2 ጢሞቴዎስ 2:20-26
2 ጢሞቴዎስ 2:20-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፤ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማርም የሚበቃ፥ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም “ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሓን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው ወደ አእምሮ ይመለሳሉ፤” ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።
2 ጢሞቴዎስ 2:20-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን፣ የዕንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ለከበረ፣ ሌሎቹም ላልከበረ አገልግሎት ይውላሉ። እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ከጠቀስኋቸው ነገሮች ቢያነጻ፣ ለክቡር አገልግሎት የሚውል፣ የተቀደሰ፣ ለጌታው የሚጠቅም፣ ለመልካም ሥራም ሁሉ የተሰናዳ ዕቃ ይሆናል። ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋርም ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ተከታተል። ከማይረባና ትርጕም የለሽ ከሆነ ክርክር ራቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ጠብን እንደሚያስከትሉ ታውቃለህ። የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቃት ያለው፣ ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል፤ እውነትን ወደ ማወቅ ይደርሱ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን እንደሚሰጣቸው ተስፋ በማድረግ የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚያቃና መሆን ይኖርበታል፤ ይኸውም ወደ አእምሯቸው ይመለሳሉ፤ ፈቃዱን ሊያስፈጽማቸው ምርኮኛ አድርጎ ከያዛቸው ከዲያብሎስ ወጥመድም ያመልጣሉ በማለት ነው።
2 ጢሞቴዎስ 2:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።
2 ጢሞቴዎስ 2:20-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በትልቅ ቤት ውስጥ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ ከእንጨትና ከሸክላ የተሠሩ ዕቃዎችም ይገኛሉ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ለተከበረ አገልግሎት፥ አንዳንዶቹም ክብር ለሌለው አገልግሎት ይውላሉ። ከእነዚህ ክብር ከሌላቸው ነገሮች ተለይቶ ንጹሕ ሆኖ የሚኖር ሰው ለተከበረ አገልግሎት እንደሚውል ዕቃ ይሆናል፤ ለማንኛውም መልካም አገልግሎት የተዘጋጀ ለጌታው የተቀደሰና ጠቃሚ መገልገያ ይሆናል። ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ሰዎች ጋር ሆነህ ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን ተከታተል። ጠብን እንደሚያመጣ ዐውቀህ ከሞኝነትና ከከንቱ ክርክር ራቅ። የጌታ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነ ሰው በሁሉም ዘንድ ገር፥ የማስተማር ችሎታ ያለውና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት እንጂ መጣላት አይገባውም፤ እርሱ የሚቃወሙትን ሰዎች በገርነት የሚያርም መሆን አለበት፤ ምናልባትም እውነትን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ንስሓ የመግባትን ዕድል ይሰጣቸው ይሆናል። በዚህ ዐይነት ወደ ልቡናቸው ተመልሰው ዲያብሎስ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ እነርሱን ከያዘበት ወጥመድ ያመልጣሉ።
2 ጢሞቴዎስ 2:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ የእንጨትና የሸክላ ዕቃዎችም ደግሞ ይኖራሉ፤ እኩሌቶቹም ለክብር፥ እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ለውርደት ከሚሆነው ነገር ራሱን ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን፥ የተቀደሰ፥ ለጌታውም የሚጠቅም፥ ለመልካምም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ጠብንም እንደሚያመጡ ታውቃለህና ከሞኝነትና ከከንቱ ንትርክ ራቅ። የጌታም ባርያ ጠበኛ መሆን አይገባውም፤ ይልቁንስ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ ትዕግሥተኛና የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚገሥጽ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህም የተነሣ ምናልባት እግዚአብሔር ንስሓ ገብተው እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፥ እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም ታስረው ከተያዙበት ከዲያብሎስ ወጥመድ ወጥተው ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋልና።