ሐዋርያት ሥራ 13:24-52
ሐዋርያት ሥራ 13:24-52 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱ ከመምጣቱ አስቀድሞ ዮሐንስ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሓ ጥምቀትን ሰበከላቸው። ዮሐንስም መልእክቱን ሲፈጽም እንዲህ አላቸው፦ ‘እኔን ለምን ትጠራጠሩኛላችሁ? እርሱን አይደለሁም፤ የጫማውን ማዘቢያ ከእግሩ ልፈታ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ እነሆ፥ ይመጣል።’ “እናንተ ከአብርሃም ወገን የተወለዳችሁ ወንድሞቻችን እግዚአብሔርንም የምትፈሩ፥ ይህ የሕይወት ቃል ለእናንተ ተልኮአል። በኢየሩሳሌም የሚኖሩና አለቆቻቸው ግን እርሱን አላወቁም፤ የነቢያት መጻሕፍትንም በየሰንበቱ ሁሉ ሲያነቡ አላስተዋሉትም፤ ነገር ግን ይሙት በቃ ፈረዱበት፥ ስለ እርሱ የተጻፈውንም ሁሉ ፈጸሙበት። ለሞትም የሚያበቃ ምንም በደል ባላገኙበት ጊዜ እንዲገድለው ጲላጦስን ለመኑት። ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከመስቀል አውርደው በመቃብር ቀበሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን ለይቶ አስነሣው። ከተነሣም በኋላ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም አብረውት ለወጡት ብዙ ቀን ተገለጠላቸው። እነርሱም በሕዝብ ዘንድ ምስክሮች ሆኑት። “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ያናገረላቸውን ተስፋ እንነግራችኋለን። በሁለተኛው መዝሙር፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ እንዳለ ኢየሱስን አስነሥቶ ተስፋውን ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአል። መፍረስ መበስበስንም እንዳያይ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው እንዲህ አለ፦ ‘የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ። በሌላ ስፍራም እንዲህ ይላል፦ ‘ጻድቅህን መፍረስ መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።’ ዳዊት ግን በዘመኑ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ አገልግሎአል፤ እንደ አባቶቹ ሞተ፥ ተቀበረም፤ መፍረስ መበስበስንም አይቶአል። ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መፍረስ መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞቻችን፥ በእርሱ ኀጢአታችሁ እንደሚሰረይላችሁ ተስፋ የሰጣችሁን ዕወቁ። ከሁሉም ይልቅ በሙሴ ሕግ መጽደቅ የተሳናችሁ ናችሁ። በእርሱ ግን ያመነ ሁሉ ይጸድቃል። እንግዲህ እንዲህ የሚለው የነቢያት ቃል እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። ‘እነሆ፥ እናንተ የምታቃልሉ፥ እዩ፤ ተደነቁም፤ ያለዚያ ግን ትጠፋላችሁ፤ ማንም ቢነግራችሁ የማታምኑትን ሥራ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ” ከምኵራብም ከወጡ በኋላ ይህን ነገር በሁለተኛው ሰንበት እንዲነግሩአቸው ማለዱአቸው። ጉባኤውም በተፈታ ጊዜ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ከተመለሱት ከደጋጉ ሰዎች ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ጸጋ ይድኑ ዘንድ እያስረዱ ነገሯቸው። በሁለተኛው ሰንበትም የከተማው ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም የተሰበሰበውን ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቀኑባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ደፍረው እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ አስቀድሞ ልንነግራችሁ ይገባል፤ እንቢ ብትሉና ራሳችሁን ለዘለዓለም ሕይወት የተዘጋጀ ባታደርጉ ግን እነሆ፥ ወደ አሕዛብ እንመለሳለን። እግዚአብሔር፦ እስከ ምድር ዳርቻ ላሉት ሁሉ መድኀኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ” ብሎ አዝዞናልና። አሕዛብም ይህን ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ። የእግዚአብሔርም ቃል በሀገሩ ሁሉ ተዳረሰ። አይሁድ ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ የከበሩ ሴቶችንና የከተማውን ሽማግሌዎች አነሳሡአቸው፤ በጳውሎስና በበርናባስ ላይም ስደትን አስነሡ፤ ከሀገራቸውም አባረሩአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። መንፈስ ቅዱስም በደቀ መዛሙርት ላይ ሞላ፤ ደስም አላቸው።
ሐዋርያት ሥራ 13:24-52 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር። ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ መፍታት የማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር። “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው። የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በርሱ ፈረዱበት። ለሞት የሚያበቃው አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ ጲላጦስ የሞት ፍርድ እንዲፈርድበት ተማጸኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከተሰቀለበት ዕንጨት አውርደው በመቃብር ውስጥ አስገቡት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው። ከገሊላ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋራ ለነበሩትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው። “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶች ቃል የገባውን የምሥራች ቃል ለእናንተ እንሰብካለን፤ ኢየሱስንም ከሙታን በማስነሣቱ ለእነርሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሟል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር እንዲህ ብሎ ተጽፏል፤ “ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’ ደግሞም፣ እርሱ እንዳልበሰበሰና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ለማረጋገጥ እንዲህ ብሏል፤ “ ‘የተቀደሰውንና የታመነውን፣ የዳዊትን በረከት እሰጣችኋለሁ።’ ስለዚህ በሌላም ስፍራ፣ “ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ይላል። “ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፍቷል፤ ከአባቶቹም ጋራ ተቀብሮ ሥጋው በስብሷል። እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣው እርሱ ግን መበስበስን አላየም። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “ ‘እናንተ ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም ቢነግራችሁ እንኳን፣ የማታምኑትን ነገር፣ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ” ጳውሎስና በርናባስ ከምኵራብ ሲወጡ፣ ሰዎቹ ስለዚሁ ነገር በሚቀጥለው ሰንበት እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። ጉባኤው ከተበተነ በኋላም፣ ብዙ አይሁድና ወደ ይሁዲ ሃይማኖት ገብተው በመንፈሳዊ ነገር የበረቱ ሰዎች፣ ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነርሱም አነጋገሯቸው፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ መከሯቸው። በሚቀጥለውም ሰንበት የከተማው ሕዝብ፣ ጥቂቱ ሰው ብቻ ሲቀር፣ በሙሉ የጌታን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ፣ በቅናት ተሞሉ፤ የጳውሎስንም ንግግር እየተቃወሙ ይሰድቡት ነበር። ጳውሎስና በርናባስም በድፍረት እንዲህ አሏቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገር አለበት፤ እናንተ ግን ናቃችሁት፤ በዚህም የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ ስለ ፈረዳችሁ፣ እኛም ወደ አሕዛብ ዞር ለማለት እንገደዳለን። ደግሞም ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞናል፤ “ ‘ድነትን እስከ ምድር ዳርቻ ታደርስ ዘንድ፣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ።’ ” አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ለጌታም ቃል ክብርን ሰጡ፤ ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትም ሁሉ አመኑ። የጌታም ቃል በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን በመንፈሳዊ ነገር የተጉትንና የከበሩትን ሴቶች፣ እንዲሁም የከተማውን ታላላቅ ወንዶች ቀስቅሰው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደትን አስነሡ፤ ከአገራቸውም አስወጧቸው። ጳውሎስና በርናባስም ለማስጠንቀቂያ እንዲሆን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።
ሐዋርያት ሥራ 13:24-52 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ ‘እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር። እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፦ ‘አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ፦ ‘የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል።’ ደግሞ በሌላ ስፍራ፦ ‘ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም’ ይላልና። ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን። እንግዲህ፦ እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።” በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፦ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ ጌታ፦ ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ ብሎ አዞናልና” አሉ። አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።
ሐዋርያት ሥራ 13:24-52 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስ ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ‘እኔ ማን መሰልኳችሁ? እኔ መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል’ ይል ነበር። “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞችና እናንተም እግዚአብሔርን የምትፈሩ አሕዛብ! ይህ የመዳን ቃል የተላከው ለእኛ ነው። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላወቁም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት መጻሕፍት ባለማስተዋላቸው በእርሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ትንቢቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል። ምንም እንኳ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙበት እርሱን እንዲገድልላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙበት በኋላ ከመስቀል አውርደው ቀበሩት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው። ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ለመጡትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን በሕዝብ ፊት ምስክሮቹ ናቸው። እኛም ይዘንላችሁ የመጣነው እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በተስፋ የሰጠውን መልካም ዜና ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተስፋ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታል፤ ይህም በሁለተኛው መዝሙር፥ ‘አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። መበስበስ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣው ለማስረዳት፥ ‘ቅዱሱን የታመነ በረከትን ለዳዊት የተሰጠውን ተስፋ እሰጣችኋለሁ’ ብሎ ተናግሮአል። ደግሞም በሌላ መዝሙር፥ ‘ቅዱሱ ልጅህ መበስበስ እንዲደርስበት አታደርገውም’ ይላል። ነገር ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን አገልግሎቱን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከፈጸመ በኋላ ሞቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮአል፤ መበስበስም ደርሶበታል። እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣው ግን መበስበስ አልደረሰበትም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ ነጻ ሊያወጣው ከማይችለው ኃጢአት ሁሉ ነጻ ይወጣል። ስለዚህ በነቢያት እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ‘እናንተ ፌዘኞች እዩ! ተደነቁ! ጥፉም! ማንም ሰው ቢያወራላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁ።’ ” ጳውሎስና በርናባስ ከምኲራብ ሲወጡ ይህንኑ ነገር በሚመጣው ሰንበት እንደገና እንዲነግሩአቸው ሰዎቹ ለመኑአቸው። የምኲራቡ ጉባኤ በተበተነ ጊዜ ብዙ የአይሁድ ወገኖችና ወደ አይሁድ እምነት ገብተው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ ጳውሎስና በርናባስም ሰዎቹን በማስተማር በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አሳሰቡአቸው። በሚቀጥለው ሰንበት ከከተማው ነዋሪዎች አብዛኞቻቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ፤ አይሁድ የሕዝቡን ብዛት ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞሉ፤ ንግግሩንም እየተቃወሙ ጳውሎስን ሰደቡት፤ ጳውሎስና በርናባስ ግን እንዲህ ሲሉ በድፍረት ተናገሩ፤ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ እንዲነገር አስፈላጊ ነው፤ እናንተ አንቀበልም ካላችሁና የዘለዓለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን እነሆ፥ እኛ ዞር ብለን ወደ አሕዛብ እንሄዳለን። ይህንንም የምናደርገው ጌታ፦ ‘መዳንን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንድታመጣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ በማለት ስላዘዘን ነው።” አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ የጌታንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡትም ሁሉ አመኑ። የጌታም ቃል በዚያ አገር ሁሉ ተስፋፋ። የአይሁድ መሪዎች ግን የአይሁድ እምነት ተከታዮች የሆኑትን ሀብታሞች ሴቶችና የከተማውን ታላላቅ ሰዎች አሳድመው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት እንዲነሣ አደረጉ፤ ከአገራቸውም አስወጡአቸው። ጳውሎስና በርናባስም በእነርሱ ላይ የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።
ሐዋርያት ሥራ 13:24-52 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ ‘እኔ ማን እንደሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤’ ይል ነበር።” እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ! ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ “የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ፤” ብሏል። ደግሞ በሌላ ስፍራ “ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም፤” ይላልና። ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “እናንተ የምትንቁ፥ ተመልከቱ፤ ተደነቁም፤ ጥፉም፤ ማንም ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና፤” ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘለዓለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ ጌታ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ፤” ብሎ አዞናልና፤ አሉ። አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፤ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።