ሐዋርያት ሥራ 4:23-28
ሐዋርያት ሥራ 4:23-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ተፈትተውም ወደ ሰዎቻቸው ሄዱ፤ ሊቃነ ካህናትና ሽማግሌዎችም ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በአንድነት ቃላቸውን ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፥ “ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠርህ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ራስህ በአባታችን በባሪያህ በዳዊት አፍ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብለህ የተናገርህ፦ አሕዛብ ለምን ተሰበሰቡ? ሕዝቡስ ለምን ከንቱ ነገርን ተናገሩ? የምድር ነገሥታት ለምን ተነሡ? አለቆችስ ከእነርሱ ጋር አብረው በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ ለምን ዶለቱ? በቀባኸው በቅዱስ ልጅህ ላይ ሄሮድስና ጰንጤናዊው ጲላጦስ ከወገኖቻቸውና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በእውነት በዚች ሀገር ላይ ዶለቱ። እጅህና ምክርህ እንዲደረግ የወሰኑትን ይፈጽሙ ዘንድ።
ሐዋርያት ሥራ 4:23-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጴጥሮስና ዮሐንስም ከተፈቱ በኋላ ወደ ወገኖቻቸው ተመልሰው፣ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ልዑል ጌታ ሆይ፤ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤ በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ “ ‘አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በጌታና በመሲሑ ላይ ሊመክሩ ተሰበሰቡ።’ በእውነትም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋራ በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ፤ ይህም የሆነው የአንተ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።
ሐዋርያት ሥራ 4:23-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ውፍደ እፍዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥ በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ፦ አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ? የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገር አምላክ ነህ። በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።
ሐዋርያት ሥራ 4:23-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጴጥሮስና ዮሐንስ ተለቀው ወደ ጓደኞቻቸው በተመለሱ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ከፍ አድርገው ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲሉ ጸለዩ፤ “ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርን፥ በውስጣቸው የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርክ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ የተናገርክ አንተ ነህ፤ ‘አሕዛብ ስለምን ተቈጡ? ሕዝቦችስ ስለምን በከንቱ ዶለቱ? የምድር ነገሥታት ተሰልፈው፥ ገዢዎችም በአንድነት ተሰብስበው፥ በጌታና በመሲሑ ላይ ተነሡ።’ “በእርግጥም ሄሮድስና ጴንጤናዊ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው መሲሕ ባደረግኸው በቅዱሱ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሡ፤ እንዲህም የሆነው አንተ አስቀድመህ በገዛ ኀይልህና በገዛ ፈቃድህ ያቀድከውን ለመፈጸም ነው፤
ሐዋርያት ሥራ 4:23-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ውፍደ እፍዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ፤ እንዲህም አሉ “ጌታ ሆይ! አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥ በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ ‘አሕዛብ ለምን አጉረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ፤’ ብለህ የተናገር አምላክ ነህ። በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።