ሐዋርያት ሥራ 28:11-16
ሐዋርያት ሥራ 28:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።
ሐዋርያት ሥራ 28:11-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሦስት ወር በማልታ ከቈየን በኋላ ክረምቱን በደሴቲቱ ባሳለፈው በእስክንድርያው መርከብ ተሳፍረን ተነሣን፤ መርከቡ ዲዮስቆሮስ የተባሉ የመንታ አማልክት አርማ ነበረበት። ወደ ስራኩስ ከተማ በደረስን ጊዜ እዚያ ሦስት ቀን ተቀመጥን። ከዚያም በባሕሩ ዞረን ወደ ሬጊዩም ከተማ ደረስን፤ እዚያ አንድ ቀን ካሳለፍን በኋላ የደቡብ ነፋስ ስለ ነፈሰ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ሄድን። እዚያ ወንድሞችን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሮም ሄድን። በሮም ያሉ ምእመናን ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዮስ ገበያና “ሦስት ማደሪያዎች” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ፤ ጳውሎስ እነርሱን ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነና ተጽናና። ወደ ሮም በገባን ጊዜ ጳውሎስ አንድ የሚጠብቀው ወታደር ተሰጠውና ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።
ሐዋርያት ሥራ 28:11-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሦስት ወር በኋላም በዚያች ደሴት ወደ ከረመችው ወደ እስክንድርያ መርከብ ወጣን፤ በዚያች መርከብ ላይም የዲዮስቆሮስ ምልክት ነበረባት፤ ይኸውም “የመርከበኞች አምላክ” የሚሉት ነው። ከዚያም ሄደን ወደ ሰራኩስ ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን። ከዚያም ሄደን ሬቅዩን ወደምትባል ሀገር ደረስን፤ በማግሥቱም ወጣን፤ ከአንድ ቀንም በኋላ ከጐንዋ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ደረስን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን ተቀበሉን፤ በእነርሱ ዘንድም ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ሄደን ወደ ሮሜ ደረስን። በዚያም ያሉት ወንድሞች ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ፤ አፍዩስ ፋሩስ እስከሚባለው ገበያና እስከ ሦስተኛው ማረፊያ ድረስ ወጥተው ተቀበሉን፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ የመቶ አለቃው እስረኞችን ለሠራዊቱ አለቃ አስረከበ፤ ጳውሎስ ግን ከሚጠብቀው አንድ ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ፈቀደለት።
ሐዋርያት ሥራ 28:11-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሦስት ወር በኋላም፣ በደሴቲቱ ክረምቱን ቆሞ በሰነበተ በአንድ መርከብ ተነሥተን ጕዞ ጀመርን። ይህም መርከብ የእስክንድርያ ሲሆን፣ በላዩ ላይ የመንታ አማልክቱ የዲዮስቆሮስ አርማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስ ከተማ ገብተን ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጥን። ከዚያም በመርከብ ተጕዘን ሬጊዩም ደረስን፤ በማግስቱም የደቡብ ነፋስ ስለ ተነሣ ፑቲዮሉስ የደረስነው በሚቀጥለው ቀን ነበር። በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነርሱም ሰባት ቀን ዐብረናቸው እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሮም ሄድን። በዚያ የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለ ሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ እንዲሁም “ሦስት ማደሪያ” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም። ሮም በደረስን ጊዜም፣ ጳውሎስ ይጠብቀው ከነበረው ወታደር ጋራ ለብቻው በዚያ እንዲቈይ ተፈቀደለት።
ሐዋርያት ሥራ 28:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፤ በእርሱም የዲዮስቆሮስ ዓላማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።