ሐዋርያት ሥራ 23:1-4
ሐዋርያት ሥራ 23:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጳውሎስም በአደባባዩ ወደአሉት ሰዎች አተኵሮ ተመለከተና፥ “እናንተ ሰዎች ወንድሞች፥ እኔስ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ እግዚአብሔርን ሳገለግል ኑሬአለሁ” አላቸው። ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ግን ጳውሎስን አፉን እንዲመቱት በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። ጳውሎስም መልሶ፥ “አንተ የተለሰነ ግድግዳ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዝዛለህን? እግዚአብሔር በቍጣው መቅሠፍት ይመታሃል” አለው። በአጠገቡ ቆመው የነበሩትም ጳውሎስን፥ “እግዚአብሔር የሾመውን ሊቀ ካህናት እንዴት ትሳደባለህ?” አሉት።
ሐዋርያት ሥራ 23:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጳውሎስም ወደ ሸንጎው ትኵር ብሎ በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ሕሊና ተመላልሻለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ። ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው። ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።
ሐዋርያት ሥራ 23:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ፦ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ አለ። ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ፦ አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን? አለው። በአጠገቡ የቆሙትም፦ የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን? አሉት።
ሐዋርያት ሥራ 23:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጳውሎስም ሸንጎውን ትኲር ብሎ ተመለከተና “ወንድሞቼ ሆይ! እስከ ዛሬ ድረስ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የኖርኩት በመልካም ኅሊና ነው” አለ። የካህናት አለቃው ሐናንያ ግን ጳውሎስን አፉን እንዲመቱት በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አዘዘ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ሐናንያን፥ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳን የምትመስል! አንተንም እግዚአብሔር ይመታሃል! በሕግ መሠረት የእኔን ጉዳይ ልትፈርድ ተቀምጠህ ሳለ ያለ ሕግ እንዲመቱኝ ታዛለህን?” እዚያ የነበሩ ሰዎች ጳውሎስን “የእግዚአብሔርን የካህናት አለቃ ትሳደባለህን?” አሉት።
ሐዋርያት ሥራ 23:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጳውሎስም ሸንጎውን ትኩር ብሎ ተመልክቶ “ወንድሞች ሆይ! እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ፤” አለ። ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ! እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?” አለው። በአጠገቡ የቆሙትም “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን?” አሉት።