ሐዋርያት ሥራ 2:14-21
ሐዋርያት ሥራ 2:14-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጴጥሮስም ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “እናንተ የአይሁድ ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ ይህን ዕወቁ፤ ቃሌንም ስሙ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና። ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። በኋለኛዪቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል እግዚአብሔር፦ ሥጋን በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁ ራእይን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ። በወንዶችና በሴቶች ባሮች ላይም ያንጊዜ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። በላይ በሰማይ ተአምራትን፥ በታች በምድርም ምልክቶችን፥ ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ። የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።
ሐዋርያት ሥራ 2:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋራ ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንተ የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ። ጊዜው ገና ከጧቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም! ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሮቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ። በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣ አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ ይሆናል። ታላቁና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’
ሐዋርያት ሥራ 2:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ “አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፦ እግዚአብሔር ይላል፦ ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።’
ሐዋርያት ሥራ 2:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ምድር ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፥ ይህን የሆነውን ነገር ለማወቅ ንግግሬን አዳምጡ፤ ከጠዋቱ ገና ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ እናንተ እንዳሰባችሁት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም። ነገር ግን ይህ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ‘እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል፤ መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። እንዲሁም በእነዚያ ቀኖች በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ። በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮችን፥ በታች በምድር ተአምራትን አሳያለሁ፤ ደም፥ እሳት፥ የጢስ ጭጋግም ይታያል። ታላቁና አስገራሚው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፥ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ትመስላለች። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’
ሐዋርያት ሥራ 2:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው “የይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፤ “እግዚአብሔር ይላል ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።’