2 ቆሮንቶስ 7:2-7
2 ቆሮንቶስ 7:2-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ታገሡን፥ የበደልነው የለም፤ የገፋነውም የለም፤ ያጠፋነውም የለም፤ የቀማነውም የለም። ይህንም የምለው በእናንተ ለመፍረድ አይደለም፤ ለሞትም፥ ለሕይወትም ቢሆን እናንተ በልባችን እንዳላችሁ ፈጽሜ ተናግሬአለሁና። በእናንተ ዘንድ እንዲሁ ብዙ መወደድ አለኝ፤ ስለ እናንተም የምመካበት ብዙ ነው፤ መጽናናትንም አገኘሁ፤ ከመከራዬም ሁሉ ይልቅ ደስታዬ በዛልኝ። ወደ መቄዶንያም በደረስን ጊዜ ለሰውነታችን ጥቂት ስንኳን ዕረፍት አላገኘንም፤ በሁሉም መከራ አጸኑብን እንጂ፤ በውጭም መጋደል ነበር፤ በውስጥም ፍርሀት ነበር። ነገር ግን ያዘኑትን የሚያጽናና እርሱ እግዚአብሔር በቲቶ መምጣት አጽናናን። በመምጣቱ ብቻ አይደለም፤ በአጽናናችሁት ማጽናናትም ነው እንጂ፤ ለእኛ እንደምታስቡና እንደምትቀኑ ፍቅራችሁን ነግሮናል፤ ይህንም ሰምቼ ደስታዬ በእናንተ በዛ።
2 ቆሮንቶስ 7:2-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልባችሁን አስፉልን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም ወደ ብልሹነት አልመራንም፤ ማንንም አላታለልንም። ይህን የምለው ልኰንናችሁ አይደለም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርኋችሁ፣ በልባችን ውስጥ ስፍራ አላችሁ፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም ዐብረን ነው። በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ትልቅ ነው፤ በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ፣ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን። ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል።
2 ቆሮንቶስ 7:2-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በልባችሁ ስፍራ አስፉልን፤ ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም። ለኵነኔ አልልም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና። ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፥ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከመጠን ይልቅ ይበዛል። ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን።
2 ቆሮንቶስ 7:2-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከልባችሁ ተቀበሉን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አልጐዳንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም። ይህንንም የምለው በእናንተ ላይ ለመፍረድ አይደለም። ከዚህ በፊት እንደ ነገርኳችሁ እናንተ በልባችን ውስጥ ናችሁ፤ ስለዚህ በሕይወትም ሆነ በሞት ሁልጊዜ ከእናንተ አንለይም። በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ከፍተኛ ነው፤ በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ በእናንተም እጽናናለሁ፤ በመከራችን ሁሉ በጣም እደሰታለሁ። መቄዶንያ በደረስን ጊዜ እንኳ ከብዙ አቅጣጫ ችግር ደረሰብን እንጂ ምንም ዕረፍት አላገኘንም፤ በውጭ ጠብ በውስጥም ፍርሀት ነበረብን። ነገር ግን የተዋረዱትን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተ እርሱን ያጽናናችሁት መሆኑን በመስማታችንም ጭምር ነው፤ ስለ እኔ ያላችሁን ናፍቆትና ሐዘን ጭንቀትም በነገረን ጊዜ ይበልጥ ደስ አለኝ።
2 ቆሮንቶስ 7:2-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በልባችሁ ስፍራ አኑሩን፤ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አላጭበረበርንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም። ይህን የምለው እናንተን ለመኮነን አይደለም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን ስፍራ እንዳላችሁ አስቀድሜ ተናግሬለሁ። ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፤ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ እኔም በመጽናናት ተሞልቻለሁ፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አልነበረውም፤ ከውጭ ጠብ ነበረ፤ ከውስጥ ደግሞ ፍርሃት ነበረብን። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም የነበራችሁን ቅንዓት ሲነገረን በእናንተ ስለተጽናናን ማለቴ ነው፤ ስለዚህም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ አለኝ።