ሐዋርያት ሥራ 13:1-23
ሐዋርያት ሥራ 13:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በአንጾኪያ በነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉቅዮስ፥ ከአራተኛው ክፍል ገዢ ከሄሮድስ ጋር ያደገው ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ፥ ሲጾሙም መንፈስ ቅዱስ፥ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አላቸው። ያንጊዜም ከጾሙና ከጸለዩ፥ እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ከጫኑባቸው በኋላ ላኩአቸው። ከመንፈስ ቅዱስም ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ወደ ሰልሚና ሀገርም ገብተው በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስም እየአገለገላቸው ከእነርሱ ጋር ነበር። በደሴቲቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፤ በዚያም አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሐሰተኛ ነቢይና አስማተኛ ሰው አገኙ፤ ስሙም በርያሱስ ይባላል። እርሱም ብልህ ሰው በሆነ ሰርግዮስ ጳውሎስ በሚባል አገረ ገዢ ዘንድ ይኖር ነበረ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሊሰማ ወድዶ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠራቸው። አስማተኛው ኤልማስም የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበረና፥ ገዥውን ከማመን ሊከለክለው ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ በተባለው በሳውል ላይም ቅዱስ መንፈስ ሞላበት፤ አተኵሮም ተመለከተው። እንዲህም አለው፥ “ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ ማጣመምህን ትተው ዘንድ እንቢ አልህን? እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ። አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ። ከዚህም በኋላ እነ ጳውሎስ ከጳፉ ከተማ ወጥተው ሄዱና የጵንፍልያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ ጰርጌን ገቡ፤ ዮሐንስ ግን ትቶአቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱም ከጰርጌን አልፈው የጲስድያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ኦሪትንና ነቢያትን ካነበቡ በኋላም የምኵራቡ አለቆች፥ “እናንተ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለሕዝብ ሊነገር የሚገባው የምክር ቃል እንደ አላችሁ ተናገሩ” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሥቶ ዝም እንዲሉ አዘዘና እንዲህ አላቸው፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርንም የምትፈሩ ሁሉ፥ ስሙ። የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ ወገኖቹንም በተሰደዱበት በምድረ ግብፅ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከዚያም ከፍ ባለ ክንዱ አወጣቸው። አርባ ዘመንም በምድረ በዳ መገባቸው። ሰባቱን የከነዓንን አሕዛብ አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ አራት መቶ አምሳ ዓመት እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሾመላቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ነገድ የተወለደውን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት አነገሠላቸው። እርሱንም ሻረው፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ‘የእሴይን ልጅ ዳዊትን ፈቃዴን ሁሉ የሚፈጽም እንደ ልቤም የታመነ ሰው ሆኖ አገኘሁት’ ብሎ መሰከረለት። እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጣቸው ከዳዊት ዘር ለእስራኤል መድኀኒት አድርጎ ኢየሱስን አመጣላቸው።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስ ዐብሮ አደግ የነበረው ምናሔ እና ሳውል ነበሩ። እነዚህም ጌታን እያመለኩና እየጾሙ ሳሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። እነርሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጭነው አሰናበቷቸው። በርናባስና ሳውልም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ስልማና በደረሱም ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ ዮሐንስም እንደ አገልጋያቸው ዐብሯቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት ከዳር እስከ ዳር አቋርጠው ጳፉ በደረሱ ጊዜ፣ በርያሱስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ አገኙ፤ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ አገረ ገዥ ጋራ ነበረ። ይህ አገረ ገዥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን አስጠራቸው። ጠንቋዩ ኤልማስ ግን፣ የስሙ ትርጕም እንዲህ ነበርና፣ አገረ ገዥው እንዳያምን ለማደናቀፍ ስለ ፈለገ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለውም ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ትኵር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፤ “አንተ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ ተንኰልንና ክፋትን ሁሉ የተሞላህ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጌታን ቀና መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም የጌታ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውር ትሆናለህ፤ ከእንግዲህ የፀሓይን ብርሃን ለአንድ አፍታ እንኳ አታይም።” ወዲያውም ጭጋግና ጨለማ በላዩ ወረደ፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ለመፈለግ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር። አገረ ገዥውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ በጌታ ትምህርት በመደነቅ አመነ። ጳውሎስና ጓደኞቹ ከጳፉ ተነሥተው በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌን ሄዱ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን ተነሥተው በጲስድያ ውስጥ ወዳለችው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ፣ የምኵራብ አለቆች፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሕዝቡን የሚመክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ሲሉ ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሥቶ በእጁ በመጥቀስ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ደግሞም እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ አድምጡ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ፣ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ በግብጽ ምድር እያሉም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኀያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው። አርባ ዓመት ያህልም በበረሓ ታገሣቸው፤ በከነዓን ምድር የነበሩትንም ሰባት መንግሥታት አጥፍቶ፣ ምድራቸውን ለገዛ ሕዝቡ ርስት አድርጎ አወረሳቸው። ይህም ሁሉ የተፈጸመው በአራት መቶ ዐምሳ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነበር። “ከዚህ በኋላ፣ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለመኑት፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን፣ የቂስን ልጅ ሳኦልን ሰጣቸው፤ እርሱም አርባ ዓመት ገዛቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት። “እግዚአብሔርም በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው፦ “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ። የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ። ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ። እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ። እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው። በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ። ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን! አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ። ከዚህ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ በመርከብ ተሳፍረው ከጳፉ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌ ሄዱ፤ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ግን ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ። እነርሱ ግን ከጴርጌ ተነሥተው በጲስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀን ወደ አንድ ምኲራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ የምኲራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝቡን የሚያጽናና የምክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ወደነጳውሎስ ሰው ላኩ። ስለዚህ ጳውሎስ ተነሣና ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ እንዲህም ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩ እናንተ አሕዛብ! ስሙ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው። ለአርባ ዓመትም ያኽል በበረሓ ታገሣቸው ከዚያም በኋላ በከነዓን አገር ሰባት መንግሥታትን አጥፍቶ የእነርሱን ምድር አወረሳቸው፤ ከዚህም በኋላ ለአራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያኽል እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። “ከዚያም ቀጥሎ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት አነገሠላቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲመሰክር፦ ‘እንደ ፍላጎቴ የሚሆንልኝን፤ ፈቃዴንም የሚፈጽመውን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ብሎአል። ከዚህ ሰው ዘር እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የእስራኤልን አዳኝ ኢየሱስን አስነሣላቸው።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ፤” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኩር ብሎ ሲመለከተው “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፤ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ! ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ፤” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ! ስሙ። የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብጽ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። በበረሃም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፤ ሲመሰክርለትም ‘እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤’ አለ። ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።