ሐዋርያት ሥራ 22:24-30
ሐዋርያት ሥራ 22:24-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሻለቃው የሚጮሁበት ስለ ምን እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ወደ ወታደሮች ሰፈር እንዲያገቡትና እየገረፉ የሠራውን እንዲመረምሩት አዘዘ። ሊገርፉትም በአጋደሙት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የነበረውን የመቶ አለቃ፥ “የሮማን ሰው ያለ ፍርድ ልትገርፉ ይገባችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃውም ይህን በሰማ ጊዜ፥ ወደ ሻለቃው ሄደና፥ “ይህ ሰው ሮማዊ ነው፥ የምታደርገውን ዕወቅ” ብሎ ነገረው። የሻለቃውም ወደ እርሱ ቀርቦ፥ “አንተ ሮማዊ ነህን? እስኪ ንገረኝ” አለው፤ ጳውሎስም፥ “አዎን” አለው። የሻለቃውም መልሶ፥ “እኔ ይህችን ዜግነት ያገኘኋት ብዙ ገንዘብ ሰጥቼ ነው” አለው፤ ጳውሎስም፥ “እኔማ የተወለድሁ በዚያው ነው” አለው። ከዚህም በኋላ ይመረምሩት ዘንድ የሚሹት ተዉት፤ የሻለቃውም ሮማዊ መሆኑን በዐወቀ ጊዜ“ ለምን አሰርሁት?” ብሎ ፈራ። በማግሥቱም የሻለቃው አይሁድ የሚከሱት ስለ ምን እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ወደደና ከእስራቱ ፈታው፤ ሊቃነ ካህናቱና ሸንጎውም ሁሉ እንዲመጡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አምጥቶ በፊታቸው አቆመው።
ሐዋርያት ሥራ 22:24-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የጦር አዛዡ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈር እንዲያስገቡትና ሕዝቡ ለምን እንዲህ እንደሚጮኹበት እየተገረፈ እንዲመረመር ትእዛዝ ሰጠ። ጳውሎስም በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲሉ፣ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ፣ “አንድን የሮም ዜጋ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃውም ይህን ሲሰማ፣ ወደ ጦር አዛዡ ቀርቦ፣ “ምን እያደረግህ እንደ ሆነ ዐውቀሃል? ሰውየው እኮ ሮማዊ ነው” አለው። አዛዡም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ፣ “አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ፤ ሮማዊ ነህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፤ ነኝ” አለው። አዛዡም መልሶ፣ “እኔ ይህን ዜግነት ያገኘሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለ። ጳውሎስም፣ “እኔ ግን ከተወለድሁ ጀምሮ ሮማዊ ነኝ” አለው። ስለዚህ እነዚያ ሊመረምሩት ያሰቡት ሰዎች ወዲያው ከርሱ ሸሹ፤ የጦር አዛዡም የሮም ዜጋ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ በሰንሰለት አስሮት ስለ ነበር ፈራ። በማግስቱም የጦር አዛዡ፣ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ስለ ፈለገ ፈታው፤ ከዚያም የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባላት በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።
ሐዋርያት ሥራ 22:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፥ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ፦ እየገረፋችሁ መርምሩት አላቸው። በጠፈርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ፦ የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን? አለው። የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ፦ ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ ብሎ ነገረው። የሻለቃውም ቀርቦ፦ አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ አለው፤ እርሱም፦ አዎን አለ። የሻለቃውም መልሶ፦ እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት አለ። ጳውሎስም፦ እኔ ግን በእርስዋ ተወለድሁ አለ። ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፥ አሳስሮት ነበርና። በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደ ሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፥ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፥ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።
ሐዋርያት ሥራ 22:24-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አዛዡ ይህን ባየ ጊዜ ጳውሎስን ወደ ወታደሮች ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ፤ ሕዝቡ በእርሱ ላይ ስለምን ይህን ያኽል እንደሚጮኹ ለማወቅም እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ። ነገር ግን በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲዘጋጁ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ “የሮም ዜግነት ያለውን ሰው ያለ ፍርድ ልትገርፉት ተፈቅዶላችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃው ይህን በሰማ ጊዜ ወደ አዛዡ ሄደና “ምን ልታደርግ ነው? ይህ ሰው እኮ የሮም ዜጋ ነው!” አለው። ስለዚህ አዛዡ ወደ ጳውሎስ ቀረብ አለና “እስቲ ንገረኝ፤ አንተ የሮም ዜጋ ነህን?” አለው፤ እርሱም “አዎ፥ ነኝ፤” አለ። አዛዡም “እኔ ይህን ዜግነት የገዛሁት በብዙ ገንዘብ ነው” አለ፤ ጳውሎስም “እኔ ግን በሮም ዜግነት ተወልጄአለሁ” አለ። ስለዚህ እነዚያ ሊመረምሩት ተዘጋጅተው የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእርሱ ራቁ፤ አዛዡም የሮም ዜጋ የሆነውን ሰው በሰንሰለት ማሰሩን በተገነዘበ ጊዜ ፈራ። በማግስቱ አዛዡ፥ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ፈለገ፤ ስለዚህ የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም ከእስራቱ ፈቶ ወሰደና በፊታቸው አቀረበው።
ሐዋርያት ሥራ 22:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፤ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ “እየገረፋችሁ መርምሩት፤” አላቸው። በጠፈርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ “የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ “ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ፤” ብሎ ነገረው። የሻለቃውም ቀርቦ “አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ፤” አለው፤ እርሱም “አዎን” አለ። የሻለቃውም መልሶ “እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት፤” አለ። ጳውሎስም “እኔ ግን በእርሷ ተወለድሁ፤” አለ። ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፤ አሳስሮት ነበርና። በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፤ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።