ሐዋርያት ሥራ 2:5-11
ሐዋርያት ሥራ 2:5-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሰማይ በታች ካሉ አሕዛብ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደጋግ የአይሁድ ሰዎች ነበሩ። ይህንም ቃል ሲናገሩ ሰምተው ሁሉም ደንግጠው ተሰበሰቡ፤ ሁሉም በየሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋልና የሚሉትን አጡ። ተገረሙ፤ አደነቁም፥ እንዲህም አሉ፥ “እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንግዲህ በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንዴት እንሰማቸዋለን? እኛ በተወለድንበት በጳርቴ፥ በሜድ፥ በኢላሜጤ፥ በሁለቱ ወንዞች መካከል፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስና በእስያ፥ በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብፅ፥ በሊብያ አውራጃ፥ በቀርኔን የምንኖር፥ ከሮሜም የመጣን አይሁድ፥ መጻተኞችም፥ ከቀርጤስና ከዐረብም የመጣን፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ጌትነት በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።”
ሐዋርያት ሥራ 2:5-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ። ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤ በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድንበት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው? እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጰዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣ በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!”
ሐዋርያት ሥራ 2:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ “እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋ ችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።”
ሐዋርያት ሥራ 2:5-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዓለም ካሉት አገሮች ሁሉ የመጡ፥ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። ይህንንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ በየቋንቋቸውም ሲናገሩ ስለ ሰሙአቸው ተደነቁ። በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ እንዲህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? ታዲያ፥ እኛ በየትውልድ አገራችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ነው? እኛ በጳርቴ፥ በሜድ፥ በዔላም፥ በመስጴጦምያ፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስ፥ በእስያ፥ በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብጽ፥ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር ነን፤ ከሮምም የመጣን አይሁድና ወደ አይሁድነትም የገባን እንገኛለን፤ እንዲሁም የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ይገኛሉ፤ እነሆ፥ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማለን!”
ሐዋርያት ሥራ 2:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ “እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋ ችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በመስጴጦምያም በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።”