ሐዋርያት ሥራ 6:1-4
ሐዋርያት ሥራ 6:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያም ወራት ደቀ መዛሙርት በበዙ ጊዜ ከግሪክ የመጡ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ ምእመናን ላይ አንጐራጐሩባቸው፤ የዕለት የዕለቱን ምግብ ሲያካፍሉ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ነበርና። ዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም። ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን። እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።”
ሐዋርያት ሥራ 6:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የደቀ መዛሙርት ቍጥር እየጨመረ በሄደበት በዚህ ወቅት፣ ከግሪክ አገር የመጡ አይሁድ በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት አይሁድ ላይ አጕረመረሙ፤ ምክንያቱም በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ ተብለው ነበር። ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሌሎችን ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “እኛ የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤ እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን።”
ሐዋርያት ሥራ 6:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፦ “የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።”
ሐዋርያት ሥራ 6:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአማኞች ቊጥር እየበዛ ሲሄድ የግሪክ ቋንቋ የሚናገሩ አይሁድ የይሁዳ አገር ተወላጆች በሆኑት አይሁድ ላይ ማጒረምረም ጀመሩ፤ ያጒረመረሙትም በየቀኑ ይታደል በነበረው ርዳታ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ችላ ይሉባቸው ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አማኞችን ሁሉ ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “ምግብ ለማደል ብለን የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማር ሥራችንን መተው አይገባንም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ፥ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን ከመካከላችሁ ምረጡ፤ እነርሱን ለዚህ ኀላፊነት እንሾማቸዋለን። እኛ ግን በመጸለይና የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር እንተጋለን።”
ሐዋርያት ሥራ 6:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፤ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። ዐሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው “የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ! በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፤ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።”