ሐዋርያት ሥራ 1:12-26
ሐዋርያት ሥራ 1:12-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ለኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። ወደ ማደሪያቸውም በደረሱ ጊዜ ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ ማቴዎስ፥ በርተሎሜዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከጌታችን ከኢየሱስ እናት ከማርያም፥ ከወንድሞቹም ጋር በአንድነት ለጸሎት ይተጉ ነበር። ያንጊዜም ጴጥሮስ ተነሣና በወንድሞቹ መካከል ቆመ፤ መቶ ሃያ ያህል ሰዎችም በዚያ ሳሉ እንዲህ አላቸው። “እናንተ ሰዎች ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ ጌታችን ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባል። እርሱም ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበር፤ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበር። ከዚህም በኋላ ይህ ሰው በዐመፅ ዋጋዉ መሬት ገዛ፤ በምድር ላይም በግንባሩ ወደቀና ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ። በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ዜናዉ ተሰማ፤ ያም መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ይኸውም የደም መሬት ማለት ነው። በመዝሙር መጽሐፍ ‘መኖሪያዉ ምድረ በዳ ትሁን፤ በውስጧም የሚኖር አይኑር፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ’ ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤዉ ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።” ኢዮስጦስ የሚሉትን በርናባስ የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን ሰዎች አቆሙ። እንዲህም ብለው ጸለዩ፥ “አቤቱ፥ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ፥ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥኸውን አንዱን ግለጥ። ይሁዳ ወደ ሀገሩ ይሄድ ዘንድ የተዋትን ይህቺን የአገልግሎትና የሐዋርያነትን ቦታ የሚቀበላትን ግለጥ።” ዕጣም አጣጣሏቸው፤ ዕጣዉም በማትያስ ላይ ወጣ፤ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋራም ተቈጠረ።
ሐዋርያት ሥራ 1:12-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ይህም ተራራ ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል ይርቅ ነበር። ወደ ከተማዪቱም በገቡ ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፤ እነዚህም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብ፣ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ ቶማስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናኢው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ከሴቶቹና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ጋራ እንዲሁም ከወንድሞቹ ጋራ በአንድ ልብ ሆነው ያለ ማቋረጥ ተግተው ይጸልዩ ነበር። በእነዚያም ቀናት፣ ጴጥሮስ መቶ ሃያ በሚሆኑ ወንድሞች መካከል ቆሞ፣ እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፣ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፉ ቃል መፈጸም ስላለበት፣ እርሱ ከእኛ እንደ አንዱ ተቈጥሮ በዚህ አገልግሎት የመሳተፍ ዕድል አግኝቶ ነበር።” ይህ ሰው ስለ ክፉ ሥራው በተከፈለው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በዚያም በግንባሩ ተደፍቶ ሰውነቱ እመካከሉ ላይ ፈነዳ፤ ሆድ ዕቃውም ተዘረገፈ። ይህም በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ መሬቱም በቋንቋቸው “አኬልዳማ” ተብሎ ተጠራ፤ ትርጓሜውም “የደም መሬት” ማለት ነው። ጴጥሮስም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “በመዝሙር መጽሐፍ፣ ‘መኖሪያው ባድማ ትሁን፤ የሚኖርባትም አይገኝ’ ደግሞም፣ ‘ሹመቱንም ሌላ ይውሰደው’ ተብሎ ተጽፏል። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በመካከላችን በገባበትና በወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ ከእኛ ጋራ ከነበሩት መካከል አንድ ሰው መምረጥ ያስፈልጋል፤ ይኸውም፣ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ኢየሱስ ከእኛ ተለይቶ እስካረገበት ቀን ድረስ የነበረ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋራ የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን ያስፈልጋል።” ስለዚህ ኢዮስጦስ የሚሉትን፣ በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቀረቡ፤ እንዲህም ብለው ጸለዩ፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ታውቃለህ፤ ከእነዚህ ከሁለቱ መካከል የመረጥኸውን ሰው አመልክተንና ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ትቶት በሄደው በዚህ አገልግሎትና በሐዋርያዊነት ቦታ ላይ ሹመው።” ከዚያም ዕጣ ጣሉላቸው፤ ዕጣውም ለማትያስ ወጣ፤ እርሱም ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋራ ተቈጠረ።
ሐዋርያት ሥራ 1:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር። በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሀያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤ ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበርና፥ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና።” ይህም ሰው በዓመፅ ዋጋ መሬት ገዛ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም የደም መሬት ማለት ነው። በመዝሙር መጽሐፍ፦ “መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን የሚኖርባትም አይኑር፤” ደግሞም፦ “ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት” ተብሎ ተጽፎአልና። ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል። ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ። ሲጸልዩም፦ “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ፥ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ።” ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።
ሐዋርያት ሥራ 1:12-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም የሚርቀው የሰንበት መንገድ (አንድ ኪሎ ሜትር) ያኽል ነው። ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ወደሚኖሩበት ሰገነት ላይ ወጡ፤ እነርሱም “ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ በርተሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ” ናቸው። እነዚህ ሁሉ ዘወትር ለጸሎት በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር አንዳንድ ሴቶችና የኢየሱስ እናት ማርያም፥ እንዲሁም የኢየሱስ ወንድሞች ነበሩ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መቶ ኻያ በሚያኽሉ አማኞች መካከል ቆመና እንዲህ አለ፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፥ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም ነበረበት። ይሁዳ ከእኛ አንዱ ሆኖ የዚህ አገልግሎታችን ተካፋይ ነበር። ነገር ግን ይህ ሰው በክፉ ሥራው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ተዘረገፈ፤ ይህም ነገር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህ ያ መሬት በቋንቋቸው ‘አኬልዳማ’ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጓሜውም ‘የደም መሬት’ ማለት ነው። “ይህም የሆነበት ምክንያት በመዝሙር መጽሐፍ፥ ‘መኖሪያው ባዶ ይሁን፤ ማንም አይኑርበት፤ ደግሞም ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰድበት’ የሚል ተጽፎ ስለ ነበር ነው። “ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በተመላለሰበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር አብረውን ከነበሩት፥ እንዲሁም ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ አብረውን ከነበሩት ከነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን ያስፈልጋል።” ከዚህ በኋላ ሁለት ሰዎች አቀረቡ፤ እነርሱም በርሳባስ ወይም ኢዮስጦስ የሚባለው ዮሴፍና ማትያስ ነበሩ። እንዲህ ሲሉም ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ጌታ ሆይ፥ ከነዚህ ከሁለቱ ማንን እንደ መረጥክ አሳየን፤ የምንጸልየውም ይሁዳ ወደ ራሱ ስፍራ ሲሄድ የተወውን አገልግሎትና ሐዋርያነት በመቀበል የሚተካውን እንድትገልጥልን ነው።” ዕጣም በጣሉ ጊዜ ዕጣው ለማትያስ ወጣ፤ ስለዚህ እርሱ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።
ሐዋርያት ሥራ 1:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ ደብረዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፤ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር። በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሃያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ “ወንድሞች ሆይ! ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤ ከእኛ ጋር ተቆጥሮ ነበርና፤ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና። ይህም ሰው በዐመፅ ዋጋ መሬት ገዛ፤ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም የደም መሬት ማለት ነው። በመዝሙር መጽሐፍ ‘መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን፤ የሚኖርባትም አይኑር፤’ ደግሞም ‘ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት፤’ ተብሎ ተጽፎአልና። ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።” ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ። ሲጸልዩም “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ! ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው፤” አሉ። ዕጣም ተጣጣሉላቸው፤ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ።