ቈላስይስ 2:8-12
ቈላስይስ 2:8-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥርዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ ተጠንቀቁ። በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና። የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል።
ቈላስይስ 2:8-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ። የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና፤ እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከእርሱ ጋር ደግሞ ተነሣችሁ።
ቈላስይስ 2:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።
ቈላስይስ 2:8-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በክርስቶስ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሰው ሠራሽ ወግና በዓለማዊ ተራ ሥርዓት ላይ በተመሠረተ በፍልስፍናና በከንቱ ሽንገላ ማንም እንዳያጠምዳችሁ ተጠንቀቁ። የአምላክነት ፍጹም ሙላት በአካል ተገልጦ የሚኖረው በክርስቶስ ነው። እናንተም ሙሉ ሕይወትን ያገኛችሁት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የግዛትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ነው። በእርሱም በማመናችሁ ተገርዛችኋል፤ ይህም መገረዛችሁ ኃጢአተኛውን የሥጋ ባሕርይ ለማስወገድ በክርስቶስ የተደረገ ነው እንጂ በሰው እጅ የተደረገ አይደለም። በተጠመቃችሁ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተቀበራችሁ፤ ከእርሱም ጋር ከሞት ተነሥታችኋል፤ ከሞት የተነሣችሁትም ክርስቶስን ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመናችሁ ነው።
ቈላስይስ 2:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ መሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ በፍልስፍናና በከንቱ መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠንቀቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል ተገልጦ ይኖራልና፤ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። በክርስቶስ መገረዝ የሥጋዊውን አካል በመግፈፍ በሰው እጅ ባልተከናወነ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።