ቈላስይስ 3:10-16
ቈላስይስ 3:10-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፈጣሪውን ለመምሰል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱት። በእርሱ ዘንድ አይሁዳዊ፥ ግሪካዊም፥ የተገዘረ፥ ያልተገዘረም፥ አረመኔም፥ ባላገርም፥ ቤተ ሰብእና አሳዳሪ ማለት የለም ነገር ግን ክርስቶስ ለሁሉ በሁሉም ዘንድ ነው። እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ መረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች፥ ምሕረትንና ርኅራኄን፥ ቸርነትንና ትሕትናን፥ የውሀትንና ትዕግሥትን ልበሱት። ባልንጀሮቻችሁን ታገሡአቸው፤ እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ፤ ባልንጀሮቻችሁን የነቀፋችሁበትን ሥራ ተዉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። ከዚህም ሁሉ ጋር ዘወትር ተፋቀሩ፤ የመጨረሻው ማሰሪያ እርሱ ነውና። በአንድ አካል የተጠራችሁለት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ጸንቶ ይኑር፤ ክርስቶስንም በማመስገን ኑሩ። በጥበብ ሁሉ እንድትበለጽጉ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ዘንድ ይጽና፤ በመንፈስም ራሳችሁን አስተምሩ፤ ገሥፁ፤ መዝሙርንና ምስጋናን፥ የቅድስና ማሕሌትንም በልባችሁ በጸጋ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ቈላስይስ 3:10-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ቈላስይስ 3:10-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ቈላስይስ 3:10-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በፈጣሪው አምሳል በዕውቀት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ባሕርይ ልበሱ። በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔር ምርጦችና ቅዱሳን፥ የተወደዳችሁም እንደ መሆናችሁ መጠን ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ ገርነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ይቅር በሉ። ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉን ነገር ሰብስቦ በማሰር ፍጹም አንድነትን የሚያስገኘውን ፍቅርን ልበሱ። የአንድ አካል ክፍሎች ሆናችሁ በእርግጥ የተጠራችሁት ለዚህ ሰላም ስለ ሆነ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በልባችሁ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመሰገናችሁ ዘምሩ።
ቈላስይስ 3:10-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንደ ፈጣሪውም መልክ በእውቀት የታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንና የተወደዳችሁ ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ማንም ሰው በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ይቅር በሉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካል ሥር ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ውስጥ ገዢ ይሁን፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በእናንተ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩም፤ በመዝሙርና በውዳሴ በመንፈሳዊም ዝማሬ በልባችሁ በማመስገን ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤