ሐዋርያት ሥራ 2:41-47
ሐዋርያት ሥራ 2:41-47 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቃሉንም ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚችም ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ተጨመሩ። በሐዋርያት ትምህርትና በአንድነት ማዕድን በመባረክ፥ በጸሎትም ጸንተው ይኖሩ ነበር። ሰው ሁሉ ፈራቸው፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ተአምራትና ድንቅ ሥራ ይደረግ ነበር። ያመኑትም ሁሉ በአንድነት ይኖሩ ነበር፤ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበር። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ እንደሚያሻው ይሰጡ ነበር። ሁልጊዜም አንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደስ ያገለግሉ ነበር፤ በቤትም ኅብስትን ይቈርሱ ነበር፤ በደስታና በልብ ቅንንነትም ምግባቸውን ይመገቡ ነበር። እግዚአብሔርንም ያመሰግኑ ነበር፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ መወደድ ነበራቸው፤ እግዚአብሔርም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 2:41-47 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ፤ በዚያ ቀን ሦስት ሺሕ ያህል ሰዎች በቍጥራቸው ላይ ተጨመሩ። እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር። በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ታምራት ይደረግ ስለ ነበር፣ ሰው ሁሉ ፍርሀት ዐደረበት። ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ። ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር። በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 2:41-47 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 2:41-47 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእነርሱ ብዙዎቹ ቃሉን ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያኽሉ አማኞች ተጨመሩ። እነርሱም የሐዋርያትን ትምህርት በመስማት፥ በኅብረት በመኖር፥ ማዕድን አብሮ በመብላትና በጸሎት ይተጉ ነበር። በዚያን ጊዜ በሐዋርያት እጅ ብዙ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች ይደረጉ ስለ ነበር በሁሉም ላይ ፍርሀት ዐደረባቸው። አማኞች ሁሉ በአንድነት አብረው ይኖሩ ነበር፤ ያላቸውም ነገር ሁሉ የጋራ ነበር። ዕርሻቸውንና ሀብታቸውን እየሸጡ ገንዘቡን ለእያንዳንዱ እንደሚያስፈልገው ያከፋፍሉ ነበር። በየቀኑ በቤተ መቅደስ በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር፤ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በጥሩ ልብ ይመገቡ ነበር፤ ጌታንም ያመሰግኑ ነበር፤ ሰውም ሁሉ ያከብራቸው ነበር፤ እግዚአብሔርም የሚድኑትን ሰዎች በየቀኑ ወደ ማኅበራቸው ይጨምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 2:41-47 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።