2 ሳሙኤል 1:1-27
2 ሳሙኤል 1:1-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመለሰ፤ ዳዊትም በሴቄላቅ ሁለት ቀን ተቀመጠ። በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሰፈር ከሳኦል ወገን አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ፥ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፤ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በምድር ላይ ወድቆ ሰገደለት። ዳዊትም፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው፤ እርሱም፥ “ከእስራኤል ሰፈር አምልጬ መጣሁ” አለው። ዳዊትም፥ “ነገሩ ምንድን ነው? እስኪ ንገረኝ” አለው። እርሱም መልሶ፥ “ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፤ ከሕዝቡም ብዙው ወደቁ፤ ሞቱም፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ደግሞ ሞተዋል” አለው። ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ጐልማሳ፥ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ እንዴት ዐወቅህ?” አለው። ወሬውን ያመጣለት ጎልማሳም አለ፥ “በጌላቡሄ ተራራ ተዋግተው ወደቁ፤ እነሆም፥ ሳኦል በጦሩ ላይ ተኝቶ ነበር፤ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፤ እኔም፦ እነሆኝ አልሁ። እርሱም፦ አንተ ማን ነህ? አለኝ፤ እኔም አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። እርሱም፦ ክፉ ጨለማ ይዞኛልና ደግሞ እስካሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያውት ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። እኔም ከወደቀ በኋላ አለመዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ፥ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፤ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት።” ዳዊትም ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። በጦር ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፥ ለይሁዳም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ጐልማሳ፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ እርሱም፥ “እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም፥ “ትገድለው ዘንድ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጅህን ስትዘረጋ እንዴት አልፈራህም?” አለው። ዳዊትም ከብላቴኖቹ አንዱን ጠርቶ፥ “ሂድና ግደለው” አለው፤ ገደለውም። ዳዊትም፥ “እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው። ዳዊትም ስለ ሳኦልና ስለ ልጁ ዮናታን ይህን የኀዘን ቅኔ ተቀኘ፤ የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ ይህ በጻድቃን መጽሐፍ ተጽፎአል። “እስራኤል ሆይ፥ ለሞቱትና ለተገደሉት ሐውልት ትከል፤ ኀያላን እንዴት ወደቁ! የፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች ደስ እንዳይላቸው፥ የቈላፋንም ሴቶች ልጆች እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፤ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ። እናንተ የጌላቡሄ ተራሮች ሆይ፥ ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፤ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ። የኀያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና፤ የሳኦልም ጋሻ ዘይት አልተቀባምና። ከሞቱት ደምና ከኀያላን ስብ፥ የዮናታን ቀስት ባዶዋን አልተመለሰችም፤ የሳኦልም ሰይፍ ባዶዋን አልተመለሰችም። ሳኦልና ዮናታን የተወደዱና ያማሩ ነበሩ፤ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፤ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። የእስራኤል ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ያስጌጣችሁ ለነበረ ለሳኦል አልቅሱለት። ኀያላን በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታን ሆይ፥ ሌሎችም የተመቱት በኮረብቶችህ ላይ ወደቁ። ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ አንተ በእኔ ዘንድ እጅግ የተወደድህ ነበርህ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ። ኀያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃዎች እንዴት ጠፉ!”
2 ሳሙኤል 1:1-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳኦል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ በመመለስ፣ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቈየ። በሦስተኛውም ቀን የተቀደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም፣ ወደ መሬት ለጥ ብሎ በአክብሮት እጅ ነሣ። ዳዊትም፣ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር ሸሽቼ መምጣቴ ነው” በማለት መለሰለት። ዳዊትም፣ “ምን ነገር ተፈጠረ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋል፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ። ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፣ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት ዐወቅህ?” ሲል ጠየቀው። ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት። ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም፣ ‘ምን ልታዘዝ’ አልሁ። “እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፤ “እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት። “ከዚያም፣ ‘እኔ በሞት ጣር ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ። “መቼም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፣ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፤ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።” ከዚያም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፣ ለእግዚአብሔር ሰራዊትና ለእስራኤል ቤት ዐዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ፤ የወደቁት በሰይፍ ነበርና። ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ። ዳዊትም፣ “ታዲያ እግዚአብሔር የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው። ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “በል ቅረብና ውደቅበት” አለው። እርሱም መታው፤ ሞተም። ዳዊትም፣ “ ‘እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፣ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው። ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የሐዘን እንጕርጕሮ እየተቀኘ አለቀሰ፤ እንዲሁም የቀስት እንጕርጕሮ የተባለውን ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፏል። “እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል፤ ኀያላኑ እንዴት እንደዚህ ይውደቁ! “ይህን በጌት አትናገሩ፤ በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁት፤ የፍልስጥኤም ቈነጃጅት አይደሰቱ፤ ያልተገረዙት ሴቶች ልጆች እልል አይበሉ። “እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤ ጠል አያረስርሳችሁ፤ ዝናብም አይውረድባችሁ፤ የቍርባን እህል የሚያበቅሉም ዕርሻዎች አይኑራቸው፤ በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሷልና፤ የሳኦል ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም። “ከሞቱት ሰዎች ደም፣ ከኀያላኑም ሥብ፣ የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም። ሳኦልና ዮናታን በሕይወት እያሉ፣ የሚዋደዱና የሚስማሙ ነበሩ፤ ሲሞቱም አልተለያዩም፤ ከንስርም ይልቅ ፈጣኖች፣ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። “እናንት የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፤ ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፣ ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፣ ለሳኦል አልቅሱለት። “ኀያላን እንዴት እንዲህ በጦርነት ወደቁ! ዮናታን በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል። ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ ዐዘንሁ፤ አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤ ከሴት ፍቅርም ይልቅ ግሩም ነበር። “ኀያላኑ እንዴት ወደቁ! የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ከንቱ ይሁኑ!”
2 ሳሙኤል 1:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመልሶ በጺቅላግ ሁለት ቀን ያህል ተቀመጠ። በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፥ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ። ዳዊትም፦ ከወዴት መጣህ? አለው፥ እርሱም፦ ከእስራኤል ሰፈር ኮብልዬ መጣሁ አለው። ዳዊትም፦ ነገሩ እንደ ምን ሆነ? እስኪ ንገረኝ አለው። እርሱም መልሶ፦ ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፥ ከሕዝቡ ብዙው ወደቁ ሞቱም፥ ሳኦልና ልጁም ዮናታን ደግሞ ሞተዋል አለ። ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ፦ ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ በምን ታውቃለህ? አለው። ወሬኛውም ጕልማሳ አለ፦ በድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ መጣሁ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ቆሞ ነበር፥ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፥ እኔም፦ እነሆኝ አልሁ። እርሱም፦ አንተ ማን ነህ? አለኝ፥ እኔም፦ አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። እርሱም፦ ሰውነቴ ዝሎአልና፥ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያው ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። እኔም ከወደቀ በኋላ አለ መዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፥ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፥ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ይዘው ቀደዱ። በሰይፍም ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ለእግዚአብሔርም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፥ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ፦ አንተ ከወዴት ነህ? አለው፥ እርሱም፦ እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ ብሎ መለሰለት። ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው። ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፦ ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም። ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው። ዳዊትም ስለ ሳኦልና ሰለ ልጁ ስለ ዮናታን ይህን የኅዘን ቅኔ ተቀኘ፥ የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል። የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ፥ ኃያላን እንዴት ወደቁ! የፍልስጥኤማውያን ቈነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፥ የቆላፋንም ቈነጃጅት እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፥ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ። እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ። ከሞቱት ደምና ከኃያላን ስብ የዮናታን ቀስት አልተመለሰችም፥ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም። ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፥ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፥ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፥ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት። ኃያላንም በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታንም በኮረብቶችህ ላይ ወድቆአል። ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፥ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበር፥ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ። ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!
2 ሳሙኤል 1:1-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት ዐማሌቃውያንን ድል አድርጎ ተመለሰ፤ በጺቅላግም ሁለት ቀን ቈየ፤ በሦስተኛው ቀን አንድ ወጣት ከሳኦል ሰፈር መጣ፤ ልብሱን ቀዶ በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ ነበር፤ ወደ ዳዊትም ቀርቦ በአክብሮት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ ዳዊትም “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ከእስራኤላውያን ሰፈር አምልጬ የመጣሁ ነኝ” ሲል መለሰ። ዳዊትም “እስቲ የሆነውን ሁሉ ንገረኝ” አለው። እርሱም “ሠራዊታችን ከጦር ግንባር ሸሸ፤ ከሰዎቻችንም ብዙዎቹ ሞቱ፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ። ዳዊትም ወሬ ያመጣውን ወጣት “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት ዐወቅህ?” ሲል ጠየቀው። ወጣቱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ነበርኩ፤ ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ የጠላት ሠረገሎችና ፈረሰኞች ወደ እነርሱ ሲጠጉ አየሁ፤ እርሱም ወደ ኋላ መለስ ሲል እኔን አየኝና ጠራኝ፤ እኔም ‘ጌታዬ፥ እነሆ አለሁ!’ አልኩት፤ ማን እንደ ሆንኩ በጠየቀኝ ጊዜም ዐማሌቃዊ መሆኔን ነገርኩት፤ እርሱም ‘ወደ እኔ ቀርበህ ግደለኝ፤ በብርቱ ስለ ቈሰልኩ መሞቴ ነው!’ አለኝ፤ በሚወድቅበት ጊዜ እንደሚሞት ዐውቅ ስለ ነበር ወደ እርሱ ቀርቤ ገደልኩት፤ ከዚህ በኋላ ዘውዱን ከራሱ ላይ፥ አንባሩንም ከክንዱ ላይ ወሰድኩ፤ ጌታዬ ሆይ! እነሆ፥ እነርሱን ለአንተ አመጣሁልህ።” ዳዊትም በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ተከታዮቹ ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ፤ በሰይፍ ስለ ተገደሉ ለሳኦል፥ ለልጁ ለዮናታንና ለእግዚአብሔር ሠራዊት ለመላው እስራኤል እስከ ምሽት ድረስ በመጾም በከባድ ሐዘን አለቀሱላቸው። ዳዊትም ወሬውን ይዞ የመጣውን ያንን ወጣት “የየት አገር ሰው ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “በሀገርህ ውስጥ በመጻተኛነት የሚኖር የዐማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰለት። ዳዊትም “ታዲያ እግዚአብሔር መርጦ የቀባውን ንጉሥ ለመግደል እንዴት ደፈርክ?” ሲል ጠየቀው። ከዚህ በኋላ ዳዊት ከተከታዮቹ አንዱን ጠርቶ “ግደለው!” ሲል አዘዘው፤ ሰውየውም ዐማሌቃዊውን መትቶ ገደለው፤ ዳዊትም ዐማሌቃዊውን “ይህን ጥፋት በራስህ ላይ ያመጣህ አንተው ራስህ ነህ፤ እግዚአብሔር መርጦ የቀባውን ንጉሥ ገድያለሁ ብለህ በተናገርክ ጊዜ በራስህ ላይ ፈርደሃል” አለው። ዳዊት ስለ ሳኦልና ስለ ልጁም ስለ ዮናታን ይህን የሐዘን ቅኔ ተቀኘ፤ የይሁዳም ሕዝብ ያጠኑት ዘንድ አዘዘ፤ ቅኔውም በያሻር መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፦ “እስራኤል ሆይ! ያንተ ጀግና በተራሮች ላይ ተገድሎ ወደቀ! ኀያላኑ እንዴት ወደቁ! የፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች እንዳይደሰቱ፥ የአሕዛብ ሴቶች ልጆች እልል እንዳይሉ፥ ይህን ወሬ በጋት አታውሩ፤ በአስቀሎናም አደባባይ አታውጁ። “እናንተ የጊልቦዓ ተራራዎች ሆይ! ዝንብም ሆነ ጤዛ አይውረድባችሁ! የእርሻ መሬቶቻችሁም ምንም ነገር አይብቀልባቸው! የጀግኖች ጋሻዎች እዚያ በውርደት ወድቀዋልና፤ የሳኦልም ጋሻ በዘይት መወልወሉ ቀርቶአልና። የዮናታን ቀስት ሳይገድል የማይመለስ፥ የሳኦልም ሰይፍ ጠላትን የሚቈራርጥ ኀያላንን መትቶ የሚሰብር፥ ጠላትን የሚገድል ነበር። “ሳኦልና ዮናታን በአስደናቂ ፍቅር ኖሩ፤ በሕይወትም ሆነ በሞት ላለመለያየት ተባበሩ፤ እነርሱም ከንስር የፈጠኑ፥ ከአንበሳም የበረቱ ነበሩ። “የእስራኤል ሴቶች ሆይ! ውድ የሆነ ሐምራዊ ቀሚስ ያለብሳችሁ ለነበረው በወርቀ ዘቦም ላስጌጣችሁ፥ ለሳኦል አልቅሱለት! “በጦርነቱ መካከል ኀያላን እንዴት ወደቁ? ዮናታን በተራሮችህ ላይ ተገድሎ ወድቆአል። “ወንድሜ ዮናታን ሆይ! እኔ ስለ አንተ በጣም አዘንኩ፤ አንተ ለእኔ በጣም ተወዳጅ ነበርክ። ፍቅርህ ለእኔ አስደናቂ ነበር፤ ይኸውም ከሴት ፍቅር የበረታ ነበር። “ኀያላን እንዴት ወደቁ? የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ጠፉ?”
2 ሳሙኤል 1:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሳኦል ከሞተ በኋላ፥ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ ሲመለስ፥ ሁለት ቀን በጺቅላግ ቆየ። በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ የተቀደደ ልብስ የለበሰ፥ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት መጥቶም በግምባሩ በመደፋት እጅ ነሣ። ዳዊትም፥ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “ከእስራኤላውያን ሰፈር አምልጬ መጣሁ” በማለት መለሰለት። ዳዊትም፥ “እስቲ ምን ነገር እንደተፈጠረ ንገረኝ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋልም፤ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ። ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፥ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው። ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ሳለ፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከትለው ደረሱበት፤ ወደ ኋላውም ዞር ሲል አየኝና ጠራኝ፤ እኔም፥ ‘እነሆ አለሁ!’ አልኩት። እርሱም፥ ‘አንተ ማን ነህ?’ ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስኩለት። ከዚያም፥ ‘እኔ የሞት ጣር ይዞኛል፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ። እኔም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፥ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና በክንዱ ላይ የነበረውን አንባር ወስጄ፥ እነሆ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።” ከዚያም ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ። የወደቁት በሰይፍ ነበርና፥ ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፥ ለጌታ ሠራዊትና ለእስራኤል ቤትም አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፥ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ። ዳዊትም፥ “ታዲያ ጌታ የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው። ከዚህ በኋላ ዳዊት ከጉልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፥ “በል ቅረብና ግደለው!” አለው። እርሱም መታው፤ ገደለውም። ዳዊትም፥ “ ‘ጌታ የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፥ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው። ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ የይሁዳንም ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ እነሆ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። “እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል! ኀያላኑ እንዴት ወደቁ! የፍልስጥኤም ቆነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፤ ያልተገረዙት ሴት ልጆች እልል እንዳይሉ፤ ይህን በጌት አትናገሩ፤ በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁ፤ እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤ በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፤ የሳኦል ጋሻ በዘይት መወልወሉ ቀርቶአልና፤ ጠልም ሆነ ዝናብ አይውረድባችሁ፤ የቁርባን እህል የሚያበቅሉም እርሻዎች አይኑራችሁ። ከሞቱት ሰዎች ደም፥ ከኀያላኑም ሥብ፥ የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም። ሳኦልና ዮናታን፥ የተዋደዱና የተስማሙ፤ በሕይወትም ሆነ በሞት ያልተለያዩ፤ ከንስርም ይልቅ የፈጠኑ፥ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። እናንት የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ! ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፥ ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፥ ለሳኦል አልቅሱ። ኀያላን እንዴት በጦርነት ወደቁ! ዮናታን በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል። ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤ አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤ ከሴት ፍቅርም ይልቅ የበረታ ነበር። ኀያላን እንዴት ወደቁ! የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ጠፉ!”