ሐዋርያት ሥራ 28:1-10
ሐዋርያት ሥራ 28:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በደኅና በደረስን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባል ዐወቅን። በዚያ የሚኖሩት አረማውያንም አዘኑልን፤ መልካም ነገርንም አደረጉልን፤ ከቍሩም ጽናትና ከዝናሙ ብዛት የተነሣ እሳት አንድደው እንድንሞቅ ሁላችንንም ሰበሰቡን። ጳውሎስም ብዙ ጭራሮ ሰብስቦ በእሳቱ ላይ ጨመረው፤ እፉኝትም ከእሳቱ ወላፈን የተነሣ ወጥታ ጳውሎስን እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እፉኝቱ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል፤ ከባሕር እንኳ በደኅና ቢወጣም በሕይወት ይኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ አልተወውም” አሉ። ጳውሎስ ግን እጁን አራግፎ እፉኝቱን በእሳት ውስጥ ጣላት፤ ጕዳትም አላገኘውም። እነርሱ ግን ወዲያውኑ የሚያብጥ ወይም ሞቶ የሚወድቅ መስሎአቸው ነበር። እያዩትም ብዙ ሰዓት ቆሙ፤ አንዳችም እንደ አልጐዳው በአዩ ጊዜም፥ “ይህስ አምላክ ነው” ብለው ቃላቸውን ለወጡ። በዚያ ቦታም አጠገብ ስሙን ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴቲቱ አለቃ መሬት ነበር፤ እርሱም ሦስት ቀን ሙሉ በደስታ በቤቱ ተቀብሎ አስተናገደን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ይኖር ነበር፤ ጳውሎስም እርሱ ወዳለበት ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ያደረገውንም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ በዚያች ደሴት ያሉትን ድውያን ሁሉ አመጡለት፤ ፈወሳቸውም። እጅግ ታላቅ ክብርም አከበሩን፤ ከእነርሱም ዘንድ ለመሄድ በተነሣን ጊዜ የሚያስፈልገንን ስንቅ ሰጡን።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በደኅና ወደ ምድር ከደረስን በኋላ፣ ደሴቲቱ መላጥያ ተብላ እንደምትጠራ ተረዳን። የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስም ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጨምር፣ ከሙቀቱ የተነሣ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች። የደሴቲቱ ነዋሪዎች እባብ በእጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነፍስ ገዳይ ነው፤ ከባሕር ቢያመልጥ እንኳ የፍርድ አምላክ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቢቱን ወደ እሳቱ አራገፋት፤ አንዳችም ጕዳት አልደረሰበትም። ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ “ይህስ አምላክ ነው” አሉ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የተባለ የደሴቲቱ አለቃ ርስት የሆነ መሬት ነበረ፤ እርሱም በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በቸርነት አስተናገደን። የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ፣ በደሴቲቱ የነበሩ ሌሎች ሕመምተኞችም እየመጡ ተፈወሱ። እኛንም በብዙ መንገድ አከበሩን፤ በመርከብም ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ጫኑልን።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፦ “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም” አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤ እነርሱም፦ “ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው” ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ፦ “ይህስ አምላክ ነው” ብለው አሳባቸውን ለወጡ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፥ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወደ ምድር በደኅና ከደረስን በኋላ የደረስንባት ደሴት ማልታ የምትባል መሆንዋን ዐወቅን። የዚያች ደሴት ነዋሪዎች የሚያስደንቅ ደግነት አደረጉልን፤ በዚያን ጊዜም ዝናብ ስለ ዘነበና ብርድ ስለ ሆነ እሳት አንድደው ተቀበሉን፤ ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጥል፥ ከሙቀቱ የተነሣ አንድ እባብ ወጣና በእጁ ላይ ተጣብቆ ተንጠለጠለ፤ የማልታ ሰዎች እባብ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥሎ ባዩ ጊዜ “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው! ከባሕሩ ማዕበል በደኅና ቢወጣም ከአምላክ ፍርድ አምልጦ በሕይወት ለመኖር አልቻለም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቡን ወደ እሳቱ አራግፎ ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያገኘው ቀረ። ሰዎቹም “ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል፤ ወይም በድንገት ሞቶ ይወድቃል” በማለት ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተጠባብቀውት ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ አሳባቸውን ለወጡና “ይህስ አምላክ ነው!” አሉ። በዚያ በነበርንበት ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ ገዢ የፑፕልዮስ መሬት ነበር፤ ይህ ሰው በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በጥሩ ሁኔታ አስተናገደን። በዚያን ጊዜ የፑፕልዮስ አባት ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስ ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው። ይህ ከሆነ በኋላ በደሴቲቱ የሚኖሩት ሌሎች በሽተኞች መጡና ተፈወሱ። ሰዎቹ ብዙ ስጦታ አመጡልን፤ አክብሮታቸውንም ገለጡልን፤ በመርከብ ለመሄድ በተነሣንም ጊዜ የሚያስፈልገንን ሁሉ በመርከብ ላይ ጫኑልን።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባለ አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም፤” አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት፤ አንዳችም አልጐዳችውም፤ እነርሱም “ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ “ይህስ አምላክ ነው፤” ብለው አሳባቸውን ለወጡ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፤ እርሱም በእንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፤ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን።