ሐዋርያት ሥራ 4:13-22
ሐዋርያት ሥራ 4:13-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጴጥሮስና ዮሐንስም ግልጥ አድርገው ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፥ ያልተማሩና መጽሐፍን የማያውቁ ሰዎች እንደ ሆኑ ዐውቀው አደነቁ፤ ሁልጊዜም ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ ዐወቁ። ያን የዳነውን ሰውም ከእነርሱ ጋር ቆሞ በአዩት ጊዜ የሚሉትን አጡ። ከሸንጎውም ጥቂት ፈቀቅ አደረጉአቸውና እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። እንዲህም አሉ፥ “እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? እነሆ፥ በእነርሱ የሚደረገው ተአምር በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ዘንድ ታወቀ፤ ግልጥም ሆነ፤ ልንሰውረውም አንችልም። ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ እጅግ እንዳይስፋፋ ዳግመኛ በኢየሱስ ስም ሰውን እንዳያስተምሩ አጠንክረን እንገሥጻቸው።” ጠርተውም፦“ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ አትናገሩ አታስተምሩም” ብለው አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስም እንዲህ ብለው መለሱላቸው፥ “እግዚአብሔርን ያይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም።” እነርሱንም የሚቀጡበት ምክንያት ስለ አጡባቸው ገሥጸው ለቀቁአቸው፤ ስለ ተደረገው ተአምር ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበርና። ይህ የድኅነት ምልክት ለተደረገለት ለዚያ ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበረና።
ሐዋርያት ሥራ 4:13-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰዎቹም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋራ እንደ ነበሩም ተገነዘቡ። የተፈወሰውን ሰው እዚያው ከእነርሱ ጋራ ቆሞ ስላዩት የሚናገሩበትን ሰበብ ዐጡ። ስለዚህ ከሸንጎው እንዲያወጧቸው አዘዙ፤ ከዚያም በአንድነት ተሰብስበው ተመካከሩ፤ እንዲህም ተባባሉ፤ “እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? በኢየሩሳሌም የሚኖር ሁሉ በእነርሱ እጅ የተደረገውን ድንቅ ታምር ዐውቋል፣ ስለዚህ ይህን ማስተባበል አንችልም፤ ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገር ከእንግዲህ በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ፣ እነዚህም ሰዎች ዳግመኛ በዚህ ስም ለማንም እንዳይናገሩ እናስጠንቅቃቸው።” ከጠሯቸውም በኋላ፣ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዟቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፤ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደ ሆነ እስኪ እናንተው ፍረዱ! እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።” እንደ ገና ከዛቱባቸው በኋላም ለቀቋቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ስለ ነበር ሊቀጧቸው አልቻሉም፤ በዚህ ታምር የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበርና።
ሐዋርያት ሥራ 4:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፥ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤ የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ። ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው፦ “በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው” ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” አሉአቸው። እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና። ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና።
ሐዋርያት ሥራ 4:13-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት መናገራቸውን የሸንጎ አባሎች ባዩ ጊዜ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ያውቁ ስለ ነበረ ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩም ዐወቁ፤ የዳነውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ በማየታቸው በእነርሱ ላይ የሚሉትን አጡ። ስለዚህ ከሸንጎው ወዲያ ገለል አደረጉአቸውና በቈይታ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። “እንግዲህ በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን እናድርግ? ይህ ታላቅ ተአምር በእነርሱ እጅ መደረጉ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ታውቆአል፤ ስለዚህ ልንክደው አንችልም። ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ እየተስፋፋ እንዳይሄድ ከእንግዲህ ወዲህ የኢየሱስን ስም በመጥራት ለማንም እንዳይናገሩ፥ እናስጠንቅቃቸው።” ከዚህ በኋላ ጠሩአቸውና የኢየሱስን ስም በመጥራት ከቶ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ በጥብቅ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ተገቢ ነውን? እስቲ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር አንቈጠብም።” የሕዝብ አለቆችና የሸንጎው አባሎች ጴጥሮስንና ዮሐንስን የሚያስቀጣ ምንም ምክንያት ባለማግኘታቸው፥ ሕዝቡንም ስለ ፈሩ እንደገና አስጠንቅቀው ለቀቁአቸው፤ ይህንንም ያደረጉት ሕዝቡ በሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግን ስለ ነበር ነው። በዚህ ተአምር የተፈወሰው ያ ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 4:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፤ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤ የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ። ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው “በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገበኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፤ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደሆነ ቁረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም፤” አሉአቸው። እነርሱም እንደምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና። ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና።