ቈላስይስ 3:1-14
ቈላስይስ 3:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሯልና፤ ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
ቈላስይስ 3:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ በአለበት በላይ ያለውን ሹ። የላይኛውን አስቡ፤ በምድር ያለውንም አይደለም። እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና። ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያንጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ። ምድራዊ ሰውነታችሁንም ከዝሙትና ከርኵሰት፥ ከጥፋትና ከክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ ከሆነው ከቅሚያም ግደሉት። በእነርሱም ምክንያት በማይታዘዙ ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ይመጣል። እናንተም ቀድሞ በዚህ ሥራ በነበራችሁ ጊዜ የሄዳችሁበት ነው። አሁንም ቍጣንና ብስጭትን፥ ክፋትንና ስድብን፥ የሚያሳፍረውንም ነገር ተዉ፤ ከንቱ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ተዉት እንጂ፤ ወንድሞቻችሁን አቷሹ። ፈጣሪውን ለመምሰል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱት። በእርሱ ዘንድ አይሁዳዊ፥ ግሪካዊም፥ የተገዘረ፥ ያልተገዘረም፥ አረመኔም፥ ባላገርም፥ ቤተ ሰብእና አሳዳሪ ማለት የለም ነገር ግን ክርስቶስ ለሁሉ በሁሉም ዘንድ ነው። እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ መረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች፥ ምሕረትንና ርኅራኄን፥ ቸርነትንና ትሕትናን፥ የውሀትንና ትዕግሥትን ልበሱት። ባልንጀሮቻችሁን ታገሡአቸው፤ እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ፤ ባልንጀሮቻችሁን የነቀፋችሁበትን ሥራ ተዉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። ከዚህም ሁሉ ጋር ዘወትር ተፋቀሩ፤ የመጨረሻው ማሰሪያ እርሱ ነውና።
ቈላስይስ 3:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።
ቈላስይስ 3:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከሞት ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ በሰማይ ያሉትን ነገሮች ፈልጉ። ዘወትር በላይ በሰማይ ስላሉት ነገሮች አስቡ እንጂ በምድር ላይ ስላሉት ነገሮች አታስቡ። እናንተ በሞት የመለየትን ያኽል ከዚህ ዓለም ተለይታችኋል፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአል። ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። ስለዚህ በእናንተ የሚገኙትን የምድራዊ ሕይወት ምኞቶች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም “ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ፍትወት፥ ክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀት” ናቸው። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በማይታዘዙ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። እናንተም ራሳችሁ ከዚህ በፊት በማይታዘዙ ሰዎች መካከል ሳላችሁ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ትኖሩ ነበር። አሁን ግን ቊጣን፥ ንዴትን፥ ተንኰልን፥ ስም ማጥፋትን ከእናንተ አስወግዱ፤ የሚያሳፍር ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ባሕርይ ከነሥራው አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁት እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። በፈጣሪው አምሳል በዕውቀት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ባሕርይ ልበሱ። በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔር ምርጦችና ቅዱሳን፥ የተወደዳችሁም እንደ መሆናችሁ መጠን ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ ገርነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ይቅር በሉ። ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉን ነገር ሰብስቦ በማሰር ፍጹም አንድነትን የሚያስገኘውን ፍቅርን ልበሱ።
ቈላስይስ 3:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ በሰማይ ስላለው አስቡ እንጂ በምድር ስላለው አታስቡ። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በተገለጠ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በእናንተ ያሉትን ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም፦ “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ ስግብግብነት” ናቸው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም በቀድሞው ሕይወታችሁ ስትኖሩ እነዚህን ነገሮች በመተግበር ትመላለሱ ነበር። አሁን ግን እናንተ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁ አስወግዳችሁታልና እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፤ እንደ ፈጣሪውም መልክ በእውቀት የታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንና የተወደዳችሁ ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ማንም ሰው በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ይቅር በሉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።