2 ቆሮንቶስ 7:5-12
2 ቆሮንቶስ 7:5-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ መቄዶንያም በደረስን ጊዜ ለሰውነታችን ጥቂት ስንኳን ዕረፍት አላገኘንም፤ በሁሉም መከራ አጸኑብን እንጂ፤ በውጭም መጋደል ነበር፤ በውስጥም ፍርሀት ነበር። ነገር ግን ያዘኑትን የሚያጽናና እርሱ እግዚአብሔር በቲቶ መምጣት አጽናናን። በመምጣቱ ብቻ አይደለም፤ በአጽናናችሁት ማጽናናትም ነው እንጂ፤ ለእኛ እንደምታስቡና እንደምትቀኑ ፍቅራችሁን ነግሮናል፤ ይህንም ሰምቼ ደስታዬ በእናንተ በዛ። መጀመሪያ በጻፍሁት መልእክት ባሳዝናችሁም እንኳ አያጸጽተኝም፤ ብጸጸትም፥ እነሆ ያች መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘነቻችሁ አያለሁ። አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፤ ደስታዬም ስለ አዘናችሁ አይደለም፤ ንስሓ ልትገቡ ስለ አዘናችሁ እንጂ፤ ከእናንተ አንዱ ስንኳ እንዳይጠፋ፥ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ አዝናችኋልና። ስለ እግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ኀዘን የዘለዓለም ሕይወትን የሚያሰጥ ንስሓ ነው። ስለ ዓለም የሚደረግ ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ያ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ ያደረጋችሁት ኀዘን ምንም የማታውቁ እስከ መሆን ደርሳችሁ፥ ራሳችሁን በበጎ ሥራና በንጽሕና እስክታጸኑ ድረስ፥ ትጋትንና ክርክርን፥ ቍጣንና ፍርሀትን፥ ናፍቆትንና ቅንዐትን፥ በቀልንም አደረገላችሁ፤ ይህን የጻፍሁላችሁ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ እንደ ተጋችሁ ይታወቅ ዘንድ ነው እንጂ ስለ በደለና ስለ ተበደለ ሰው አይደለም።
2 ቆሮንቶስ 7:5-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ፣ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን። ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል። በመልእክቴ ባሳዝናችሁም በዚህ አልጸጸትም፤ ብጸጸትም እንኳ መልእክቴ ያሳዘናችሁ ለጥቂት ጊዜ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ። አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ ደስታዬም ስላዘናችሁ ሳይሆን፣ ሐዘናችሁ ንስሓ ለመግባት ስላበቃችሁ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተነሣ ምንም አልተጐዳችሁም። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል። ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅናት፣ እንዴት ያለ ተግሣጽ እንዳስገኘላችሁ ተመልከቱ። በዚህም ጕዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል። እንግዲህ እኔ የጻፍሁላችሁ ስለ በደለው ወይም ስለ ተበደለው ሰው አይደለም፤ ነገር ግን ለእኛ ምን ያህል ታማኞች እንደ ሆናችሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን እንድታዩ በማለት ነው።
2 ቆሮንቶስ 7:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን። በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል። እንግዲያስ የጻፍሁላችሁ ብሆን እንኳ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በዳዩ ወይም ስለ ተበዳዩ አልጻፍሁም። ስለዚህ ተጽናንተናል።
2 ቆሮንቶስ 7:5-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መቄዶንያ በደረስን ጊዜ እንኳ ከብዙ አቅጣጫ ችግር ደረሰብን እንጂ ምንም ዕረፍት አላገኘንም፤ በውጭ ጠብ በውስጥም ፍርሀት ነበረብን። ነገር ግን የተዋረዱትን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተ እርሱን ያጽናናችሁት መሆኑን በመስማታችንም ጭምር ነው፤ ስለ እኔ ያላችሁን ናፍቆትና ሐዘን ጭንቀትም በነገረን ጊዜ ይበልጥ ደስ አለኝ። ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁ መልእክት ያሳዘናችሁ ቢሆንም እንኳ መልእክቱን በመጻፌ አልጸጸትም፤ ተጸጽቼም ብሆን እንኳ የተጸጸትኩት መልእክቴ ለጥቂት ጊዜ ስላሳዘናችሁ ነው። አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ የተደሰትኩበትም ምክንያት እናንተን ስላሳዘንኳችሁ ሳይሆን በሐዘናችሁ ምክንያት ንስሓ ገብታችሁ በመለወጣችሁ ነው፤ እንግዲህ ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ እኛ ምንም አልበደልናችሁም ማለት ነው። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ሐዘን ወደ መዳን የሚመራ በንስሓ የሚገኘውን ለውጥ ስለሚያስገኝ ጸጸትን አያስከትልም፤ ዓለማዊ ሐዘን ግን ሞትን ያመጣል። ይህ ሐዘናችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ እንዴት ያለ የመከላከያ መልስ መስጠትን፥ እንዴት ያለ ቶሎ መቈጣትን፥ እንዴት ያለ ፍርሀትን፥ እንዴት ያለ ናፍቆትን፥ እንዴት ያለ ቅናትን፥ እንዴት ያለ ቅጣትንም እንዳስከተለ ልብ ብላችሁ አስተውሉ። እናንተ ደግሞ በሁሉም ነገር ከጉዳዩ ነጻ መሆናችሁን አስመስክራችኋል። ስለዚህ ምንም እንኳ ለእናንተ ብጽፍ እኔ የጻፍኩላችሁ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋት በእግዚአብሔር ፊት ለእናንተ ግልጥ እንዲሆን ብዬ ነው እንጂ በደል ስለ ሠራውና በደል ስለ ተፈጸመበት ሰው ብዬ አይደለም።
2 ቆሮንቶስ 7:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አልነበረውም፤ ከውጭ ጠብ ነበረ፤ ከውስጥ ደግሞ ፍርሃት ነበረብን። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም የነበራችሁን ቅንዓት ሲነገረን በእናንተ ስለተጽናናን ማለቴ ነው፤ ስለዚህም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ አለኝ። በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ ተረድቻለሁ፤ አሁን ግን ሐዘናችሁ ወደ ንስሓ ስለመራችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ደስታዬ ስለ ሐዘናችሁ አይደለም፤ በማንኛውም መንገድ በእኛ በኩል እንድትጎዱ አንፈልግም። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ወደ መዳን ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም፤ ዓለማዊው ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ለእንዴት ዓይነት ትጋት፥ ለእንዴት ዓይነት ራስን የማንጻት ጉጉት፥ ለእንዴት ዓይነት ቊጣ፥ ለእንዴት ዓይነት ፍርሃት፥ ለእንዴት ዓይነት ናፍቆት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅንዓት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅጣት እንዳደረሳችሁ ተመልከቱ! በዚህም ጉዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል። እንግዲያስ ጽፌው እንኳን ቢሆን ኖሮ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋት በእናንተ በኩል በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በደለኛ ወይም ስለ ተበዳይ አይደለም የጻፍኩት።