ሐዋርያት ሥራ 26:19-32
ሐዋርያት ሥራ 26:19-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አሁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከሰማይ የተገለጠልኝን ራእይ አልካድሁም። አስቀድሜ በኢየሩሳሌምና በደማስቆ ላሉት፥ ለይሁዳ አውራጃዎችም ሁሉ ነገርኋቸው፤ ለአሕዛብም ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ፥ ለንስሓቸውም የሚገባ ሥራን ይሠሩ ዘንድ አስተማርኋቸው። ሰለዚህም ብቻ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ወደዱ። እግዚአብሔርም አዳነኝና ለታላቁም፥ ለታናሹም እየመሰከርሁ እስከ ዛሬ ደረስሁ፤ ይደረግ ዘንድ ካለው፥ ነቢያት ከተናገሩት፥ ሙሴም ከተናገረው ሌላ ያስተማርሁት የለም። ክርስቶስ እንደሚሞት፥ ከሙታን ተለይቶም አስቀድሞ እንደሚነሣ፥ ለሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ፥ ለመላውም ዓለም እንደሚያበራ።” ይህንም ስለ ራሱ ሲናገር ሀገረ ገዢው ፊስጦስ መለሰ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “ጳውሎስ ሆይ፥ ልታብድ ነውን? ብዙ ትምህርት እኮ ልብን ይነሣል” አለው። ጳውሎስም እንዲህ አለው፥ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ እውነትና የተጣራ ነገርን እናገራለሁ እንጂ ዕብደትስ የለብኝም። በፊቱ ገልጬ የምናገርለት እርሱ ራሱ ንጉሥ አግሪጳ ያውቅልኛል፤ ከዚህም የሚሳተው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ ወደ ጎን የተሰወረ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እነሆ፥ በነቢያት ቃል ታምናለህን? እንደምታምንም አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፥ “አሁንስ ወደ ክርስቲያንነት ልታገባኝ ጥቂት ብቻ ቀርቶሃል” አለው። ጳውሎስም፥ “በጥቂትም ቢሆን፥ በብዙም ቢሆን አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ።” ከዚህም በኋላ ንጉሡ፥ ሀገረ ገዥውም፥ በርኒቄም፥ ሹሞቻቸውም ተነሡ። ለብቻቸውም ገለል ብለው እርስ በርሳቸው እንዲህ ብለው ተነጋገሩ፥ “ይህ ሰው እንዲሞት ወይም እንዲታሰር የሚያበቃ የሠራው በደል የለም።” አግሪጳም ፊስጦስን፥ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ኖሮ ይህ ሰው ይፈታ ዘንድ በተገባ ነበር” አለው።
ሐዋርያት ሥራ 26:19-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እንግዲህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ከሰማይ ለታየኝ ራእይ አልታዘዝ አላልሁም፤ ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ። አይሁድም በመቅደስ ይዘው ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚሁ ምክንያት ነው። የእግዚአብሔር ርዳታ እስከ ዛሬ ስላልተለየኝ፣ እነሆ፤ እዚህ ቆሜ ለትንሹም ለትልቁም እመሰክራለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆናል፣ ይፈጸማል ካሉት በቀር አንዳች ነገር አልተናገርሁም፤ ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።” ፊስጦስም የጳውሎስን ንግግር እዚህ ላይ በማቋረጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አእምሮህን ስተሃል! የትምህርትህም ብዛት አሳብዶሃል” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፤ የምናገረው እውነተኛና ትክክለኛ ነገር እንጂ እብድስ አይደለሁም። ይህን የምናገረውን ነገር ንጉሡ ያውቀዋልና፤ በፊቱ በልበ ሙሉነት እናገራለሁ፤ ደግሞም በድብቅ የተደረገ ነገር ባለመኖሩ፣ ከዚህ ነገር አንድም እንደማይሰወርበት ርግጠኛ ነኝ። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ነቢያትን ታምን የለም ወይ? አዎን፤ እንደምታምን ዐውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፣ “እንዲህ በቀላሉ ክርስቲያን የምታደርገኝ ይመስልሃልን?” አለው። ጳውሎስም፣ “በቀላሉም ሆነ በብዙ፣ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ፣ ከዚህ ከታሰርሁበት ሰንሰለት በቀር፣ እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” አለ። ከዚህ በኋላ ንጉሡም፣ አገረ ገዥውም፣ በርኒቄም፣ ከእነርሱ ጋራ የተቀመጡትም ተነሡ፤ ወጥተውም ሲሄዱ፣ “ይህ ሰው እንኳን ለሞት፣ ለእስራት የሚያበቃው ነገር አላደረገም” ተባባሉ። አግሪጳም ፊስጦስን፣ “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ መልቀቅ ይቻል ነበር” አለው።
ሐዋርያት ሥራ 26:19-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ። ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።” እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ፦ “ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፦ “በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ” አለው። ጳውሎስም፦ “በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራቴ በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ” አለው። ንጉሡም አገረ ገዡም በርኒቄም ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፥ ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው፦ “ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ ብለው ተነጋገሩ። አግሪጳም ፈስጦስን፦ ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር” አለው።
ሐዋርያት ሥራ 26:19-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ስለዚህ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ከሰማይ ለተሰጠኝ ራእይ እምቢተኛ አልሆንኩም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ያሉት ሰዎች፥ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ሁሉ ያሉት እንዲሁም አሕዛብ ጭምር ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ አስተማርኳቸው፤ ንስሓ መግባታቸውን የሚያመለክት ነገር እንዲያደርጉም አስተማርኳቸው። በዚህ ምክንያት አይሁድ በቤተ መቅደስ እንዳለሁ ያዙኝና ሊገድሉኝ ሞከሩ። እስከ ዛሬ ድረስ የእግዚአብሔር ርዳታ አልተለየኝም፤ ስለዚህ ለትንሹም ለትልቁም እየመሰከርኩ እዚህ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ አስቀድመው እንዲህ ይሆናል ያሉትን ከመናገር በቀር ሌላ ምንም አልተናገርኩም። እነርሱም የተናገሩት ‘መሲሕ መከራ ይቀበላል፤ ከሞት በመነሣትም የመጀመሪያ ሆኖ የመዳንን ብርሃን ለእስራኤል ሕዝብና ለአሕዛብ ይገልጣል’ ብለው ነው።” ጳውሎስ ይህን ሲናገር ሳለ ፊስጦስ “ጳውሎስ ሆይ! አሁንስ አበድክ፤ ብዙ መማርህ ወደ እብደት አድርሶሃል!” ሲል ጮኾ ተናገረ። ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እጅግ የተከበርክ ፊስጦስ ሆይ! እውነተኛውንና ትክክለኛውን ነገር እናገራለሁ እንጂ አላበድኩም። በፊቱ በግልጥ የተናገርኩት ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል። ይህም በስውር ያልተደረገ ስለ ሆነ ንጉሡ እንደሚረዳው እርግጠኛ ነኝ። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምን የለምን? እንደምታምን ዐውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፥ “አንተ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው እኮ” አለው። ጳውሎስም “በአጭር ጊዜም ይሁን በረጅም ጊዜ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ ንግግሬን የሰሙ ሁሉ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ እግዚአብሔርን እለምናለሁ!” አለ። ከዚህ በኋላ ንጉሡ፥ ገዢውና በርኒቄ፥ ከእነርሱ ጋር ተቀምጠው የነበሩትም ሰዎች ሁሉ ተነሡ። ከዚያም ወጥተው ሲሄዱ፥ “ይህ ሰው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃው ምንም ነገር አላደረገም” ተባባሉ። አግሪጳም ፊስጦስን “ይህ ሰው ወደ ሮሙ ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ባይል ኖሮ በነጻ በተለቀቀ ነበር” አለ።
ሐዋርያት ሥራ 26:19-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሓ ይገቡ ዘንድና ለንስሓ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ተናገርሁ። ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ሞከሩ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።” እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ “ጳውሎስ ሆይ! አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል፤” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ! የእውነትንና የአምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን “በጥቂት ጊዜ ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ፤” አለው። ጳውሎስም “በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራት በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ፤” አለው። ንጉሡም፥ አገረ ገዢውም፥ በርኒቄና ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፤ ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ፤” ብለው ተነጋገሩ። አግሪጳም ፈስጦስን “ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር፤” አለው።