የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 11:1-18

ሐዋርያት ሥራ 11:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሐዋ​ር​ያ​ትና በይ​ሁዳ የነ​በሩ ወን​ድ​ሞ​ችም አሕ​ዛብ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል እንደ ተቀ​በሉ ሰሙ። ጴጥ​ሮ​ስም ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም በወጣ ጊዜ ከአ​ይ​ሁድ ወገን የሆ​ኑት ወን​ድ​ሞች ተቃ​ወ​ሙት። “ወደ አል​ተ​ገ​ረ​ዙት ሰዎች ቤት ገብ​ተህ አብ​ረ​ሃ​ቸው በል​ተ​ሃል” አሉት። ጴጥ​ሮ​ስም ከመ​ጀ​መ​ሪያ ጀምሮ ይነ​ግ​ራ​ቸው ጀመረ፤ እን​ዲ​ህም አላ​ቸው። “በኢ​ዮጴ ከተማ ሳለሁ ስጸ​ልይ ተመ​ስጦ መጣ​ብ​ኝና ራእይ አየሁ፤ ታላቅ መጋ​ረጃ የመ​ሰለ ዕቃ በአ​ራቱ ማዕ​ዘን ተይዞ ከሰ​ማይ ወረደ፤ ወደ እኔም መጣ። በው​ስ​ጡም አራት እግር ያላ​ቸው እን​ስ​ሳ​ንና አራ​ዊ​ትን፥ ተን​ቀ​ሳ​ቃ​ሾ​ች​ንም፥ የሰ​ማይ ወፎ​ች​ንም አየሁ። ‘ጴጥ​ሮስ ሆይ፥ ተነ​ሥና አር​ደህ ብላ’ የሚ​ለ​ኝ​ንም ቃል ሰማሁ። ‘አቤቱ፥ ከቶ አይ​ሆ​ንም፤ ንጹሕ ያል​ሆነ ርኩስ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያ​ው​ቅም’ አልሁ። ደግ​ሞም፦ ‘እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ንጹሕ ያደ​ረ​ገ​ውን አንተ አታ​ር​ክ​ሰው’ የሚል ቃል ከሰ​ማይ መለ​ሰ​ልኝ። እን​ዲ​ህም መላ​ልሶ ሦስት ጊዜ ነገ​ረኝ፤ ዳግ​መ​ኛም ሁሉ ተጠ​ቅ​ልሎ ወደ ሰማይ ተመ​ለሰ። በዚ​ያ​ችም ሰዓት ከቂ​ሳ​ርያ ወደ እኔ የተ​ላኩ ሦስት ሰዎች መጡ፤ እኔ ባለ​ሁ​በት ግቢ በርም ቆሙ። መን​ፈስ ቅዱ​ስም፦ ‘ሳት​ጠ​ራ​ጠር አብ​ረ​ሃ​ቸው ሂድ’ አለኝ፤ እነ​ዚህ ስድ​ስቱ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ንም ተከ​ት​ለ​ውኝ መጡና ወደ​ዚያ ሰው ቤት ገባን። እር​ሱም በቤቱ ቆሞ ሳለ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ እን​ዳየ ‘ወደ ኢዮጴ ከተማ ልከህ ጴጥ​ሮስ የተ​ባ​ለ​ውን ስም​ዖ​ንን ይጥ​ሩ​ልህ። አን​ተና ቤተ ሰቦ​ችህ ሁሉ የም​ት​ድ​ኑ​በ​ትን ነገር እርሱ ይነ​ግ​ር​ሃል’ እንደ አለው ነገ​ረን። ላስ​ተ​ም​ራ​ቸው በጀ​መ​ርሁ ጊዜም ቀድሞ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ መን​ፈስ ቅዱስ በእ​ነ​ር​ሱም ላይ ወረደ። ‘ዮሐ​ንስ በውኃ አጠ​መቀ፤ እና​ንተ ግን፤ በመ​ን​ፈስ ቅዱስ ትጠ​መ​ቃ​ላ​ችሁ’ ያለ​ውን የጌ​ታ​ች​ንን ቃል ዐሰ​ብሁ። እን​ግ​ዲህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ለአ​መ​ን​ነው ለእኛ እንደ ሰጠን፥ ያን ጸጋ​ውን እንደ እኛ አስ​ተ​ካ​ክሎ ከሰ​ጣ​ቸው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ልከ​ለ​ክል የም​ችል እኔ ማነኝ?” ይህ​ንም በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለአ​ሕ​ዛብ ደግሞ ለሕ​ይ​ወት የሚ​ሆን ንስ​ሓን ሰጣ​ቸው እንጃ” እያሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አመ​ሰ​ገኑ።

ሐዋርያት ሥራ 11:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። ስለዚህ ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ፣ ከተገረዙት ወገን የነበሩ አማኞች ነቀፉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ።” ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ነገሩን በቅደም ተከተል ያስረዳቸው ጀመር፤ “በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ በተመስጦ ውስጥ እያለሁ ራእይ አየሁ፤ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር፣ በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ እኔ ወደ ነበርሁበት ቦታ ሲወርድ አየሁ። አተኵሬም ይህን ነገር ስመለከት አራት እግር ያላቸው እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በሰማይ የሚበርሩ አዕዋፍ አየሁ። በዚህ ጊዜ፣ ‘ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣና ዐርደህ ብላ’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነገር ፈጽሞ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልሁ። “ያም ድምፅ ዳግመኛ፣ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው’ ሲል ከሰማይ ተናገረኝ። ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ከዚያ ሁሉም እንደ ገና ወደ ሰማይ ተወሰደ። “ልክ በዚያው ሰዓት፣ ሦስት ሰዎች ከቂሳርያ ወደ እኔ ተልከው መጥተው እኔ ባለሁበት ቤት ደጅ ላይ ቆሙ፤ መንፈስ ቅዱስም ምንም ሳላወላውል ከእነርሱ ጋር እንድሄድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስት ወንድሞች ከእኔ ጋር ሄዱ፤ ወደ ሰውየውም ቤት ገባን። እርሱም መልአክ በቤቱ ውስጥ ቆሞ እንደ ታየውና እንዲህ እንዳለው ነገረን፤ ‘ወደ ኢዮጴ ሰው ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ቃል ይነግርሃል።’ “እኔም ገና መናገር ስጀምር፣ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ በእነርሱም ላይ ወረደ። በዚህ ጊዜ፣ ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ሲል ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን ለእኛ የሰጠንን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፣ ታዲያ፣ እግዚአብሔርን መቋቋም እችል ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” ይህን በሰሙ ጊዜም የሚሉትን አጥተው እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ “ይህማ ከሆነ አሕዛብም ወደ ሕይወት ይመጡ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን ሰጥቷቸዋል ማለት ነዋ።”

ሐዋርያት ሥራ 11:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው፦ “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ” አሉት። ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ፦ “እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤ ይህንም ትኵር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ። ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ። እኔም፦ “ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ ርኵስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና” አልሁ። ሁለተኛም፦ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው” የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ እንደ ገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ። እነሆም፥ ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ። መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን። እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና፦ “ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል” እንዳለው ነገረን። ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው። ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከላከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና፦ “እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።

ሐዋርያት ሥራ 11:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በይሁዳ ምድር የሚገኙ ሐዋርያትና ወንድሞች አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን ሰሙ። ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በሄደ ጊዜ በግዝረት አስፈላጊነት የሚያምኑ የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ “ስለምን ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ?” በማለት ወቀሱት። ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ሁሉንም ነገር በተከታታይ ማስረዳት ጀመረ፦ “እኔ በኢዮጴ ከተማ በጸሎት ላይ ሳለሁ በተመስጦ ራእይ አየሁ፤ ያየሁትም ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ ሲወርድና ወደ እኔ ሲመጣ ነው፤ እርሱን ትኲር ብዬ ስመለከት በመጋረጃው ጨርቅ ላይ እንስሶችን፥ የዱር አራዊትን፥ በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችንና በሰማይ የሚበርሩ ወፎችን አየሁ፤ ‘ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!’ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ፤ እኔ ግን ‘አይሆንም ጌታ ሆይ! ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በአፌ ገብቶ አያውቅም’ አልኩ። ነገር ግን ሁለተኛ ጊዜ፥ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም’ የሚል መልስ ከሰማይ ሰማሁ። ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር በሙሉ ወደ ሰማይ ተወሰደ። እነሆ፥ በዚያን ጊዜ ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች እኔ ወደነበርኩበት ቤት ደረሱ። ያላንዳች ማመንታት ከእነርሱ ጋር እንድሄድም መንፈስ ቅዱስ ነገረኝ፤ እነዚህ ስድስት ወንድሞችም ከእኔ ጋር ነበሩ፤ ከእነርሱም ጋር አብረን ቆርኔሌዎስ ወደ ተባለው ሰው ቤት ገባን። እርሱም መልአክን በቤቱ ውስጥ ቆሞ እንዳየና ‘ወደ ኢዮጴ ሰው ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ አንተና ቤተሰብህ ሁሉ የምትድኑበትን ቃል ይነግርሃል’ እንዳለው ነገረን። እኔም መናገር በጀመርኩ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ዐይነት በእነርሱ ላይ ወረደ። በዚያን ጊዜ ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል አስታወስኩ። እኛ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠውን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፤ ታዲያ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል የምችል እኔ ማን ነኝ!” እነርሱም ይህንን በሰሙ ጊዜ የሚመልሱትን አጥተው ዝም አሉ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር ለአሕዛብም ለአዲስ ሕይወት የሚያበቃቸውን ንስሓ ሰጥቶአቸዋል፤” በማለትም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ሐዋርያት ሥራ 11:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ፤” አሉት። ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ “እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤ ይህንም ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ። ‘ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤’ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ ርኩስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና፤’ አልሁ። ሁለተኛም ‘እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፤ እንደገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ። እነሆም፥ ያንጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ። መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ፤ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን። እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና ‘ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል፤’ እንዳለው ነገረን። ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱም ወረደላቸው። ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፤’ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከላከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና “እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው፤” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።