2 ሳሙኤል 9:1-13
2 ሳሙኤል 9:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትም፦ ስለ ዮናታን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው ቀርቶአልን? አለ። ከሳኦልም ቤት ሲባ የሚባል አንድ ባሪያ ነበረ፥ ወደ ዳዊትም ጠሩት፥ ንጉሡም፦ አንተ ሲባ ነህን? አለው። እርሱም፦ እኔ ባሪያህ ነኝ አለ። ንጉሡም፦ የእግዚአብሔርን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው አልቀረምን? አለ። ሲባም ንጉሡን፦ እግሩ ሽባ የሆነ አንድ የዮናታን ልጅ አለ አለው። ንጉሡም፦ ወዴት ነው? አለው፥ ሲባም ንጉሡን፦ እነሆ፥ እርሱ በሎዶባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት አለ አለው። ንጉሡም ዳዊት ልኮ ከሎዶባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጣ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ፥ ዳዊትም፦ ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ አለ፥ እርሱም፦ እነሆኝ ባሪያህ አለ። ዳዊትም፦ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፥ የአባትህንም የሳኦልን ምድር ሁሉ እመልስልሃለሁ፥ አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው። እርሱም፦ የሞተ ውሻ ወደምመስል ወደ እኔ የተመለከትህ እኔ ባሪያህ ምንድር ነኝ? ብሎ እጅ ነሣ። ንጉሡም የሳኦልን ባሪያ ሲባን ጠርቶ፦ ለሳኦልና ለቤቱ ሁሉ የነበረውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቻለሁ። አንተና ልጆችህ ሎሌዎችህም ምድሩን እረሱለት፥ ለጌታህም ልጅ እንጀራ ይሆነው ዘንድ ፍሬውን አግባ፥ የጌታህ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ሁልጊዜ ከገበታዬ ይበላል አለው። ለሲባም አሥራ አምስት ልጆችና ሀያ ባሪያዎች ነበሩት። ሲባም ንጉሡን፦ ጌታዬ ንጉሡ ባሪያውን እንዳዘዘ እንዲሁ ባሪያህ ያደርጋል አለው። ሜምፊቦስቴም ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት ገበታ ይበላ ነበር። ለሜምፊቦስቴም ሚካ የተባለ ታናሽ ልጅ ነበረው። በሲባም ቤት ያሉ ሁሉ ለሜምፊቦስቴ ያገለግሉ ነበር። ሜምፊቦስቴም ከንጉሥ ገበታ ሁልጊዜ እየበላ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ነበር፥ ሁለት እግሩም ሽባ ነበረ።
2 ሳሙኤል 9:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትም፥ “ስለ ዮናታን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ አንድ ሰው አለን?” አለ። ከሳኦልም ቤት አንድ ብላቴና ነበረ፤ ስሙም ሲባ ነበረ፤ ወደ ዳዊትም ጠሩት፤ ንጉሡም፥ “አንተ ሲባ ነህን?” አለው። እርሱም፥ “እኔ አገልጋይህ ነኝ” አለ። ንጉሡም፥ “የእግዚአብሔርን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው አለን?” አለ። ሲባም ንጉሡን፥ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” አለው። ንጉሡም፥ “ወዴት ነው?” አለው፤ ሲባም ለንጉሡ፥ “እነሆ እርሱ በሎዶባር በአብያል ልጅ በማኪር ቤት አለ” አለው። ንጉሡም ዳዊት ልኮ ከሎዶባር ከአብያል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፌቡስቴ ወደ ዳዊት መጣ፤ በግንባሩም ወድቆ ሰገደለት፤ ንጉሥ ዳዊትም፥ “ሜምፌቡስቴ ሆይ፥” አለ፤ እርሱም፥ “እነሆኝ አገልጋይህ” አለ። ዳዊትም፥ “ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፤ የአባትህን አባት የሳኦልን መሬት ሁሉ እመልስልሃለሁ፤ አንተም ሁል ጊዜ ከገበታዬ እንጀራን ትበላለህ” አለው። እርሱም፥ “የሞተ ውሻ ወደምመስል ወደ እኔ ትመለከት ዘንድ እኔ አገልጋይህ ምንድን ነኝ?” ብሎ ሰገደ። ንጉሡም የሳኦልን አገልጋይ ሲባን ጠርቶ፥ “ለሳኦልና ለቤቱ ሁሉ የነበረውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቻለሁ። አንተና ልጆችህ፥ ሎሌዎችህም ምድሩን እረሱለት፤ ለጌታህም ልጅ እንጀራ ይሆነው ዘንድ ፍሬውን አግቡ፤ እናንተም ትመግቡታላችሁ፤የጌታህ ልጅ ሜምፌቡስቴ ግን ሁልጊዜ ከገበታዬ ይበላል” አለው። ለሲባም ዐሥራ አምስት ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት። ሲባም ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሡ አገልጋዩን እንዳዘዘ እንዲሁ አገልጋይህ ያደርጋል” አለው። ሜምፌቡስቴም ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት ገበታ ይበላ ነበር። ለሜምፌቡስቴም ሚካ የተባለ ታናሽ ልጅ ነበረው፤ በሲባም ቤት ያሉ ሁሉ ለሜምፌቡስቴ ያገለግሉ ነበር። ሜምፌቡስቴም ከንጉሥ ገበታ ሁልጊዜ እየበላ በኢየሩሳሌም ኖረ፤ ሁለት እግሮቹም ሽባ ነበሩ።
2 ሳሙኤል 9:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳዊትም፣ “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖር ይሆን?” በማለት ጠየቀ። በዚያ ጊዜ ከሳኦል ቤት ሲባ የሚባል አንድ አገልጋይ ስለ ነበር፣ ወደ ዳዊት እንዲሄድ ነገሩት። ንጉሡም፣ “ሲባ የምትባለው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “አዎን እኔ አገልጋይህ ነኝ” አለ። ንጉሡም፣ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” ሲል ጠየቀው። ሲባም ለንጉሡ፣ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፣ “የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀ። ሲባም፣ “ሎደባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት። ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት፣ ሜምፊቦስቴን ከዓሚኤል ከማኪር ቤት ከሎደባር ልኮ አስመጣው። የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፣ አክብሮቱን ለመግለጥ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ። ዳዊትም፣ “ሜምፊቦስቴ” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “እነሆ፤ አገልጋይህ” አለ። ዳዊትም፣ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል በርግጥ ቸርነት አደርግልሃለሁና። የአባትህን የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከማዕዴ ትበላለህ” አለው። ሜምፊቦስቴ ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፣ “እንደ ሞተ ውሻ ለምቈጠር ለእኔ ይህን ያህል የምታደርግልኝ አገልጋይህ ኧረ ማን ነኝ?” አለ። ከዚያም ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ሲባን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “የሳኦልና የቤተ ሰቡ የሆነውን ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ። አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ የጌታችሁ የልጅ ልጅ የሚበላውን እንዲያገኝ መሬቱን ዕረሱለት፣ ምርቱንም አግቡለት። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ምን ጊዜም ከማእዴ ይበላል።” በዚያ ጊዜ ሲባ ዐሥራ ዐምስት ወንዶች ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት። ከዚያም ሲባ ንጉሡን፣ “ጌታዬ ንጉሥ፣ አገልጋዩን ያዘዘውን ሁሉ፣ አገልጋይህም ይፈጽመዋል” አለው። ስለዚህም ሜምፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ሆኖ ከዳዊት ማእድ ይበላ ነበር። ሜምፊቦስቴ ሚካ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ነበረው፤ የሲባ ቤተ ሰዎች በሙሉ ሜምፊቦስቴን ያገለግሉት ነበር። ሜምፊቦስቴም ሁልጊዜ ከንጉሥ ማእድ ስለሚበላ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፤ ሁለት እግሮቹም ሽባ ነበሩ።
2 ሳሙኤል 9:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ዳዊት “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤተሰብ ከሞት የተረፈ ሰው አለን?” ብሎ ጠየቀ። ከሳኦል ቤተሰብ ጺባ የሚባል አንድ አገልጋይ ነበረ፤ እርሱም ወደ ዳዊት እንዲሄድ ተነገረው፤ ዳዊትም “አንተ ጺባ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ጺባም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ ነኝ!” ሲል መለሰ። ንጉሡም “እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ቸርነት የማሳየው ከሳኦል ቤተሰብ ከሞት የተረፈ ሰው አለን?” ሲል ጺባን ጠየቀው። ጺባም “ከዮናታን ወንዶች ልጆች አንዱ አሁንም በሕይወት አለ፤ እርሱም እግረ ሽባ ነው” ሲል መለሰ። ንጉሡም “የት ነው ያለው?” ሲል ጠየቀ። ጺባም “በሎደባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ሲል መለሰ። ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት መፊቦሼትን ከሎደባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። የሳኦል የልጅ ልጅ፥ የዮናታን ልጅ መፊቦሼት በመጣ ጊዜ በዳዊት ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት አክብሮቱን ገለጠ። ዳዊትም “መፊቦሼት!” ሲል ጠራው። መፊቦሼትም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ ነኝ!” ሲል መለሰ። ዳዊትም “አይዞህ አትፍራ! ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግልሃለሁ፤ የአያትህ የሳኦል ይዞታ የነበረውን መሬት ሁሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም በማእዴ ተቀምጠህ ትመገባለህ” አለው። መፊቦሼትም በአክብሮት እጅ ነሥቶ “የሞተ ውሻ ልመመስል ለእኔ ለአገልጋይህ ይህን ያኽል ቸርነት የምታደርግልኝ ለምንድን ነው?” ከዚህ በኋላ ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ጺባን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ ንብረት የነበረውን ማናቸውንም ነገር የጌታህ የልጅ ልጅ ለሆነው ለመፊቦሼት እሰጣለሁ፤ አንተ፥ ወንዶች ልጆችህና አገልጋዮችህ ለጌታህ ለሳኦል ቤተሰብ ምድሪቱን አርሳችሁ ምግብ ይሆናቸው ዘንድ መከሩን አገቡላቸው፤ የጌታህ የልጅ ልጅ መፊቦሼት ግን ዘወትር በገበታዬ የሚቀርብ ተመጋቢ ይሆናል፤” ጺባ ዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆችና ኻያ አገልጋዮች ነበሩት። ጺባም “ንጉሥ ሆይ! እኔ አገልጋይህ አንተ ያዘዝከውን ሁሉ እፈጽማለሁ” ሲል መለሰ። በዚህ ዐይነት መፊቦሼት ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ተቈጥሮ በንጉሥ ገበታ እየቀረበ ይመገብ ነበር። መፊቦሼት ሚካ የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው፤ የጺባ ቤተሰብ አባሎች በሙሉ የመፊቦሼት አገልጋዮች ሆኑ፤ ስለዚህ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ የሆኑት መፊቦሼት በንጉሡ ገበታ እየቀረበ በመመገብ የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሆነ።
2 ሳሙኤል 9:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳዊትም፥ “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖር ይሆን?” በማለት ጠየቀ። በዚያን ጊዜ ከሳኦል ቤት ጺባ የሚባል አንድ አገልጋይ ስለ ነበር ወደ ዳዊት ጠሩት። ንጉሡም፥ “ጺባ የምትባለው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “አዎን እኔ አገልጋይህ ነኝ” አለ። ንጉሡም፥ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” ሲል ጠየቀው። ጺባም ለንጉሡ፥ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፥ “የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀ። ጺባም፥ “ሎደባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት። ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት፥ መፊቦሼትን ከዓሚኤል ከማኪር ቤት ከሎደባር ልኮ አስመጣው። የሳኦል ልጅ፥ የዮናታን ልጅ መፊቦሼት ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ። ዳዊትም፥ “መፊቦሼት!” ብሎ ጠራው። እርሱም፥ “እነሆ፤ አገልጋይህ” አለ። ዳዊትም፥ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግልሃለሁ። የአባትህን የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከማዕዴ ትበላለህ” አለው። መፊቦሼት ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፥ “እንደ ሞተ ውሻ ለምቆጠር ለእኔ ይህን ያህል የምታደርግልኝ አገልጋይህ ኧረ ማን ነኝ?” አለ። ከዚያም ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ጺባን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቸዋለሁ። አንተ፥ ልጆችህና አገልጋዮችህ የጌታችሁ የልጅ ልጅ የሚበላውን እንዲያገኝ መሬቱን እረሱለት፥ ምርቱንም አግቡለት። የጌታህ የልጅ ልጅ መፊቦሼት ግን ምንጊዜም ከማእዴ ይበላል።” በዚያን ጊዜ ጺባ ዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት። ከዚያም ጺባ ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ፥ አገልጋዩን ያዘዘውን ሁሉ፥ አገልጋይህ ይፈጽመዋል” አለው። ስለዚህም መፊቦሼት እንደ አንዱ ሆኖ ከዳዊት ማእድ ይበላ ነበር። መፊቦሼት ሚካ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ነበረው፤ የጺባ ቤተሰቦች በሙሉ መፊቦሼትን ያገለግሉት ነበር። መፊቦሼትም ሁልጊዜ ከንጉሥ ማእድ ስለሚበላ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፤ ሁለት እግሮቹም ሽባ ነበሩ።