ሐዋርያት ሥራ 20:18-24
ሐዋርያት ሥራ 20:18-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፥ “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ዘንድ እንደ ተቀመጥሁ እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔርን እያገለገልሁ በፍጹም መከራና በልቅሶ ከአይሁድም ሴራ የተነሣ በደረሰብኝ ፈተና እየተጋደልሁ፥ በጉባኤም ሆነ በቤት ስነግራችሁና ሳስተምራችሁ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳን አላስቀረሁባችሁም። ወደ እግዚአብሔር መመለስንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለአረማውያን እየመሰከርሁ፤ አሁንም እነሆ በመንፈስ ታሥሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ ነገር ግን በዚያ የሚያገኘኝን አላውቅም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ በየከተማው መከራና እስራት ይጠብቅሃል ብሎ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ወንጌል እንዳስተምር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልሁትን ሩጫዬን እንድጨርስና መልእክቴንም እንድፈጽም ነው እንጂ ለሰውነቴ ምንም አላስብላትም።
ሐዋርያት ሥራ 20:18-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በመጡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ወደ እስያ አውራጃ ከገባሁባት ከመጀመሪያዋ ዕለት አንሥቶ ዘወትር ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ ታውቃላችሁ። ምንም እንኳ ከአይሁድ ሤራ የተነሣ መከራ ቢያደርሱብኝም፣ ጌታን በታላቅ ትሕትናና በእንባ ከማገልገል አልተቈጠብሁም፤ በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም። በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ፣ ለአይሁድም ለግሪክ ሰዎችም አጥብቄ መስክሬላቸዋለሁ። “አሁንም እዚያ ስደርስ የሚደርስብኝን ባላውቅም፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው። ነገር ግን በምሄድባቸው ከተሞች ሁሉ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።
ሐዋርያት ሥራ 20:18-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም። አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 20:18-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወደ እርሱ በመጡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ እስያ ከገባሁበት ቀን ጀምሮ ዘወትር ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርኩ እናንተ ታውቃላችሁ፤ በአይሁድ ሤራ ምክንያት መከራ ቢደርስብኝም እንኳ በፍጹም ትሕትናና በእንባ ጌታን አገለግል ነበር። በአደባባይም ሆነ በየቤታችሁ ሳስተምራችሁ የሚጠቅማችሁን ሁሉ ነገርኳችሁ እንጂ፥ ምንም ነገር አላስቀረሁባችሁም። አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አስጠነቀቅኋቸው። አሁንም እዚያ ስደርስ ምን እንደሚደርስብኝ ሳላውቅ በመንፈስ ቅዱስ ታዝዤ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዴ ነው። ይሁን እንጂ በየከተማው እስራትና ችግር እንደሚገጥመኝ መንፈስ ቅዱስ ነግሮኛል። የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል ለማስተማር ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልኩትን የማገልገል ግዴታ ከፈጸምኩ ለሕይወቴ ዋጋ አልሰጠውም፤ ለነፍሴም አልሳሳለትም።
ሐዋርያት ሥራ 20:18-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሤራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ በአደባባይም ሆነ በየቤታችሁ ሳስተምራችሁ የሚጠቅማችሁን ሁሉ ነገርኳችሁ እንጂ፥ ምንም ነገር አላስቀረሁባችሁም። አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አስጠነቀቅኋቸው። አሁንም እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ‘እስራትና መከራ ይቆይሃል፤’ ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።