2 ሳሙኤል 11:2-27
2 ሳሙኤል 11:2-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፤ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱም ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ የተዋበች መልከ መልካም ነበረች። ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም፥ “የኤልያብ ልጅ የኬጤያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለው። ዳዊትም መልእክተኞችን ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፤ ከርኵሰቷም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤቷም ተመለሰች። ሴቲቱም አረገዘች፤ ወደ ዳዊትም “አርግዤአለሁ” ብላ ላከችበት። ዳዊትም ወደ ኢዮአብ፦ ኬጤያዊውን ኦርዮን ወዲህ ላከው ብሎ ላከ። ኢዮአብም ኦርዮን ወደ ዳዊት ላከው። ኦርዮም ደርሶ ወደ እርሱ በገባ ጊዜ ዳዊት የኢዮአብንና የሕዝቡን ደኅንነት፥ ሰልፉም እንዴት እንደ ሆነ ጠየቀው። ዳዊትም ኦርዮን፥ “ወደ ቤትህ ሂድ፤ እግርህንም ታጠብ” አለው። ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ አንድ የንጉሥ መልእክተኛ ተከተለው። ኦርዮ ግን ከጌታው አገልጋዮች ሁሉ ጋር በንጉሥ ቤት ደጅ ተኛ፤ ወደ ቤቱም አልወረደም። “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም ኦርዮን፥ “አንተ ከመንገድ የመጣህ አይደለህምን? ስለምን ወደ ቤትህ አልወረድህም?” አለው። ኦርዮም ለዳዊት፥ “የእግዚአብሔር ታቦትና እስራኤል፥ ይሁዳም በድንኳን ተቀምጠዋል፤ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም አገልጋዮች በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል፤ እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳለሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም” አለው። ዳዊትም ኦርዮን፥ “ዛሬ ደግሞ በዚህ ተቀመጥ፤ ነገም አሰናብትሃለሁ” አለው። ኦርዮም በዚያ ቀንና በነጋው በኢየሩሳሌም ተቀመጠ። ዳዊትም ጠራው፤ በፊቱም በላና ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው አገልጋዮች ጋር በምንጣፉ ላይ ተኛ፤ ወደ ቤቱም አልወረደም። በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈ፤ በኦርዮም እጅ ላከው። በደብዳቤውም፥ “ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፤ ተወግቶም ይሞት ዘንድ ከኋላ ሽሹ” ብሎ ጻፈ። ኢዮአብም ከተማዪቱን በከበበ ጊዜ ጀግኖች እንዳሉበት በሚያውቀው ስፍራ ኦርዮን አቆመው። የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ተዋጉ፤ ከዳዊትም አገልጋዮች ከሕዝቡ አንዳንዱ ወደቁ፤ ኬጤያዊው ኦርዮም ደግሞ ሞተ። ኢዮአብም የጦርነቱን ዜና ሁሉ ለዳዊት ይነግሩት ዘንድ ላከ፤ ለመልእክተኛውም እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “የጦርነቱን ነገር ሁሉ ለንጉሡ ነግረህ በፈጸምህ ጊዜ፤ ንጉሡ ቢቈጣ፥ እንዲህም ቢል፦ ልትዋጉ ወደ ከተማዪቱ ለምን ቀረባችሁ? ከቅጥሩ በላይ ፍላጻ እንዲወረወር አታውቁምን? የኔር ልጅ የይሩበዓልን ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? አንዲት ሴት ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላበት የሞተ አይደለምን? ስለምን ወደ ቅጥሩ እንደዚህ ቀረባችሁ? አንተም፦ ባሪያህ ኬጤያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ በለው።” የኢዮአብም መልእክተኛ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ንጉሡ ሄደ። ደርሶም ኢዮአብ የነገረውን የጦርነቱን ዜና ሁሉ ለዳዊት ነገረው። ዳዊትም በኢዮአብ ላይ ተቈጣ። ያንም መልእክተኛ፥ “ትዋጉ ዘንድ ወደ ከተማዋ ቅጥር ለምን ቀረባችሁ? በቅጥሩም እንደምትቈስሉ አታውቁምን? የይሩበዓል ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? አንዲት ሴት ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላበት በቴቤስ የሞተ አይደለምን? ስለምን ወደ ቅጥሩ ቀረባችሁ?” አለው። መልእክተኛውም ዳዊትን፥ “ሰዎቹ በረቱብን፤ ወደ ሜዳም ወጡብን፤ እኛም እስከ በሩ መግቢያ ድረስ አሳደድናቸው። ፍላጻም የሚወረውሩ በቅጥሩ ላይ ሆነው በአገልጋዮችህ ላይ ወረወሩ፤ ከንጉሡም ብላቴኖች አንዳንድ ሞቱ፤ አገልጋይህ ኬጤያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ” አለው። ዳዊትም መልእክተኛውን፥ “ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፥ አንድ ጊዜም ያን ይበላልና ይህ ነገር በዐይንህ አይክፋ፤ ከተማዪቱን የሚወጉትን አበርታ፤ አፍርሳትም ብለህ ለኢዮአብ ንገረው፤ አንተም አጽናው” አለው። የኦርዮም ሚስት ባልዋ ኦርዮ እንደ ሞተ በሰማች ጊዜ ለባልዋ አለቀሰች። የልቅሶዋም ወራት ሲፈጸም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስትም ሆነችው፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ።
2 ሳሙኤል 11:2-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን ማታ፣ ዳዊት ከዐልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፣ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች። ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ አጠያየቀ። ሰውየውም፣ “ይህች የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ። ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሯትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርኃዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች። ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፣ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት። ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፣ “ኬጢያዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ወደ ዳዊት ላከው። ኦርዮን በመጣ ጊዜም፣ ዳዊት የኢዮአብንና የሰራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፣ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም ማለፊያ ምግብ አስከትሎ ላከለት። ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ሁሉ ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ፣ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር። ዳዊት፣ “ኦርዮን ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮን፣ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኦርዮም ዳዊትን፣ “ታቦቱ፣ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፣ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፣ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? እንዲህ ያለውን ነገር እንደማላደርገው በነፍስህ እምላለሁ” አለው። ከዚያም ዳዊት፣ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ ዕደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮን በዚያ ዕለትና በማግስቱም እዚያው ኢየሩሳሌም ቈየ። በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮን በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አሽከሮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፤ በደብዳቤውም ላይ፣ “ኦርዮ ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ። ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፣ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮን መደበው። የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሰራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ። ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ። መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፣ ንጉሡ በቍጣ ቱግ ብሎ ‘ለመዋጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለ ምንድን ነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰድዱባችሁ አታውቁም ኖሯል? የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቅቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ቢጠይቅህ፣ አንተም መልሰህ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቷል’ ብለህ ንገረው።” ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደ ደረሰም፣ ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው። መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ ዐየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳድደን መለስናቸው። ከዚያም ባለ ፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፣ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።” ዳዊትም፣ መልእክተኛውን፣ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፣ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን’ ” አለው። የኦርዮን ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ ዐዘነች፤ አለቀሰችለትም። የሐዘኑ ጊዜ ካበቃ በኋላም፣ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት የሠራው ሥራ እግዚአብሔርን አላስደሰተውም ነበር።
2 ሳሙኤል 11:2-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፥ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፥ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፥ አንድ ሰውም፦ ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ። ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፥ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኩሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፥ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም፦ አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት። ዳዊትም ወደ ኢዮአብ፦ ኬጢያዊውን አርዮን ስደድልኝ ብሎ ላከ። ኢዮአብም ኦርዮን ወደ ዳዊት ሰደደው። ኦርዮም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዳዊት የኢዮአብንና የሕዝቡን ደኅንነት፥ ሰልፉም እንዴት እንደ ሆነ ጠየቀው። ዳዊትም ኦርዮን፦ ወደ ቤትህ ሂድ፥ እግርህንም ታጠብ አለው። ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ የንጉሥ መብል ተከትሎት ሄደ። ኦርዮ ግን ከጌታው ባሪያዎች ሁሉ ጋር በንጉሥ ቤት ደጅ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም። ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም ብለው ለዳዊት ነገሩት፥ ዳዊትም ኦርዮን፦ አንተ ከመንገድ የመጣህ አይደለምን? ስለ ምን ወደ ቤትህ አልወረድህም? አለው። ኦርዮም ዳዊትን፦ ታቦቱና እስራኤል ይሁዳም በጎጆ ተቀምጠዋል፥ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ባሪያዎች በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳላሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም አለው። ዳዊትም ኦርዮን፦ ዛሬ ደግሞ በዚህ ተቀመጥ፥ ነገም አሰናብትሃለሁ አለው። ኦርዮም በዚያ ቀንና በነጋው በኢየሩሳሌም ተቀመጠ። ዳዊትም ጠራው፦ በፊቱም በላና ጠጣ፥ አሰከረውም፥ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው ባሪያዎች ጋር በምንጣፉ ላይ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም። በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈ፥ በኦርዮም እጅ ላከው። በደብዳቤውም፦ ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፥ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ጻፈ። ኢዮአብም ከተማይቱን በከበበ ጊዜ ጀግኖች እንዳሉበት በሚያውቀው ስፍራ ኦርዮን አቆመው። የከተማይቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ተዋጉ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከሕዝቡ አንዳንዱ ወደቁ፥ ኬጢያዊው ኦርዮም ደግሞ ሞተ። ኢዮአብም ልኮ በሰልፍ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። ለመልእክተኛውም እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ የሰልፉን ነገር ሁሉ ለንጉሡ ነግረህ በፈጸምህ ጊዜ፥ ስትዋጉ ወደ ከተማይቱ ለምን ቀረባችሁ? ከቅጥሩ በላይ ፍላጻ እንዲወረወር አታውቁምን? የሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላ በቴቤስ ላይ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ስለ ምን ወደ ቅጥሩ እንደዚህ ቀርባችሁ? ብሎ ንጉሡ ሲቆጣ ብታይ፥ አንተ፦ ባሪያህ ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ በለው። መልእክተኛውም ተነሥቶ ሄደ፥ ኢዮአብም ያዘዘውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። መልእክተኛውም ዳዊትን፦ ሰዎቹ በረቱብን፥ ወደ ሜዳም ወጡብን፥ እኛም ወደቅንባቸው፥ እስከ ከተማይቱም በር ድረስ ተከተልናቸው። ፍላጻ የሚወረውሩም በቅጥሩ ላይ ሆነው በባሪያዎችህ ላይ ወረወሩ፥ ከንጉሡም ባሪያዎች አንዳንድ ሞቱ፥ ባሪያህም ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ አለው። ዳዊትም መልእክተኛውን፦ ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜም ያን ያጠፋልና ይህ ነገር በዓይንህ አይክፋ፥ ከተማይቱን የሚወጉትን አበርታ፥ አፍርሳትም ብለህ ለኢዮአብ ንገረው፥ አንተም አጽናው አለው። የኦርዮም ሚስት ባልዋ ኦርዮ እንደሞተ በሰማች ጊዜ ለባልዋ አለቀሰች። የልቅሶዋም ወራት ሲፈጸም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወንድ ልጅም ወለደችለት ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ።
2 ሳሙኤል 11:2-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ከቀትር በኋላ ዘግየት ብሎ ዳዊት ከቀን እንቅልፉ ነቅቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወጣ፤ እዚያም ወዲያና ወዲህ ሲመላለስ ገላዋን የምትታጠብ አንዲት ሴት አየ፤ ሴትዮዋም በጣም ውብ ነበረች፤ ስለዚህ ማንነትዋን ለማወቅ ዳዊት አንድ መልእክተኛ ልኮ ቤርሳቤህ ተብላ የምትጠራው የኤሊዓም ልጅ፥ የሒታዊው የኦርዮ ሚስት መሆንዋን ተረዳ። እርስዋንም ሄደው ያመጡለት ዘንድ ዳዊት መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ሄደው አመጡለትና ከእርስዋ ጋር ግንኙነት አደረገ፤ በዚህም ጊዜ ሴትዮዋ ወርኃዊ የመንጻት ሥርዓትዋን የፈጸመች ጥብቅ ነበረች፤ ከዚህ በኋላ ሴትዮዋ ወደ ቤትዋ ተመልሳ ሄደች። ከጊዜ በኋላም መፅነስዋን ስለ ተገነዘበች መልእክት ልካ ለዳዊት ነገረችው። ከዚህ በኋላ ዳዊት “ሒታዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ላከው” ሲል ወደ ኢዮአብ መልእክት ሰደደ፤ ስለዚህም ኢዮአብ ኦርዮን ወደ ዳዊት ላከው፤ ኦርዮ በደረሰ ጊዜ ዳዊት “ኢዮአብና ሠራዊቱ ሁሉ እንዴት ናቸው? የጦርነቱስ ሁኔታ እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀው፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት ኦርዮን “እንግዲህ ወደ ቤትህ ሂድና እግርህን ታጠብ” አለው፤ ኦርዮም ከዳዊት ፊት ወጥቶ ሄደ፤ ዳዊትም ወዲያውኑ የምግብ ስጦታ ላከለት፤ ኦርዮ ግን ወደ ቤቱ ሳይሄድ ከንጉሡ ክብር ዘበኞች ጋር በቤተ መንግሥቱ የቅጽር በር አጠገብ ተኝቶ ዐደረ፤ ኦርዮ ወደ ቤቱ አለመሄዱን ዳዊት በሰማ ጊዜ “ብዙ ጊዜ ከቤተሰብህ ተለይተህ እነሆ አሁን ገና መመለስህ ነው፤ ታዲያ ወደ ቤትህ ያልሄድከው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኦርዮም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች በድንኳን ሰፍረው በጦር ሜዳ ይገኛሉ፤ የቃል ኪዳኑም ታቦት ከእነርሱ ጋር ነው፤ የጦር አለቃዬ ኢዮአብና የእርሱም የጦር መኰንኖች በሜዳ ሰፍረዋል፤ ታዲያ እኔ ወደ ቤቴ ሄጄ መብላት፥ መጠጣት፥ ከሚስቴም ጋር መተኛት እንዴት ይቻለኛል? ይህን የመሰለ ነገር ከቶ እንደማላደርግ በአንተ ሕይወት እምላለሁ!” ዳዊትም “በል እንግዲህ የዛሬን እዚህ ዋል፤ ነገ ግን መልሼ እልክሃለሁ” አለው፤ ስለዚህ ኦርዮ በዚያን ቀንና በሚቀጥለው ቀን በኢየሩሳሌም ቈየ፤ ዳዊትም ኦርዮን ራት ጋበዘውና እስኪሰክር ድረስ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ አደረገው፤ በዚያም ሌሊት ኦርዮ በቤተ መንግሥቱ ዘበኞች ቤት ብርድ ልብሱን በማንጠፍ ተኝቶ ዐደረ እንጂ ወደ ቤቱ አልሄደም። በማግስቱም ጧት ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈና በኦርዮ እጅ ላከው፤ የጻፈውም ቃል “ኦርዮን ጦርነቱ በተፋፋመበት ግንባር አሰልፈው፤ ከዚያም አንተ ወደ ኋላ አፈግፍገህ እርሱ እንዲገደል አድርገው” የሚል ነበር። በዚህ ዐይነት ኢዮአብ ከተማይቱን ከቦ በመያዝ ላይ ሳለ ጠላት ማየሉን በሚያውቅበት ስፍራ ኦርዮን አሰለፈው። የጠላት ወታደሮች ከከተማይቱ ወጥተው የኢዮአብን ሠራዊት ወጉ፤ ከዳዊት የጦር መኰንኖች ጥቂቶቹ ሞቱ፤ ኦርዮም አብሮ ሞተ። ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ስለ ጦርነቱ የሚያስረዳ መልእክት ወደ ዳዊት ላከ፤ ለመልእክተኛውም እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጠው፤ “ስለ ጦርነቱ ሁሉን ነገር ለንጉሡ ካስረዳህ በኋላ፥ ንጉሡ ተቈጥቶ እንዲህ ይልህ ይሆናል፥ ‘እነርሱን ለመውጋት ወደ ከተማይቱ ለምን ተጠጋችሁ? በግንብ ላይ ሆነው ፍላጻዎችን እንደሚወረውሩባችሁ አላወቃችሁምን? የጌዴዎን ልጅ አቤሜሌክ እንዴት እንደ ሞተ አታስታውሱምን? እርሱን ቴቤጽ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ አንዲት ሴት ከግንብ ላይ የወፍጮ ድንጋይ ናዳ በመጣል ገደለችው፤ ታዲያ እናንተ ወደ ግንብ የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ ንጉሡ ይህን ጥያቄ ቢያቀርብልህ፥ ‘የጦር መኰንንህ ኦርዮም ተገድሎአል’ ብለህ ንገረው።” ስለዚህም መልእክተኛው ወደ ዳዊት ሄዶ ኢዮአብ ያዘዘውን ሁሉ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “ጠላቶቻችን ስለ በረቱብን እኛን ለመውጋት ከከተማይቱ ወጥተው ወደ ሜዳ መጡ፤ እኛ ግን አሳደን ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር መለስናቸው። ከዚያም በኋላ በግንብ ላይ ሆነው ፍላጻዎችን ወረወሩብን፤ ንጉሥ ሆይ! ከጦር መኰንኖችህ ጥቂቶቹ በዚያን ጊዜ ሞቱ፤ አገልጋይህ ኦርዮም ተገደለ።” ዳዊትም መልእክተኛውን “እንዲህ ብለህ ለኢዮአብ ንገረው፦ በጦርነት ላይ ማን እንደሚሞት በቅድሚያ ስለማይታወቅ ‘አይዞህ በርታ’ በለው፤ ብስጭት እንዳያድርበትም ንገረው፤ ይልቁንም ኀይሉን አጠናክሮ አደጋ በመጣል ከተማይቱን እንዲይዝ አስጠንቅቀው” አለው። የኦርዮ ሚስት ባልዋ እንደ ተገደለ በሰማች ጊዜ በማልቀስ አዘነችለት፤ የሐዘንዋም ጊዜ ሲፈጸም ዳዊት ሰው ልኮ ወደ ቤተ መንግሥት አስመጣት፤ ለእርሱም ሚስት ሆና ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር እግዚአብሔርን አሳዘነ።
2 ሳሙኤል 11:2-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንድ ቀን ማታ፥ ዳዊት ከአልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፥ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ ውብ ነበረች። ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ። እርሱም፥ “ይህች የኤሊዓም ልጅ፥ የሒታዊው የኦርዮን ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ። ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሮአትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርሐዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች። ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፥ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት። ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፥ “ሒታዊውን ኦርዮንን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ኦርዮንን ወደ ዳዊት ላከው። ኦርዮን በመጣ ጊዜም፥ ዳዊት የኢዮአብንና የሠራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። ከዚያም ዳዊት ኦርዮንን፥ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም የምግብ ስጦታ ላከለት። ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር። ዳዊት፥ “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮንን፥ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኦርዮም ዳዊትን፥ “ታቦቱ፥ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፥ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፥ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም” አለው። ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፥ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮ በዚያ ዕለትና በማግስቱ በኢየሩሳሌም ቆየ። በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮ በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አገልጋዮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮ እጅ ላከለት፤ በደብዳቤውም ላይ፥ “ኦርዮን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ። ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፥ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮንን መደበው። የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሠራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ሒታዊው ኦርዮንም ሞተ። ከዚያም ኢዮአብ በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ። መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፥ ንጉሡ በቁጣ ቱግ ብሎ እንዲህ ይልህ ይሆናል፥ ‘ለመውጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለ ምንድነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል? የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤጽ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ አንተም መልሰህ፥ ‘አገልጋይህ ሒታዊው ኦርዮም ሞቷል’ ብለህ ንገረው።” ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደደረሰም ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው። መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳደን መለስናቸው። ከዚያም ባለፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፥ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ሒታዊው ኦርዮም ሞተ።” ዳዊትም፥ መልእክተኛውን፥ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፥ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን’ ” አለው። የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ ኀዘን ተቀመጠች። የሐዘኑ ጊዜ ካበቃ በኋላም፥ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት የሠራው ሥራ ጌታን አላስደሰተውም ነበር።