ቈላስይስ 2:9-15
ቈላስይስ 2:9-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና። የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል። እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ። ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው። አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው።
ቈላስይስ 2:9-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በርሱ ይኖራልና፤ እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። በርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ በጥምቀትም ከርሱ ጋራ ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከርሱ ጋራ ደግሞ ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከክርስቶስ ጋራ ሕያዋን አደረጋችሁ፤ በደላችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤ ሲቃወመንና ሲፃረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። የገዦችና የባለሥልጣናትንም ማዕርግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ።
ቈላስይስ 2:9-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።
ቈላስይስ 2:9-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአምላክነት ፍጹም ሙላት በአካል ተገልጦ የሚኖረው በክርስቶስ ነው። እናንተም ሙሉ ሕይወትን ያገኛችሁት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የግዛትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ነው። በእርሱም በማመናችሁ ተገርዛችኋል፤ ይህም መገረዛችሁ ኃጢአተኛውን የሥጋ ባሕርይ ለማስወገድ በክርስቶስ የተደረገ ነው እንጂ በሰው እጅ የተደረገ አይደለም። በተጠመቃችሁ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተቀበራችሁ፤ ከእርሱም ጋር ከሞት ተነሥታችኋል፤ ከሞት የተነሣችሁትም ክርስቶስን ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመናችሁ ነው። ኃጢአት በመሥራታችሁና የኃጢአተኛው ሥጋችሁ በክርስቶስ በማመን ባለመገረዙ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል፤ ኃጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር ብሎላችኋል። እርሱ ያንን ይከሰንና ይቃወመን የነበረውን በሕግ ያለውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰው፤ በመስቀል ላይ ቸንክሮም ከእኛ አስወገደው። ኀይሎችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነሥቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው።
ቈላስይስ 2:9-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል ተገልጦ ይኖራልና፤ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። በክርስቶስ መገረዝ የሥጋዊውን አካል በመግፈፍ በሰው እጅ ባልተከናወነ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሞታችሁ የነበራችሁትን በደላችንን ሁሉ ይቅር ባለን ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ እርሱም ይፃረረንና ይቃወመን የነበረውን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ በመስቀልም ላይ ቸንክሮ ከእኛ አስወገደው፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ በመስቀሉ ድል በመንሣት እነርሱን በይፋ አጋለጣቸው።