ሐዋርያት ሥራ 14:1-3
ሐዋርያት ሥራ 14:1-3 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢቆንዮን በምትባል ከተማም እንደ ሁልጊዜው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ ከአይሁድና ከአረማውያንም ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። ማመንን እንቢ ያሉት የአይሁድ ወገኖች ግን የአሕዝብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም። በጌታም ፊት ደፍረው እያስተማሩ፥ እርሱም የጸጋውን ቃል ምስክር እያሳየላቸው፥ በእጃቸውም ድንቅ ሥራና ተአምራትን እያደረገላቸው ብዙ ወራት ኖሩ።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በኢቆንዮንም ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ በዚያም በሚገባ ስላስተማሩ፣ ከአይሁድም ከግሪክም እጅግ ብዙ ሰዎች አመኑ። ያላመኑት አይሁድ ግን፣ አሕዛብን አነሣሥተው ወንድሞችን እንዲጠሉ አደረጓቸው። ጳውሎስና በርናባስም ስለ ጌታ በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ እዚያው ቈዩ፤ ጌታም የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግጥላቸው ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ አስከፉም። ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ።
ሐዋርያት ሥራ 14:1-3 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ፤ በዚያም ብዙ አይሁድና ከአሕዛብ እጅግ ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን አሕዛብን አነሣሥተው በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር አደረጉ። ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ የጌታን ነገር በድፍረት እየተናገሩ እዚያ ብዙ ጊዜ ቈዩ፤ ጌታም ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በእነርሱ እጅ እንዲደረጉ ሥልጣን በመስጠት፥ የእርሱ የጸጋ ቃል እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥ ነበር።