2 ሳሙኤል 23:8-39

2 ሳሙኤል 23:8-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የዳ​ዊት ኀያ​ላን ስም ይህ ነው። የሦ​ስ​ተ​ኛው ክፍል አለቃ የሆነ ከነ​ዓ​ና​ዊው ኢያ​ቡ​ስቴ ነበረ፤ ጎራ​ዴ​ውን መዝዞ ስም​ንት መቶ ያህል ጭፍ​ሮ​ችን በአ​ንድ ጊዜ የገ​ደለ አሶ​ና​ዊው አዲ​ኖን ነበረ። ከእ​ር​ሱም በኋላ የዳ​ዊት የአ​ጎቱ ልጅ የዱዲ ልጅ ኤል​ያ​ናን ነበረ፤ ለሰ​ልፍ የተ​ሰ​በ​ሰ​ቡ​ትን ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን በተ​ገ​ዳ​ደሩ ጊዜ ከዳ​ዊት ጋር ከነ​በሩ ከሦ​ስቱ ኀያ​ላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሰዎች ተመ​ለሱ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እርሱ ተነ​ሥቶ እጁ እስ​ከ​ሚ​ደ​ክ​ምና ከሰ​ይፉ ጋር እስ​ኪ​ጣ​በቅ ድረስ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን መታ፤ በዚ​ያም ቀን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታላቅ መድ​ኀ​ኒት አደ​ረገ፤ ሕዝ​ቡም ከእ​ርሱ በኋላ የሞ​ቱ​ትን ለመ​ግ​ፈፍ ብቻ ተመ​ለሱ። ከእ​ር​ሱም በኋላ የአ​ሮ​ዳ​ዊው የአጌ ልጅ ሴሜይ ነበረ። ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም በቴ​ሪያ ተሰ​በ​ሰቡ። በዚ​ያም ምስር የሞ​ላ​በት የእ​ርሻ ክፍል ነበር፤ ሕዝ​ቡም ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ፊት ሸሹ። እርሱ ግን በእ​ር​ሻው መካ​ከል ቆሞ ጠበቀ፤ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ን​ንም ገደለ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ታላቅ መድ​ኀ​ኒት አደ​ረገ። ከሠ​ላ​ሳ​ውም አለ​ቆች ሦስቱ ወር​ደው ወደ ቃሶን ወደ ዳዊት ወደ አዶ​ላም ዋሻ መጡ፤ የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ጭፍራ በራ​ፋ​ይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። በዚያ ጊዜም ዳዊት በም​ሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ። ዳዊ​ትም፥ “በበሩ አጠ​ገብ ካለ​ችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠ​ጣኝ?” ብሎ ተመኘ። ያን​ጊ​ዜም የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ኀይል በቤተ ልሔም ነበረ። ሦስ​ቱም ኀያ​ላን የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን ሠራ​ዊት ሰን​ጥ​ቀው ሄዱ፤ በበ​ሩም አጠ​ገብ ካለ​ችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘ​ውም ለዳ​ዊት አመ​ጡ​ለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አል​ወ​ደ​ደም፤ ነገር ግን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አፈ​ሰ​ሰው። “አቤቱ፥ ይህን አደ​ርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ ነፍ​ሳ​ቸ​ውን ሰጥ​ተው የሄዱ ሰዎች ደም አይ​ደ​ለ​ምን?” ብሎ ይጠጣ ዘንድ አል​ወ​ደ​ደም። ሦስቱ ኀያ​ላ​ንም ያደ​ረ​ጉት ይህ ነው። የሶ​ር​ህ​ያም ልጅ የኢ​ዮ​አብ ወን​ድም አቢሳ የሦ​ስቱ አለቃ ነበር። እር​ሱም ጦሩን በሦ​ስቱ መቶ ላይ አን​ሥቶ ገደ​ላ​ቸው፤ ስሙም በሦ​ስቱ ዘንድ ተጠ​ርቶ ነበር። እር​ሱም ከሦ​ስቱ ይልቅ የከ​በረ ነበር፤ አለ​ቃ​ቸ​ውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አል​ደ​ረ​ሰም። በቀ​በ​ስ​ሄል የነ​በ​ረው ታላቅ ሥራ ያደ​ረ​ገው የዮ​ዳሄ ልጅ በና​ያስ የሞ​ዓ​ባ​ዊ​ውን የአ​ር​ኤ​ልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአ​መ​ዳ​ዩም ወራት ወርዶ በጕ​ድ​ጓድ ውስጥ አን​በሳ ገደለ። እር​ሱም ልዩ የሆ​ነ​ውን ግብ​ፃዊ ሰው ገደለ፤ ግብ​ፃ​ዊ​ውም በእጁ ዛቢ​ያው እንደ ድል​ድይ ዕን​ጨት የሆነ ጦር ነበ​ረው፤ በና​ያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፤ ከግ​ብ​ፃ​ዊ​ውም እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደ​ለው። የዮ​ዳሄ ልጅ በና​ያስ ያደ​ረ​ገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦ​ስቱ ኀያ​ላን ተጠ​ርቶ ነበር። ከሦ​ስ​ቱም ይልቅ የከ​በረ ነበረ፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አል​ደ​ረ​ሰም። ዳዊ​ትም ትእ​ዛዝ አስ​ከ​ባሪ አድ​ርጎ ሾመው። የዳ​ዊት ኀያ​ላ​ንም ስማ​ቸው ይህ ነው። የኢ​ዮ​አብ ወን​ድም አሣ​ሄል በሠ​ላ​ሳው መካ​ከል ነበረ፤ የቤተ ልሔም ሰው የአ​ጎቱ የዱዲ ልጅ ኤል​ያ​ናን፥ አሮ​ዳ​ዊው ሴሜይ፥ ሔሮ​ዳ​ዊው አል​ያቃ፥ ፈል​ጣ​ዊው ሴሌ፥ የቴ​ቁ​ሓ​ዊው የኤ​ስካ ልጅ ዔራስ፥ ከአ​ስ​ቲጡ ልጆች ወገን የሚ​ሆን አና​ቶ​ታ​ዊው አብ​ዔ​ዜር፥ የኤ​ሎ​ንያ ሰው ኤላን፥ የፋጤ ሰው ናኤ​ሬት፥ የአ​ን​ጢፋ ሰው የቦ​አና ልጅ ሔሌብ፥ ከብ​ን​ያም ወገን ከጌ​ብዓ የረ​ባይ ልጅ ኢታይ፥ ኤፍ​ራ​ታ​ዊው በና​ያስ፥ የአ​ብ​ሪስ ሰው አሶም፥ ዓረ​ባ​ዊው አቤ​ዔ​ል​ቦን፥ አል​ሞ​ና​ዊው ኤማ​ሱ​ኖስ፥ አሴ​ሌ​ቦ​ና​ዊው ኤል​ያ​ሕባ፥ የአ​ሶን ልጅ ዮና​ታን፥ አሮ​ዳ​ዊው ሳም​ናን፥ የሓ​ተ​ራ​ዊው የሶሬ ልጅ አም​ናን፥ የመ​ካኪ ልጅ የአ​ሶብ ልጅ ኤላ​ፍ​ላት፥ የጊ​ሎ​ና​ዊው የአ​ኪ​ጦ​ፌል ልጅ ኤል​ያብ፥ ቀር​ሜ​ሎ​ሳ​ዊው አሰሬ፥ አረ​ባ​ዊው ኤፌዎ፥ የና​ታን ልጅ ኤአኪ፥ ከገ​ዓድ ልጆች ወገን ማሶባ፥ አሞ​ና​ዊው ኤልዩ፥ የሶ​ር​ህያ ልጅ የኢ​ዮ​አብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮ​ታ​ዊው ጌሎሬ፥ ኤተ​ራ​ዊው ዒራስ፥ ኢታ​ና​ዊው ጋሬብ፥ ኬጤ​ያ​ዊው ኦርዮ፤ ሁሉም በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።

2 ሳሙኤል 23:8-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም ይህ ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሴብ በሴትቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፣ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው የገደለ ነው። ከርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፣ ከዳዊት ጋራ ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሸሹ። እርሱ ግን የቆመበትን ስፍራ አልለቀቀም፤ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋራ እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድልን ሰጠ። የሸሸውም ሰራዊት ወደ ኤልዔዘር የተመለሰው የተገደሉትን ሰዎች ለመግፈፍ ብቻ ነበር። ከርሱም ቀጥሎ የሃራራዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ሌሒ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ዕርሻ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፣ የእስራኤል ሰራዊት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሣማ ግን የቆመበትን ስፍራ አልለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድል ሰጣቸው። በመከር ወራት፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ። በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተ ልሔም ነበረ፤ ዳዊትም በናፍቆት፣ “በቤተ ልሔም በር አጠገብ ካለችው ጕድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። ስለዚህ ሦስቱ ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፣ በቤተ ልሔም በር አጠገብ ካለችው ጕድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አድርጎ አፈሰሰው፤ “እርሱም፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላደርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” አለ፤ ዳዊትም ሊጠጣው አልፈለገም። እንግዲህ ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር። የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ እርሱም ዝናን ያተረፈ ሰው ነበረ። አቢሳ ከሦስቱ ይልቅ እጅግ የከበረ አልነበረምን? ከእነርሱ እንደ አንዱ ባይሆንም አለቃቸው ነበረ። የቀብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ታላቅ ጀብዱ የሠራ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ እርሱም ሁለት በጣም የታወቁ የሞዓብ ሰዎችን ገደለ፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጕድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሏል፤ ደግሞም አንድ ግዙፍ ግብጻዊ ገድሏል፤ ግብጻዊው በእጁ ጦር የያዘ ቢሆንም፣ በናያስ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ወደ እርሱ ሄደ፤ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው። የዮዳሄ ልጅ የበናያስ ጀብዱ እንደዚህ ያለ ነበረ፤ እርሱም እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ ከሠላሳዎቹ ሁሉ በላይ የከበረ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከሦስቱ እንደ አንዱ አልነበረም። ዳዊትም የክብር ዘበኞቹ አለቃ አድርጎ ሾመው። ከሠላሳዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣ አሮዳዊው ሣማ፣ አሮዳዊው ኤሊቃ፣ ፈሊጣዊው ሴሌስ፣ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ፣ የዓናቶቱ ሰው አቢዔዜር፤ ኩሳታዊው ምቡናይ፣ አሆሃዊው ጸልሞን፣ ነጦፋዊው ማህራይ፣ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፣ ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣ ጲርዓቶናዊው በናያስ፣ የገዓስ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፣ ዐረባዊው አቢዓልቦን፣ በርሑማዊው ዓዝሞት፣ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣ የአሳን ልጆች፤ ዮናታን የተባለው፣ የሃራራዊው የሣማ ልጅ፣ የሃራራዊው የሻራር ልጅ አሒአም፤ የማዕካታዊው የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፣ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊአም፣ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፤ አርባዊው ፈዓራይ፣ የሱባ ሰው የሆነው የናታን ልጅ ይግአል፣ ጋዳዊው ባኒ፣ አሞናዊው ጼሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጦር መሣሪያ ያዥ የነበረው ብኤሮታዊው ነሃራይ፣ ይትራዊው ዒራስ፣ ይትራዊው ጋሬብ፣ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮ።

2 ሳሙኤል 23:8-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የዳዊት ኃያላን ስም ይህ ነው። የአለቆች አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፥ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ያህል በአንድ ጊዜ ገደለ። ከእርሱም በኋላ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፥ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከሦስቱ ኃያላን አንዱ እርሱ ነበረ፥ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ። እርሱ ግን ተነሥቶ እጁ እስኪደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኃኒት አደረገ፥ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ። ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት እርሻ በአንድነት ሆነው ተካማችተው ነበር፥ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፥ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኃኒት አደረገ። ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ። ዳዊትም፦ በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ? ብሎ ተመኘ። ሦስቱም ኃያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፥ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፥ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ፦ አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፥ በነፍሳቸው ደፍረው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን? ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሠላሳው አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ ስሙም እንደ ሦስቱ ተጠርቶ ነበር። እርሱ በሠላሳው መካከል የከበረ አልነበረምን? ስለዚህም አለቃቸው ሆኖ ነበር፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። በቀብጽኤል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የቀብስኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፥ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። ረጅሙንም ግብጻዊ ሰው ገደለ፥ ግብጻዊው በእጁ ጦር ነበረው፥ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው። የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፥ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር። ከሠላሳውም ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በክብር ዘበኞቹ ላይ ሾመው። የኢዮአብም ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፥ የቤተ ልሔም ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ አሮዳዊው ሣማ፥ ሒሮዳዊው ኤሊቃ፥ ፈልጣዊው ሴሌስ፥ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ምቡናይ፥ አሆሃዊው ጸልሞን፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ በርሑማዊው ዓዝሞት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የአሳን ልጆች፥ ዮናታን፥ አሮዳዊው ሣማ፥ የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የማዕካታዊው ልጅ የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ አርባዊው ፈዓራይ፥ የሱባ ሰው የናታን ልጅ ይግዓል፥ ጋዳዊው ባኒ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሞናዊው ጼሌቅ፥ ብኤሮታዊው ነሃራይ፥ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥ ኬጢያዊው ኦርዮ፥ ሁሉ በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።

2 ሳሙኤል 23:8-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች ስም ዝርዝር ከዚህ በታች እንደ ተመለከተው ነው፤ የመጀመሪያው የታሕክሞን ተወላጅ ዮሼብ ባሼቤት የተባለው ሲሆን እርሱም ከሦስቱ ኀያላን ብልጫ ያለው ተቀዳሚ ነው፤ ይህ ሰው በአንድ ውጊያ ላይ ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ኀያላን ሰዎችን ገደለ። ከሦስቱ ኀያላን ሁለተኛው ከአሖሕ ጐሣ የሆነው ዝነኛው የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነበር፤ አንድ ቀን እርሱና ዳዊት ለጦርነት ተሰልፈው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያን ተገዳደሩ፤ እስራኤላውያን ወደ ኋላቸው አፈገፈጉ፤ ይህ ሰው ግን ባለበት ጸንቶ በመቆም እጁ ዝሎ በሰይፉ ላይ እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድልን አደረገ፤ ጦርነቱም ከቆመ በኋላ እስራኤላውያን አልዓዛር ወደነበረበት ስፍራ ተመልሰው ከሞቱት ፍልስጥኤማውያን ብዙ የጦር ልብስ ማረኩ። ከሦስቱ ኀያላን ሦስተኛው ደግሞ የሃራር ተወላጅ የሆነው ዝነኛው የአጌ ልጅ ሻማ ነበር፤ አንድ ቀን ፍልስጥኤማውያን የምስር ማሳ ባለበት በሌሒ ተሰልፈው ነበር፤ እስራኤላውያንም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሻማ ግን በዚያው በማሳው ውስጥ ጸንቶ ቆመ፤ በመከላከልም ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድልን አደረገ። በመከር ጊዜ መጀመሪያ ላይ ከሠላሳው ኀያላን በተለይ ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዐዱላም ዋሻ ወረዱ፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ጥቂቱ ክፍል በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር፤ ዳዊት በዚያን ጊዜ በተመሸገ ኮረብታ ላይ ነበር፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት አንድ ቡድን ቤተልሔምን በመውረር ያዘ፤ ዳዊትም አገሩን በመናፈቅ “በቤተልሔም ቅጽር በር አጠገብ ካለው የውሃ ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ የሚያመጣልኝ ሰው ምነው ባገኘሁ!” አለ። ስለዚህ ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር በድፍረት ጥሰው በማለፍ ከጒድጓዱ ውሃ ቀድተው ለዳዊት ይዘውለት መጡ፤ ዳዊት ግን ሊጠጣ አልወደደም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ ለእግዚአብሔር መባ አድርጎ ካፈሰሰው በኋላ፥ “እግዚአብሔር ሆይ! ይህን ውሃ ከቶ ልጠጣው አልችልም! እኔ እርሱን ብጠጣ፥ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ኀያላን ሰዎች ደም እንደ ጠጣሁ ይቈጠራል!” አለ፤ ውሃውንም መጠጣት እምቢ አለ። ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፈጸሙአቸው የጀግንነት ተግባሮች እነዚህ ናቸው። የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ ዝነኞች የሆኑት የሠላሳዎቹ ወታደሮች አለቃ ነበር፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ከሦስት መቶ ሰዎች ጋር በመዋጋት ሁሉንም ገደለ፤ ስለዚህም እንደ ሦስቱ ዝነኛ ሆነ። ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ዝነኛ በመሆኑም የእነርሱ አለቃ ሆነ፤ ይሁን እንጂ የሦስቱን ጀግኖች ያኽል ዝነኛ አልነበረም። ሌላው ዝነኛ ወታደር የቃብጽኤል ተወላጅ የነበረው የዮዳሄ ልጅ በናያ ነበር፤ እርሱም ሁለት የታወቁ ሞአባውያን ወታደሮችን ከመግደሉም ሌላ ብዙ የጀግንነት ሥራ ፈጽሞአል፤ አንድ ጊዜ በምድር ላይ ዐመዳይ በወረደበት ቀን ወደ አንድ ዋሻ ወርዶ አንበሳ ገደለ፤ እንዲሁም ጦር ይዞ የነበረውን አንድ ኀያል ግብጻዊ ገድሎአል፤ ይኸውም በናያ በእጁ ከበትር በስተቀር ሌላ የጦር መሣሪያ ሳይዝ ወደ ግብጻዊው ቀርቦ የገዛ ጦሩን በመቀማት በዚያው ጦር ግብጻዊውን ገደለው። እንግዲህ እንደ ሦስቱ ኀያላን ዝነኛ የሆነው በናያ የፈጸማቸው የጀግንነት ሥራዎች እነዚህ ናቸው፤ ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ታዋቂ ቢሆንም በዝነኛነቱ ከሦስቱ ኀያላን ደረጃ አልደረሰም፤ ዳዊትም በናያን የክብር ዘቡ አዛዥ አድርጎ ሾሞት ነበር። ከሠላሳዎቹ መካከል የሌሎቹ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ የኢዮአብ ወንድም ዐሣሄል፤ የቤተልሔሙ ተወላጅ የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፤ የሐሮድ ተወላጆች የሆኑት ሻማና ኤሊቃ፤ የፌሌጥ ተወላጅ የሆነው ሔሌጽ፤ የተቆዓ ተወላጅ የሆነው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፤ የዐናቶት ተወላጅ የሆነው አቢዔዜር፤ የሑሻ ተወላጅ የሆነው መቡናይ፤ የአሖሕ ተወላጅ የሆነው ጻልሞን፤ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው ማህራይ፤ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው የባዕና ልጅ ሔሌብ፤ በብንያም ግዛት የምትገኘው የጊብዓ ተወላጅ የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፤ የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው በናያ፤ በጋዓሽ ሸለቆ አጠገብ የተወለደው ሂዳይ፤ የዓርባ ተወላጅ የሆነው ኢቢዓልቦን፤ የባርሑም ተወላጅ የሆነው ዓዝማዌት፤ የሻዓልቦን ተወላጅ የሆነው ኤልያሕባ፤ የያሼን ልጆች፤ ዮናትን፤ የሐራር ተወላጅ የሆነው ሻማ፤ የሐራር ተወላጅ የሆነው የሻራር ልጅ አሒአም፤ የማዕካ ተወላጅ የሆነው የአሐሰባይ ልጅ ኤሊፌሌጥ፤ የጊሎ ተወላጅ የሆነው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊዓም፤ የቀርሜሎስ ተወላጅ የሆነው ሔጽሮ፤ የዐረብ ተወላጅ የሆነው ፓዓራይ፤ የጾባ ልጅ የሆነው የናታን ልጅ ዪግአል የጋድ ተወላጅ የሆነው ባኒ፤ የዐሞን ተወላጅ የሆነው ጼሌቅ፤ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ የነበረውና የበኤሮት ተወላጅ የሆነው ናሕራይ፤ የያቲር ተወላጆች የሆኑት ዒራና ጋሬብ፤ ሒታዊው ኦርዮን። ዝነኞች የሆኑት ኀያላን ወታደሮች ጠቅላላ ድምር ሠላሳ ሰባት ነበር።

2 ሳሙኤል 23:8-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሼብ ባሼቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፥ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው በአንዴ የገደለ ነው። ከእርሱ ቀጥሎ የአሆህዊው የዶዶ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፥ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች አፈገፈጉ። እርሱ ግን ተነስቶ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት ጌታ ታላቅ ድልን አደረገ። ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ። ከእርሱም ቀጥሎ የሃራርታዊው የአጌ ልጅ ሻማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት ሌሒ በተባለ ስፍራ አንድ እርሻ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ነበር። ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሻማ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት ጌታ ታላቅ ድልን አደረገ። ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዱላም ዋሻ መጡ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሠራዊት በቤተልሔም ነበረ፤ ዳዊትም በናፍቆት፥ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። ሦስቱም ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፥ በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በጌታ ፊት አፈሰሰው፤ “እርሱም፥ ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላደርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቆርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” ብሎ፥ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱ ኀያላን ሰዎች የፈጸሙአቸው ተግባሮች እነዚህ ነበሩ። የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና ስሙም ከሦስቱ ኀያላን ጋር የሚጠራ ነበረ። እርሱ ከሠላሳው ይልቅ እጅግ ዝነኛ ስለ ነበር፤ አለቃቸው ሆኖ ነበር፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ ደረጃ አልደረሰም። የቃብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያም ታላቅ ተግባር የፈፀመ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ ሁለቱን በጣም የታወቁ የሞዓብን ሰዎችን ገድሎአል፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሎአል፤ አንድ ማራኪ ግብፃዊንም ገድሎአል፤ ግብፃዊው በእጁ ጦር ይዞ፥ በናያ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ነበር ወደ እርሱ የሄደው፤ ከግብፃዊውም እጅ የገዛ ጦሩን በመንጠቅ ገደለው። የዮዳሄ ልጅ በናያ ያደረገው ይህ ነው፥ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር። ከሠላሳዎቹ ይልቅ የከበረ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከሦስቱ እንደ አንዱ አልነበረም። ዳዊትም የክብር ዘበኞቹ አለቃ አድርጎ ሾመው። ከሠላሳዎቹ መካከል፦ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተልሔሙ ሰው የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፥ ሐሮዳዊው ሻማ፥ ሐሮዳዊው ኤሊቃ፥ ፈሌጣዊው ሴሌስ፥ የቴቆአዊው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፤ ሑሻዊው መቡናይ፥ አሆሃዊው ጻልሞን፥ ነጦፋዊው ማህራይ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ተወላጅ የሆነው የጊብዓ ሰው የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያ፥ የገዓሽ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ ባርሑማዊው ዓዝማዌት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የያሼን ልጆች፤ ዮናታን፥ የሐራራዊው የሻማ ልጅ፥ የሐራራዊው የሻራር ልጅ አሒአም፤ የማዕካታዊው የአሐሰባይ ልጅ ኤሊፌሌጥ፥ የጊሎናዊው የአሒጦፌል ልጅ ኤሊአም፥ ቀርሜሎሳዊው ሔጽሮ፤ አርባዊው ፈዓራይ፥ የጾባዊው የናታን ልጅ ይግዓል፥ አሞናዊው ጸሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ የነበረው በኤሮታዊው ናሕራይ፥ ያቲራዊው ዒራ፥ ያቲራዊው ጋሬብ፥ ሒታዊው ኦርዮ፤ በጠቅላላው ሠላሳ ሰባት ነበሩ።