ሐዋርያት ሥራ 5:34-39
ሐዋርያት ሥራ 5:34-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ። ከርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው! አትንኳቸው! ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋራ ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።”
ሐዋርያት ሥራ 5:34-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሸንጎዉም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ የኦሪት መምህር ስሙን ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ ተነሣ፤ ሐዋርያትንም ከጉባኤዉ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ቀድሞም ከዚህ ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፤ ነገር ግን እርሱም ጠፋ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፤ እንደ ኢምንትም ሆኑ። ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ እርሱም ሞተ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ሰዎች ራቁ፤ ተዉአቸውም፤ ይህ ምክራቸው፥ ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል ይጠፋልም። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት አትችሉም፤ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።”
ሐዋርያት ሥራ 5:34-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ። ከርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው! አትንኳቸው! ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋራ ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።”
ሐዋርያት ሥራ 5:34-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ እንዲህም አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ፦ “እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፥ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።”
ሐዋርያት ሥራ 5:34-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የሕግ መምህር የሆነ፥ ገማልያል የተባለ አንድ ፈሪሳዊ የሸንጎ አባል ተነሣና ለጥቂት ጊዜ ሐዋርያቱን ገለል እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። ከዚህ በኋላ የሸንጎውን አባሎች እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ በምታደርጉት ነገር ተጠንቀቁ። ከዚህ በፊት ቴዎዳስ የሚባል ሰው ‘እኔ ትልቅ ሰው ነኝ’ ብሎ ተነሥቶ ነበር፤ አራት መቶ የሚያኽሉም ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እርሱ ተገደለ፤ ተከታዮቹ ተበታተኑ፤ ዓላማውም እንዳልነበረ ሆነ። ከዚያም በኋላ የሕዝብ ቈጠራ በተደረገበት ዘመን ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሰዎች እንዲከተሉት አድርጎ ነበር፤ እርሱም ተገደለ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። ስለዚህ አሁንም እኔ የምላችሁ ከነዚህ ሰዎች እንድትርቁና እንድትተዉአቸው ነው፤ ይህ አሳብ ወይም ሥራ ከሰው የመጣ ከሆነ ይጠፋል። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን እነርሱን ልታጠፉአቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ይሆንባችኋል።” እነርሱም የገማልያልን ምክር ተቀበሉ።
ሐዋርያት ሥራ 5:34-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፤ እንዲህም አላቸው “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ ‘እኔ ታላቅ ነኝ፤’ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፤ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፤ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ ‘ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።’”