ሐዋርያት ሥራ 14:1-7
ሐዋርያት ሥራ 14:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በኢቆንዮንም ጳውሎስና በርናባስ ዐብረው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ በዚያም በሚገባ ስላስተማሩ፣ ከአይሁድም ከግሪክም እጅግ ብዙ ሰዎች አመኑ። ያላመኑት አይሁድ ግን፣ አሕዛብን አነሣሥተው ወንድሞችን እንዲጠሉ አደረጓቸው። ጳውሎስና በርናባስም ስለ ጌታ በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ እዚያው ቈዩ፤ ጌታም የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግጥላቸው ነበር። የከተማውም ሕዝብ ተከፋፈለ፤ ገሚሱ ከአይሁድ ጋራ፣ ገሚሱም ከሐዋርያት ጋራ ሆነ። በዚህ ጊዜ አሕዛብና አይሁድ ከመሪዎቻቸው ጋራ ተባብረው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊያስወግሯቸው ሞከሩ። እነርሱ ግን ይህን እንዳወቁ ልስጥራንና ደርቤን ወደተባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን መስበክ ቀጠሉ።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢቆንዮን በምትባል ከተማም እንደ ሁልጊዜው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ ከአይሁድና ከአረማውያንም ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። ማመንን እንቢ ያሉት የአይሁድ ወገኖች ግን የአሕዝብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም። በጌታም ፊት ደፍረው እያስተማሩ፥ እርሱም የጸጋውን ቃል ምስክር እያሳየላቸው፥ በእጃቸውም ድንቅ ሥራና ተአምራትን እያደረገላቸው ብዙ ወራት ኖሩ። የከተማውም ሕዝብ ሁሉ ተለያዩ፤ እኩሌቶቹ ወደ አይሁድ፥ እኩሌቶቹም ወደ ሐዋርያት ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላትዋቸውና በድንጋይ ሊደበድቧቸው ተነሡ። ሐዋርያትም ይህን ዐውቀው ወደ ሊቃኦንያ ከተሞች ወደ ልስጥራንና ወደ ደርቤን፥ ወደየአውራጃውም ሸሹ። በዚያም ወንጌልን ሰበኩ።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ አስከፉም። ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኵሌቶቹ ከአይሁድ እኵሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ፤ በዚያም ብዙ አይሁድና ከአሕዛብ እጅግ ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን አሕዛብን አነሣሥተው በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር አደረጉ። ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ የጌታን ነገር በድፍረት እየተናገሩ እዚያ ብዙ ጊዜ ቈዩ፤ ጌታም ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በእነርሱ እጅ እንዲደረጉ ሥልጣን በመስጠት፥ የእርሱ የጸጋ ቃል እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥ ነበር። የከተማው ነዋሪዎች ግን፥ በሁለት ተከፍለው ግማሹ ከአይሁድ ጋር ግማሹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ከአለቆቻቸው ጋር ሆነው ጳውሎስንና በርናባስን ሊያንገላቱአቸውና በድንጋይ ሊወግሩአቸው ፈለጉ፤ ጳውሎስና በርናባስ ይህን ባወቁ ጊዜ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሽተው ሄዱ። እዚያም ወንጌልን ሰበኩ።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም። ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኩሌቶቹ ከአይሁድ እኩሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር።