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ ለመብል ከአትክልት፣ ለመጠጥም ከውሃ በስተቀር ምንም አይሰጠን፤ ከዚያም የእኛን መልክና የንጉሡን መብል የሚበሉትን ወጣቶች መልክ አስተያይ፤ በአገልጋዮችህ ላይ የወደድኸውን አድርግብን።” እርሱም በዚህ ነገር ተስማማ፤ ለዐሥር ቀንም ፈተናቸው። ከዐሥር ቀን በኋላም የንጉሡን መብል ከበሉት ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ጤናማዎችና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ተገኙ። ስለዚህ መጋቢው ምርጥ የሆነውን ምግባቸውንና ሊጠጡት የሚገባውን የወይን ጠጅ አስቀርቶ በምትኩ አትክልት ሰጣቸው። እግዚአብሔር ለእነዚህ አራት ወጣቶች በማንኛውም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ማንኛውንም ራእይና ሕልም የመረዳት ችሎታ ነበረው። ወደ እርሱ እንዲመጡ ንጉሡ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ፣ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር አቀረባቸው። ንጉሡም ባነጋገራቸው ጊዜ ከመካከላቸው እንደ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ያለ ከቶ አልተገኘም፤ ስለዚህ በንጉሡ አገልግሎት ላይ ተሰማሩ። ንጉሡ በጠየቃቸው በማንኛውም የጥበብና የማስተዋል ጕዳይ በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኞችና ድግምተኞች ሁሉ ዐሥር እጅ በልጠው አገኛቸው። ዳንኤልም፣ ንጉሥ ቂሮስ እስከ ነገሠበት እስከ መጀመሪያው ዓመት ድረስ እዚያው ቈየ።

ዳንኤል 1:3-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ንጉሡም ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፥ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም የሞላባቸውን ብልሃተኞችና አስተዋዮች የሆኑትን፥ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር ያመጣ ዘንድ የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሩአቸው ዘንድ ለጃንደረቦች አለቃ ለአስፋኔዝ ነገረ። ንጉሡም ሦስት ዓመት ያሳድጉአቸው ዘንድ ከዚያም በኋላ በንጉሡ ፊት ይቆሙ ዘንድ ከንጉሡ መብል ከሚጠጣውም ጠጅ በየዕለቱ ድርጎአቸውን አዘዘላቸው። በእነዚህም መካከል ከይሁዳ ልጆች ዳንኤልና አናንያ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። የጃንደረቦቹም አለቃ ስም አወጣላቸው፥ ዳንኤልን ብልጣሶር፥ አናንያንም ሲድራቅ፥ ሚሳኤልንም ሚሳቅ፥ አዛርያንም አብደናጎ ብሎ ጠራቸው። ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ፥ እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነ። እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። የጃንደረቦቹም አለቃ ዳንኤልን፦ መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፥ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ፥ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ አለው። ዳንኤልም የጃንደርቦቹ አለቃ በዳንኤልና በአናንያ በሚሳኤልና በአዛርያ ላይ የሾመውን ሜልዳርን፦ እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ፥ የምንበላውንም ጥራጥሬ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፥ ከዚያም በኋላ የእኛን ፊትና ከንጉሡ መብል የሚበሉትን የብላቴኖችን ፊት ተመልከት፥ እንዳየኸውም ሁሉ ከባሪያዎችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ አለው። ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው። ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ። ሜልዳርም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው። ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፥ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። እነርሱም ይገቡ ዘንድ ንጉሡ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ፥ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከነፆር ዘንድ አገባቸው። ንጉሡም በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም፥ በንጉሡም ፊት ቆሙ። ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው። ዳንኤልም እስከ ንጉሡ እስከ ቂሮስ መጀመሪያ ዓመት ተቀመጠ።

ዳንኤል 1:3-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር አሽፈናዝ የተባለውን የባለሟሎቹን አለቃ ከእስራኤል ምርኮኞች መካከል የንጉሣዊ ቤተሰቦችና የመሳፍንት ልጆች ከሆኑት ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹን መርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ የሚመረጡትም ወጣቶች በቤተ መንግሥት ለማገልገል በቂ ችሎታ እንዲኖራቸው፥ መልከ መልካሞች፥ ጥበብን ሁሉ ማስተዋልና ሁሉን ነገር በፍጥነት መረዳት የሚችሉ፥ የአካል ጒድለት የሌለባቸው መሆን ይገባቸዋል፤ እንዲሁም የባቢሎናውያንን ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ያስተምራቸውም ዘንድ አዘዘው። ምግባቸውና የሚጠጡት የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማእድ እንዲሆን ታዘዘላቸው፤ በዚህ ዐይነት ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ ፊት ቀርበው የቤተ መንግሥት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተወሰነ። ከተመረጡትም መካከል ነገዳቸው ከይሁዳ ወገን የሆነ ዳንኤል፥ ሐናንያ፥ ሚሳኤልና ዐዛርያ ነበሩ። የንጉሡም ባለሟሎች አለቃ ስማቸውን በመለወጥ ዳንኤልን ብልጣሶር፤ ሐናንያን ሲድራቅ፤ ሚሳኤልን ሚሳቅ፤ ዐዛርያን አብደናጎ ብሎ ጠራቸው። ዳንኤል ከንጉሡ ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሱን ላለማርከስ ወሰነ፤ በዚህም ሐሳብ እንዲስማማለት አሽፈናዝን ለመነው። እግዚአብሔርም ለዳንኤል በሹሙ ፊት ሞገስን ሰጥቶ ልቡን አራራለት። ይሁን እንጂ ንጉሡን ስለ ፈራ አሽፈናዝ ዳንኤልን “ምግባችሁንና መጠጣችሁን ያዘዘ ንጉሡ ራሱ ነው፤ እናንተ ከሌሎቹ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁና ተጐሳቊላችሁ ብትገኙ ጌታዬ ንጉሡ በሞት ይቀጣኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ዳንኤል ራሱንና ጓደኞቹን ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና አዛርያን እንዲጠብቅ አሽፈናዝ ወደ መደበው ጠባቂ ሄዶ እንዲህ አለው፤ “አትክልት እየተመገብንና ውሃ እየጠጣን እንድንቈይ በማድረግ እኛን አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያኽል ፈትነን፤ ከዚያ በኋላ የእኛን ሁኔታ ከቤተ መንግሥት የታዘዘውን ምግብ ከሚመገቡ ወጣቶች ጋር ታስተያየዋለህ፤ በምታገኘውም ግንዛቤ መሠረት እኛን አገልጋዮችህን በተመለከተ የመሰለህን ታደርጋለህ።” ጠባቂውም በዚህ ሐሳብ ተስማምቶ ለዐሥር ቀን ፈተናቸው። ዐሥሩም ቀን ከተፈጸመ በኋላ ከንጉሡ ምግብ ከሚመገቡት ወጣቶች ሁሉ ይልቅ እነርሱ ፊታቸው አምሮ፥ ሰውነታቸው ወፍሮ ተገኙ። ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ጠባቂው ከቤተ መንግሥት የሚላክላቸውን ምርጥ ምግብና የወይን ጠጅ አስቀርቶ ለእነርሱ የአትክልት ምግብ ይሰጣቸው ጀመር። እግዚአብሔርም ለእነዚህ ለአራት ወጣቶች በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው። ንጉሡ የወሰነው ሦስት ዓመት ሲፈጸም አሽፈናዝ ወጣቶቹን ሁሉ ወስዶ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። ንጉሡ ሁሉንም ባነጋገራቸው ጊዜ ከእነርሱ መካከል ዳንኤልን፥ ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና ዐዛርያን የሚወዳደር አልተገኘም፤ ስለዚህ እነርሱ በንጉሡ ፊት እንዲያገለግሉ ተመረጡ። ጥበብና ማስተዋልን በተመለከቱ ጉዳዮች ንጉሡ በሚጠይቃቸው ነገሮች በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ከሚገኙ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያላቸው ሆነው አገኛቸው። በዚህ ዐይነት ዳንኤል ቂሮስ እስከ ነገሠበት መጀመሪያ ዓመት ድረስ በቤተ መንግሥት ውስጥ ማገልገሉን ቀጠለ።