2 ጢሞቴዎስ 3:1-15
2 ጢሞቴዎስ 3:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፤ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኀጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም። አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ። በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ። አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፤ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል።
2 ጢሞቴዎስ 3:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወድዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወድዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወድዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኵሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወድዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ። እነርሱም በየቤቱ ሾልከው እየገቡ የኀጢአት ብዛት የተጫናቸውን፣ በተለያየ ክፉ ምኞት ውስጥ ገብተው የሚዋልሉ መንፈሰ ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ናቸው፤ እንደነዚህ ያሉ ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ ፈጽሞ ሊደርሱ አይችሉም። ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት፣ እነዚህ አእምሯቸው የጠፋባቸውና ከእምነት የተጣሉ ሰዎች ደግሞ እውነትን ይቃወማሉ። ይሁን እንጂ አይሳካላቸውም፤ ምክንያቱም የእነዚያ ሰዎች ሞኝነት እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ የእነዚህም ለሁሉ ግልጽ ይሆናል። አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ ዐላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን ሁሉ ታውቃለህ፤ ስደቴንና መከራዬን፣ በአንጾኪያና በኢቆንዮን፣ በልስጥራንም የደረሰብኝን ሁሉ፣ የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከእነዚህ ሁሉ አዳነኝ። በርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወድዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ክፉዎችና አታላዮች ግን እየሳቱና እያሳቱ፣ በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ። አንተ ግን በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና፤ ይህን ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል።
2 ጢሞቴዎስ 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም። አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ። በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ። አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።
2 ጢሞቴዎስ 3:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ዕወቅ፤ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፥ ለገንዘብ የሚስገበገቡ፥ ትምክሕተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ ውለታቢሶች፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ይቅርታ የማያደርጉ፥ የሰው ስም የሚያጠፉ፥ ራሳቸውን የማይቈጣጠሩ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን ነገር የሚጠሉ፥ ከዳተኞች፥ ጥንቃቄ የሌላቸው፥ በትዕቢት የተነፉ፥ እግዚአብሔርን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ። እግዚአብሔርን የሚያመልኩ መስለው ይታያሉ፤ የአምልኮትን ኀይል ግን ይክዳሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ። እነዚህ ሰዎች በየቤቱ ሾልከው እየገቡ ብዙ ኃጢአት የተከመረባቸውንና በልዩ ልዩ ፍትወት የሚመሩ መንፈሰ ደካማ የሆኑ ሴቶችን እንደሚያጠምዱት ሰዎች ናቸው። እንዲህ ዐይነቶቹ ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ መድረስ አይችሉም። ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት እነዚህ ሰዎች አእምሮአቸው የተበላሸና በእምነትም ነገር ውድቀት የደረሰባቸው ስለ ሆነ እውነትን ይቃወማሉ። የኢያኔስና የኢያንበሬስ ሞኝነት እንደ ተገለጠ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት በሰው ሁሉ ፊት ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም። አንተ ግን ትምህርቴን፥ አኗኗሬን፥ ዓላማዬን፥ እምነቴን፥ ትዕግሥቴን፥ ፍቅሬን፥ በያዝኩት መጽናቴን ተከትለሃል፤ እንዲሁም ስደቴንና መከራዬን ታውቃለህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የደረሰብኝን ነገርና በትዕግሥት የተቀበልኩትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከሁሉም አዳነኝ። የኢየሱስ ክርስቶስ ወገኖች ሆነው መንፈሳዊ ሕይወትን መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይገጥማቸዋል። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አስመሳዮች ግን ሰዎችን እያሳሳቱና ራሳቸውም እየተሳሳቱ፥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ አንተ ግን የተማርከው ከማን እንደ ሆነ ስለምታውቅ በተማርከውና እውነቱን በተረዳኸው ጽና። እንዲሁም ከሕፃንነትህ ጀምረህ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ትምህርት የሚሰጡህን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል።
2 ጢሞቴዎስ 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያስጨንቁ ጊዜያት እንደሚመጡ ይህን እወቅ። ሰዎች እንዲህ ይሆናሉና፤ ራሳቸውን የሚወዱ፥ ገንዘብን ወዳጆች፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይቈጣጠሩ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተወጠሩ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፥ የሃይማኖትን መልክ የያዙ ነገር ግን ኃይሉን የካዱ ሆነው ይገኛሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ። ከእነርሱም መካከል በየቤቱ እየተሽሎኮሎኩ በመግባት የኃጢአታቸው ሸክም የከበደባቸውንና በልዩ ልዩ ምኞትም ውስጥ የሚዋዠቁትን ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ይገኙባቸዋል። እንዲህ ያሉት ሴቶች ግን ሁልጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉ ናቸው። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው በእምነትም ረገድ ተፈትነው የወደቁ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን እነዚያ ሁለቱ ተቃዋሚዎች እንደሆኑት እንዲሁ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት ለሁሉም ሰው ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም። አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን ዓላማዬንም፥ እምነቴንም፥ ትዕግሥቴንም፥ ፍቅሬንም፥ መጽናቴንም፥ ስደቴንም፥ መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የደረሰብኝን ነገርና የታገሥሁትን ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከሁሉም አዳነኝ። በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ለመኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አስመሳዮች እያታለሉና እየተታለሉ ከክፋት ወደ ባሰ ክፋት ይሄዳሉ። አንተ ግን በተማርህበትና በጽኑ ባመንኸበት ነገር ሳትናወጥ ኑር፤ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ እንዲሁም ከሕፃንነትህ አንሥቶ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ወደሚገኘው መዳን የሚመራህን ጥበብ ሊሰጡህ የሚያስችሉትን ቅዱስ መጻሕፍትን አውቀሃልና።