ዳንኤል 1:14-21

ዳንኤል 1:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እርሱም በዚህ ነገር ተስማማ፤ ለዐሥር ቀንም ፈተናቸው። ከዐሥር ቀን በኋላም የንጉሡን መብል ከበሉት ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ጤናማዎችና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ተገኙ። ስለዚህ መጋቢው ምርጥ የሆነውን ምግባቸውንና ሊጠጡት የሚገባውን የወይን ጠጅ አስቀርቶ በምትኩ አትክልት ሰጣቸው። እግዚአብሔር ለእነዚህ አራት ወጣቶች በማንኛውም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ማንኛውንም ራእይና ሕልም የመረዳት ችሎታ ነበረው። ወደ እርሱ እንዲመጡ ንጉሡ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ፣ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር አቀረባቸው። ንጉሡም ባነጋገራቸው ጊዜ ከመካከላቸው እንደ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ያለ ከቶ አልተገኘም፤ ስለዚህ በንጉሡ አገልግሎት ላይ ተሰማሩ። ንጉሡ በጠየቃቸው በማንኛውም የጥበብና የማስተዋል ጕዳይ በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኞችና ድግምተኞች ሁሉ ዐሥር እጅ በልጠው አገኛቸው። ዳንኤልም፣ ንጉሥ ቂሮስ እስከ ነገሠበት እስከ መጀመሪያው ዓመት ድረስ እዚያው ቈየ።

ዳንኤል 1:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው። ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ። ሜልዳርም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው። ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፥ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። እነርሱም ይገቡ ዘንድ ንጉሡ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ፥ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከነፆር ዘንድ አገባቸው። ንጉሡም በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም፥ በንጉሡም ፊት ቆሙ። ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው። ዳንኤልም እስከ ንጉሡ እስከ ቂሮስ መጀመሪያ ዓመት ተቀመጠ።

ዳንኤል 1:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጠባቂውም በዚህ ሐሳብ ተስማምቶ ለዐሥር ቀን ፈተናቸው። ዐሥሩም ቀን ከተፈጸመ በኋላ ከንጉሡ ምግብ ከሚመገቡት ወጣቶች ሁሉ ይልቅ እነርሱ ፊታቸው አምሮ፥ ሰውነታቸው ወፍሮ ተገኙ። ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ጠባቂው ከቤተ መንግሥት የሚላክላቸውን ምርጥ ምግብና የወይን ጠጅ አስቀርቶ ለእነርሱ የአትክልት ምግብ ይሰጣቸው ጀመር። እግዚአብሔርም ለእነዚህ ለአራት ወጣቶች በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው። ንጉሡ የወሰነው ሦስት ዓመት ሲፈጸም አሽፈናዝ ወጣቶቹን ሁሉ ወስዶ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። ንጉሡ ሁሉንም ባነጋገራቸው ጊዜ ከእነርሱ መካከል ዳንኤልን፥ ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና ዐዛርያን የሚወዳደር አልተገኘም፤ ስለዚህ እነርሱ በንጉሡ ፊት እንዲያገለግሉ ተመረጡ። ጥበብና ማስተዋልን በተመለከቱ ጉዳዮች ንጉሡ በሚጠይቃቸው ነገሮች በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ከሚገኙ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያላቸው ሆነው አገኛቸው። በዚህ ዐይነት ዳንኤል ቂሮስ እስከ ነገሠበት መጀመሪያ ዓመት ድረስ በቤተ መንግሥት ውስጥ ማገልገሉን ቀጠለ።