ሐዋርያት ሥራ 5:12-42
ሐዋርያት ሥራ 5:12-42 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሐዋርያት እጅም በሕዝቡ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤ በቤተ መቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ነበሩ። ሕዝቡም እጅግ ያከብሩአቸው ነበረ። ከሌሎችም ይቀርባቸው ዘንድ አንድ ስንኳን የሚደፍር አልነበረም። በጌታችንም የሚያምኑ ብዙዎች ይጨመሩ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙዎች ነበሩ። ጴጥሮስም አልፎ ሲሄድ ጥላው ያርፍባቸው ዘንድ ድውዮችን በአልጋና በቃሬዛ እያመጡ በአደባባይ ያስቀምጡአቸው ነበር፤ ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከአሉ ከተሞች ብዙዎች ይመጡ ነበር፤ የታመሙትንና ክፉዎች አጋንንት የያዙአቸውንም ያመጡ ነበር፥ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገኖችም ቀንተው በእነርሱ ላይ ተነሡ። እጃቸውንም በሐዋርያት ላይ አነሡ፤ ያዙአቸውም፤ በሕዝቡ ወኅኒ ቤትም አስገቧቸው። የእግዚአብሔር መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒ ቤቱን ደጃፍ ከፍቶ አወጣቸው፤ እንዲህም አላቸው። “ሂዱ፤ ወደ ቤተ መቅደስም ግቡና ለሕዝብ ይህን የሕይወት ቃል አስተምሩአቸው።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ጥዋት ገስግሠው ወደ ቤተ መቅደስ ገቡና አስተማሩ፤ ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ግን ጉባኤውንና ከእስራኤልም ቤት ሽማግሌዎችን ሁሉ ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም ያመጡአቸው ዘንድ ወደ ወኅኒ ቤት ላኩ። አሽከሮቻቸውም መጥተው በወኅኒ ቤት አጡአቸውና ተመልሰው ነገሩአቸው። “ወኅኒ ቤቱንም ዙሪያውን ተዘግቶ በቍልፍም ተቈልፎ አገኘነው፤ ወታደሮቹም በሩን ይጠብቁ ነበር፤ ነገር ግን ከፍተን በገባን ጊዜ በውስጥ ያገኘነው የለም” አሉአቸው። ሊቃነ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ሹምም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ፥ የሚያደርጉትን አጥተው፥ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” አሉ። አንድ ሰውም መጥቶ፥ “ያሰራችኋቸው እነዚያ ሰዎች እነሆ፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ ናቸው፤ ቆመውም ሕዝቡን ያስተምራሉ” ብሎ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ የቤተ መቅደሱ ሹም ከሎሌዎቹ ጋር ሔዶ አባብሎ አመጣቸው፤ በግድም አይደለም፤ በድንጋይ እንዳይደበድቧቸው ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። አምጥተውም በሸንጎ መካከል አቆሙአቸው፤ ሊቀ ካህናቱም መረመራቸው፤ “በኢየሱስ ስም ለማንም እንዳታስተምሩ ከልክለናችሁ አልነበረምን? እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ላይ ታመጡብን ዘንድ ትሻላችሁን?” አላቸው። ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉአቸው፥ “ለሰው ከመታዘዝ ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባል። የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ ክዳችሁ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን አስነሣው። እግዚአብሔር እርሱን ለእስራኤል ንስሓን፥ የኀጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ ራስም አዳኝም አደረገው፤ በቀኙም አስቀመጠው። እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮቹ ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ተበሳጩ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩ፤ ሊገድሉአቸውም ወደዱ። በሸንጎዉም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ የኦሪት መምህር ስሙን ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ ተነሣ፤ ሐዋርያትንም ከጉባኤዉ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ቀድሞም ከዚህ ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፤ ነገር ግን እርሱም ጠፋ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፤ እንደ ኢምንትም ሆኑ። ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ እርሱም ሞተ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ሰዎች ራቁ፤ ተዉአቸውም፤ ይህ ምክራቸው፥ ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል ይጠፋልም። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት አትችሉም፤ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።” እሺም አሰኛቸው፤ ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፉአቸው፤ እንግዲህ ወዲህም በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ገሥጸው ተዉአቸው። እነርሱም ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ስለ ስሙ መከራ ይቀበሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አድሎአቸዋልና። ሁልጊዜም በቤተ መቅደስና በቤት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አልተዉም።
ሐዋርያት ሥራ 5:12-42 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሐዋርያትም በሕዝቡ መካከል ብዙ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎችን አደረጉ፤ አማኞቹም ሁሉ “የሰሎሞን ደጅ” በተባለው መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር። ከእነርሱ ጋር ሊቀላቀል የደፈረ ማንም አልነበረም፤ ሆኖም ሕዝቡ እጅግ ያከብሯቸው ነበር፤ ብዙ ወንዶችና ሴቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጌታ እያመኑ ወደ እነርሱ ይጨመሩ ነበር። ከዚህም የተነሣ፣ ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ፣ ቢያንስ ጥላው እንኳ በጥቂቶች ላይ እንዲያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን ወደ ውጭ እያወጡ በዐልጋና በቃሬዛ በመንገድ ላይ ያስተኙ ነበር። በኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች፣ ሕመምተኞችንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ይዘው የሚመጡት ሰዎች አካባቢውን ያጨናንቁት ነበር፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር። ከዚህም የተነሣ ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገን ሁሉ በቅናት ተሞሉ፤ ሐዋርያትንም ይዘው ማረፊያ ቤት ከተቷቸው። ይሁን እንጂ የጌታ መልአክ በሌሊት የእስር ቤቱን ደጆች ከፍቶ አወጣቸውና፣ “ሂዱ፤ በቤተ መቅደሱም አደባባይ ቁሙ፤ የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” አላቸው። እንደ ነጋም፣ በተነገራቸው መሠረት ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገብተው ሕዝቡን ማስተማር ጀመሩ። ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የአይሁድን ሸንጎና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጉባኤ በሙሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ላኩ። የተላኩትም ወደ እስር ቤቱ ሄደው በዚያ አላገኟቸውም፤ ተመልሰውም እንዲህ አሏቸው፤ “እስር ቤቱ በሚገባ ተቈልፎ፣ ጠባቂዎቹም በበሩ ላይ ቆመው አገኘን፤ ከፍተን ስንገባ ግን በውስጡ ማንም አልነበረም።” የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሹምና የካህናት አለቆችም ይህን በሰሙ ጊዜ በነገሩ ተገረሙ፤ ግራም ተጋቡ። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ፣ “እነሆ፤ እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመው ሕዝቡን እያስተማሩ ናቸው” አላቸው። የጥበቃ ሹሙም ከወታደሮቹ ጋር ሄዶ፣ ይዞ አመጣቸው፤ ያመጧቸው ግን ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግሯቸው ስለ ፈሩ በኀይል ሳያስገድዱ ነበር። ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።” ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል! እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤ እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ። ከእርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው፤ አትንኳቸው፤ ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።” እነርሱም ምክሩን ተቀብለው ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ለቀቋቸው። ሐዋርያትም፣ ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 5:12-42 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ። ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ። ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም ሞላባቸው። በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው። የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና፦ “ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ” አላቸው። በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፥ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ። ሌሎዎችም መጥተው በወኅኒው አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም፦ “ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ቆመው አገኘን፥ በከፈትን ጊዜ ግን በውስጡ አንድ ስንኳ አላገኘንም” አሉአቸው። የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ፦ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ። አንድ ሰውም መጥቶ፦ “እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው” ብሎ አወራላቸው። በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና። አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው። ሊቀ ካህናቱም፦ “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ፦ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ። ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ እንዲህም አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ፦ “እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፥ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።” ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 5:12-42 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብዙ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በሕዝቡ መካከል በሐዋርያት እጅ ይደረጉ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር። ከእነርሱ ውጪ ከሆኑት ሰዎች አንድ እንኳ ከእነርሱ ጋር ለመሆን የሚደፍር አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ ያከብራቸው ነበር። በጌታ የሚያምኑ ወንዶችና ሴቶች ቊጥራቸው በጣም እየበዛ ይሄድ ነበር። ሰዎች ብዙ በሽተኞችን ወደ መንገድ እያወጡ በአልጋ ላይና በቃሬዛ ላይ ያስተኙአቸው ነበር፤ እንዲህም ያደረጉት ጴጥሮስ በዚያ በኩል ሲያልፍ ጥላው እንኳ በአንዳንዶቹ ላይ እንዲያርፍባቸው ነበር። ሰዎች በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካሉት ከተሞች በሽተኞቻቸውንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ያመጡ ነበር፤ ሁሉም ይድኑ ነበር። የካህናት አለቃውና ከእርሱ ጋር የነበሩት የሰዱቃውያን ወገኖች ሁሉ በቅንነት ተሞልተው በእነርሱ ላይ ተነሡ፤ ሐዋርያትን ያዙና በሕዝቡ ወህኒ ቤት አስገቡአቸው። የእግዚአብሔር መልአክ ግን በሌሊት የወህኒ ቤቱን በሮች ከፍቶ፥ አስወጣቸውና፥ “ሂዱ! በቤተ መቅደስ ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝቡ ንገሩ!” አላቸው፤ ሐዋርያቱም ትእዛዙን ተቀብለው በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡና ማስተማር ጀመሩ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃውና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የሸንጎውን አባሎችና የአይሁድ ሽማግሌዎችን ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡአቸው ሰዎችን ወደ ወህኒ ቤት ላኩ። የዘብ ኀላፊዎቹ ግን ወደ ወህኒ ቤት ሄደው ሐዋርያትን በዚያ አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም መጡና “የወህኒ ቤቱ በር በጥብቅ ተቈልፎ ጠባቂዎችም በበሩ ፊት ቆመው አገኘናቸው፤ የወህኒ ቤቱን በር በከፈትነው ጊዜ ግን በውስጥ ማንንም አላገኘንም” ብለው ተናገሩ። የቤተ መቅደሱ የዘብ አዛዥና የካህናት አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” በማለት ግራ ተጋቡ። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጣና “በወህኒ ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች እነሆ፥ በቤተ መቅደስ ቆመው ሕዝቡን ያስተምራሉ” ብሎ ነገራቸው። ወዲያውኑ የቤተ መቅደሱ የዘበኞች አለቃና ሎሌዎቹ ሄደው አመጡአቸው፤ ያመጡአቸውም በኀይል ሳይሆን በማግባባት ነው፤ ይህንንም ያደረጉት ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግራቸው በመፍራት ነው። አምጥተውም በሸንጎው ፊት አቆሙአቸው፤ የካህናት አለቃውም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “የኢየሱስን ስም በመጥራት እንዳታስተምሩ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ እናንተ ለዚያ ሰው ሞት እኛን ተጠያቂዎች ልታደርጉን ትፈልጋላችሁ።” ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ግን እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ለሰው ከመታዘዝ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል፤ የአባቶቻችን አምላክ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን ከሞት አስነሣው፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ንስሓንና የኃጢአትን ይቅርታ እንዲሰጥ ኢየሱስን መሪና አዳኝ አድርጎ በቀኙ በክብር እንዲቀመጥ አድርጎታል፤ ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።” የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ በጣም ተቈጥተው ሐዋርያቱን ለመግደል ፈለጉ። ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የሕግ መምህር የሆነ፥ ገማልያል የተባለ አንድ ፈሪሳዊ የሸንጎ አባል ተነሣና ለጥቂት ጊዜ ሐዋርያቱን ገለል እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። ከዚህ በኋላ የሸንጎውን አባሎች እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ በምታደርጉት ነገር ተጠንቀቁ። ከዚህ በፊት ቴዎዳስ የሚባል ሰው ‘እኔ ትልቅ ሰው ነኝ’ ብሎ ተነሥቶ ነበር፤ አራት መቶ የሚያኽሉም ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እርሱ ተገደለ፤ ተከታዮቹ ተበታተኑ፤ ዓላማውም እንዳልነበረ ሆነ። ከዚያም በኋላ የሕዝብ ቈጠራ በተደረገበት ዘመን ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሰዎች እንዲከተሉት አድርጎ ነበር፤ እርሱም ተገደለ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። ስለዚህ አሁንም እኔ የምላችሁ ከነዚህ ሰዎች እንድትርቁና እንድትተዉአቸው ነው፤ ይህ አሳብ ወይም ሥራ ከሰው የመጣ ከሆነ ይጠፋል። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን እነርሱን ልታጠፉአቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ይሆንባችኋል።” እነርሱም የገማልያልን ምክር ተቀበሉ። ከዚህ በኋላ ሐዋርያቱን ወደ እነርሱ ጠርተው አስገረፉአቸው፤ የኢየሱስንም ስም በመጥራት እንዳይናገሩ አዘዙአቸውና ለቀቁአቸው። ሐዋርያት ግን ስለ ኢየሱስ ስም ውርደት ለመቀበል የተገቡ በመሆናቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየቀኑም በቤተ መቅደስና በየቤቱም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ማስተማርንና የምሥራች መናገርን አላቋረጡም ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 5:12-42 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ። ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፤ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ። ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኩሳን መናፍስት የተሠቃዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ፤ ቅንዓትም ሞላባቸው። በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው። የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና “ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ፤” አላቸው። በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፤ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ። ሌሎዎችም መጥተው በወኅኒው አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም “ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ቆመው አገኘን፤ በከፈትን ጊዜ ግን በውስጡ አንድ ስንኳ አላገኘንም፤” አሉአቸው። የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ። አንድ ሰውም መጥቶ “እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው፤” ብሎ አወራላቸው። በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፤ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና። አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው። ሊቀ ካህናቱም “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ፤” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ “ከሰው ሥልጣን ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት እንዲሰጥ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቆጡ፤ ሊገድሉአቸውም አሰቡ። ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፤ እንዲህም አላቸው “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ ‘እኔ ታላቅ ነኝ፤’ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፤ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፤ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ ‘ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።’” ሰሙትም፤ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፤ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።