2 ጢሞቴዎስ 3:5-9
2 ጢሞቴዎስ 3:5-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኀጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።
2 ጢሞቴዎስ 3:5-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ። እነርሱም በየቤቱ ሾልከው እየገቡ የኀጢአት ብዛት የተጫናቸውን፣ በተለያየ ክፉ ምኞት ውስጥ ገብተው የሚዋልሉ መንፈሰ ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ናቸው፤ እንደነዚህ ያሉ ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ ፈጽሞ ሊደርሱ አይችሉም። ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት፣ እነዚህ አእምሯቸው የጠፋባቸውና ከእምነት የተጣሉ ሰዎች ደግሞ እውነትን ይቃወማሉ። ይሁን እንጂ አይሳካላቸውም፤ ምክንያቱም የእነዚያ ሰዎች ሞኝነት እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ የእነዚህም ለሁሉ ግልጽ ይሆናል።
2 ጢሞቴዎስ 3:5-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።
2 ጢሞቴዎስ 3:5-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርን የሚያመልኩ መስለው ይታያሉ፤ የአምልኮትን ኀይል ግን ይክዳሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ። እነዚህ ሰዎች በየቤቱ ሾልከው እየገቡ ብዙ ኃጢአት የተከመረባቸውንና በልዩ ልዩ ፍትወት የሚመሩ መንፈሰ ደካማ የሆኑ ሴቶችን እንደሚያጠምዱት ሰዎች ናቸው። እንዲህ ዐይነቶቹ ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ መድረስ አይችሉም። ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት እነዚህ ሰዎች አእምሮአቸው የተበላሸና በእምነትም ነገር ውድቀት የደረሰባቸው ስለ ሆነ እውነትን ይቃወማሉ። የኢያኔስና የኢያንበሬስ ሞኝነት እንደ ተገለጠ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት በሰው ሁሉ ፊት ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም።
2 ጢሞቴዎስ 3:5-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሃይማኖትን መልክ የያዙ ነገር ግን ኃይሉን የካዱ ሆነው ይገኛሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ። ከእነርሱም መካከል በየቤቱ እየተሽሎኮሎኩ በመግባት የኃጢአታቸው ሸክም የከበደባቸውንና በልዩ ልዩ ምኞትም ውስጥ የሚዋዠቁትን ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ይገኙባቸዋል። እንዲህ ያሉት ሴቶች ግን ሁልጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉ ናቸው። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው በእምነትም ረገድ ተፈትነው የወደቁ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን እነዚያ ሁለቱ ተቃዋሚዎች እንደሆኑት እንዲሁ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት ለሁሉም ሰው ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም።