2 ጴጥሮስ 1:1-11
2 ጴጥሮስ 1:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤ የመለኮቱ ኀይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ በተስፋው ቃል ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፤ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፤ የቀደመውንም ኀጢአቱን መንጻት ረስቶአል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና።
2 ጴጥሮስ 1:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ስምዖን ጴጥሮስ፤ በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤ እግዚአብሔርንና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል። ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ካለው ምግባረ ብልሹ ሕይወት አምልጣችሁ፣ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ በእነዚህ ነገሮች አማካይነት እጅግ ታላቅና ክቡር የሆነውን ተስፋ ሰጥቶናል። በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ባሕርያት ተትረፍርፈው ቢኖሯችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች ከመሆን ይጠብቋችኋል። እነዚህ ባሕርያት የሌሉት ግን የሩቁን የማያይ ወይም ዕውር ነው፤ ከቀድሞው ኀጢአቱ መንጻቱንም ረስቷል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ምክንያቱም እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህም ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል።
2 ጴጥሮስ 1:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፦ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፦ የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና።
2 ጴጥሮስ 1:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፥ ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጽድቅ አማካይነት እኛ እንዳገኘነው እምነት ያለ የከበረ እምነት ላገኛችሁት፤ እግዚአብሔርንና ጌታችንን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። በክብሩና በደግነቱ የጠራንን እርሱን በማወቃችን መለኮታዊ ኀይሉ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚያስፈልገንን ሁሉ ሰጥቶናል። በክብሩና በቸርነቱ ክቡር ዋጋ ያለውንና እጅግ ታላቅ የሆነውን ተስፋውን አግኝተናል፤ በእነዚህም አማካይነት እናንተ በክፉ ምኞት ምክንያት በዚህ ዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች ሆናችኋል። በዚህ ምክንያት የሚከተሉት ነገሮች እንዲጨመሩላችሁ ትጉ፦ በእምነት ላይ ደግነትን፥ በደግነት ላይ ዕውቀትን፥ በዕውቀት ላይ ራስ መቈጣጠርን፥ በራስ መቈጣጠር ላይ በትዕግሥት መጽናትን፥ በትዕግሥት በመጽናት ላይ እግዚአብሔርን ማምለክን፥ እግዚአብሔርን በማምለክ ላይ የወንድማማችነት መዋደድን፥ በወንድማማችነት መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች በብዛት ቢኖሩአችሁ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ የማትጠቅሙ ፍሬቢሶች እንዳትሆኑ ይጠብቁአችኋል። እነዚህ ነገሮች የሌሉት ግን የሩቁን ነገር ማየት የማይችል ዕውር ነው፤ ካለፉት ኃጢአቶቹም መንጻቱን ረስቶአል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማረጋገጥ በይበልጥ የምትጓጉ ሁኑ፤ ይህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህ ዐይነት ዘለዓለማዊት ወደሆነችው ወደ ጌታችንና ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ለመግባት ሙሉ መብት ይሰጣችኋል።
2 ጴጥሮስ 1:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር አቻ የሆነ ክቡር እምነትን ላገኙ፤ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። በመለኮቱ ኃይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ሰጠን። በእነዚህም አማካኝነት፥ ከክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ፥ በተስፋው ቃል ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ፥ በክብርና በበጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። በዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ ሠናይነትን ጨምሩ፥ በሠናይነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችነት መዋደድ፥ በወንድማማችነትም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ቢኖሩአችሁና ቢበዙላችሁ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ በተመለከተ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ግን የሩቁን ነገር ማየት የማይችል ዕውር ነው፤ ከቀደመው ኀጢአቱም መንጻቱን ረስቷአል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁንና መመረጣችሁን እንድታጸኑ፥ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ይህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህ መልክ፥ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል።